በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

ሉቃስ 1:37—“ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና”

ሉቃስ 1:37—“ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና”

 “አምላክ የተናገረው ቃል ሳይፈጸም አይቀርምና።”—ሉቃስ 1:37 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና።”—ሉቃስ 1:37 የ1954 ትርጉም

የሉቃስ 1:37 ትርጉም

 ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በሰው ዓይን የማይቻሉ የሚመስሉ ነገሮችን ማድረግ ይችላል። የተናገረውን ወይም ቃል የገባውን ነገር ከመፈጸም ሊያግደው የሚችል ነገር የለም።

 በበኩረ ጽሑፉ ላይ የሚገኘው “የተናገረው” ተብሎ የተተረጎመው ቃል አንድን “ቃል” ወይም “አባባል” ሊያመለክት ይችላል፤ በዚህ ጥቅስ መሠረት ደግሞ አምላክ የተናገረውን “ቃል” ወይም “አባባል” ያመለክታል። ይሖዋ a አምላክ የተናገረው ነገር የሚያስገኘውን ውጤትም ሊያመለክት ይችላል። አምላክ የሚናገረው ቃል ሁሌም ስለሚፈጸም ሉቃስ 1:37 ላይ ያለው ሐሳብ “አምላክ የገባው ቃል ሁሉ በእርግጥ ይፈጸማልና” ወይም “አምላክ የማይችለው ነገር የለምና” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። እነዚህ አተረጓጎሞች በግሪክኛው በኩረ ጽሑፍ ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ተመሳሳይ መሠረታዊ እውነታ የሚያስተላልፉ ናቸው፦ አምላክ ምንም የሚሳነው ነገር ስለሌለ የተናገረው ነገር ወይም የገባው ቃል ሁሉ ይፈጸማል።—ኢሳይያስ 55:10, 11

 አምላክ ስለሰጠው ተስፋ የሚናገሩ ተመሳሳይ አገላለጾች በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም ላይ ይገኛሉ። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ ልጅ ያልነበራት የአብርሃም ሚስት ሣራ በስተርጅናዋ እንደምትፀንስ በአንድ መልአክ አማካኝነት ተናግሮ ነበር። አክሎም “ለይሖዋ የሚሳነው ነገር አለ?” በማለት ተናገረ። (ዘፍጥረት 18:13, 14) ኢዮብ በአምላክ የፍጥረት ሥራ ላይ ካሰላሰለ በኋላ “አንተ . . . ያሰብከውን ነገር ሁሉ ማድረግ እንደማይሳንህ አሁን አወቅኩ” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 42:2) የኢየሱስ ተከታዮች መዳን ለማግኘት አምላክ ያወጣውን መሥፈርት ማሟላት ስለመቻላቸው ጥርጣሬ ባደረባቸው ጊዜ ኢየሱስ “በአምላክ ዘንድ ግን ሁሉ ነገር ይቻላል” በማለት አበረታቷቸዋል።—ማቴዎስ 19:25, 26 b

የሉቃስ 1:37 አውድ

 በሉቃስ 1:37 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ማርያም ለተባለች አይሁዳዊት ድንግል የነገራት ገብርኤል የተባለ መልአክ ነው። ገብርኤል ለማርያም ‘የልዑሉን አምላክ ልጅ’ እንደምትወልድና “ስሙንም ኢየሱስ” ብላ እንደምትጠራው ነግሯት ነበር። ይህ ልጅ ለዘላለም የሚገዛው የአምላክ መንግሥት ንጉሥ እንደሚሆንም ነገራት።—ሉቃስ 1:26-33፤ ራእይ 11:15

 በዚህ ጊዜ ማርያም ስላላገባችና ‘ከወንድ ጋር ግንኙነት ፈጽማ ስለማታውቅ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?’ በማለት ጠየቀች። (ሉቃስ 1:34, 35) ገብርኤል፣ አምላክ ቅዱስ መንፈሱን ማለትም የተለያዩ ነገሮችን ለማከናወን የሚጠቀምበትን ኃይሉን እንደሚጠቀም ነገራት። በወቅቱ ኢየሱስ በሰማይ የሚኖር የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ ነበር። ስለዚህ ይሖዋ የልጁን ሕይወት ከሰማይ ወደ ማርያም ማህፀን ለማዛወር ቅዱስ መንፈሱን ተጠቅሟል። (ዮሐንስ 1:14፤ ፊልጵስዩስ 2:5-7) በመሆኑም ማርያም በተአምራዊ ሁኔታ ፀነሰች። መልአኩ፣ ማርያም በአምላክ ኃይል ላይ ያላትን እምነት ለማጠናከር ሲል ዘመዷ ኤልሳቤጥም “በስተርጅናዋ” ወንድ ልጅ እንደፀነሰች ነገራት። ኤልሳቤጥ መሃን ስለነበረች እሷና ባሏ ዘካርያስ ልጅ አልነበራቸውም። (ሉቃስ 1:36) በኋላም የወለዱት ልጅ መጥምቁ ዮሐንስ ሆነ፤ ይሖዋ ስለ ዮሐንስ አገልግሎትም አስቀድሞ ተናግሮ ነበር።—ሉቃስ 1:10-16፤ 3:1-6

 ከዚያም መልአኩ ገብርኤል በሉቃስ 1:37 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ተናገረ፤ ምናልባት ይህን ሐሳብ የተናገረው ማርያምንና ኤልሳቤጥን በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ቃላት በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ሕዝቦችም ይሖዋ ቃሉን እንደሚጠብቅ ያላቸውን እምነት ያጠናክሩላቸዋል። አምላክ የገባው ቃል ሰብዓዊ መንግሥታትን ማጥፋትንና እነዚህን መንግሥታት በጽድቅ የሚገዛው ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተዳድረው ሰማያዊ መንግሥት መተካትን ይጨምራል።—ዳንኤል 2:44፤ 7:13, 14

 የሉቃስ መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።

a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።