በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና

ልጆችን ስለ ዘረኝነት ማስተማር

ልጆችን ስለ ዘረኝነት ማስተማር

 ልጃችሁ ከትንሽነቱ አንስቶ፣ አንዳንድ ሰዎች የቆዳ ቀለምን ወይም ዘርን መሠረት አድርገው በሰዎች ላይ መድልዎ እንደሚፈጽሙ ሊያስተውል ይችላል። ታዲያ ልጃችሁ ሌሎች ያላቸው ጭፍን ጥላቻ ተጽዕኖ እንዳያሳድርበት ልትረዱት የምትችሉት እንዴት ነው? ወይም ደግሞ ልጃችሁ በዘሩ የተነሳ መድልዎ ቢደርስበት ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

በዚህ ርዕስ ውስጥ

 ልጆቻችሁን ስለ ዘር ልዩነት ማስተማር የምትችሉት እንዴት ነው?

 ምን ማለት ትችላላችሁ? በዓለም ዙሪያ ባሉ ሰዎች መካከል ማራኪ የሆነ ልዩነት ይታያል፤ ይህ ልዩነት የአካላዊ ገጽታ ወይም የባሕል ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ሰዎች በዚህ ልዩነት የተነሳ በሌሎች ላይ በደል ይፈጽማሉ።

 ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሁሉም ሰዎች ከአንድ ወንድና ከአንዲት ሴት እንደተገኙ ይናገራል። በሌላ አነጋገር ሁላችንም ዘመዳሞች ነን ማለት ነው።

[አምላክ] የሰውን ወገኖች በሙሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ።”የሐዋርያት ሥራ 17:26

 “ልጆቻችን የተለያየ ዘር ካላቸው ሰዎች ጋር ጊዜ ማሳለፋቸው እያንዳንዱ ሰው ፍቅርና አክብሮት እንደሚገባው ለመገንዘብ እንደረዳቸው አስተውለናል።”—ኬረን

 ልጆቻችሁን ስለ ዘረኝነት ማስተማር የምትችሉት እንዴት ነው?

 ይዋል ይደር እንጂ፣ ልጃችሁ ስለ ጥላቻ ወንጀሎች ወይም የዘር መድልዎ ስለሚንጸባረቅባቸው ሌሎች ድርጊቶች የሚገልጹ ዜናዎችን መስማቱ አይቀርም። ስለዚህ ጉዳይ ልጃችሁን ማስረዳት የምትችሉት እንዴት ነው? የምታስረዱበት መንገድ በልጃችሁ ዕድሜ ላይ የተመካ ነው።

  •   ሕፃናት። ዶክተር አሊሰን ብሪስኮስሚዝ ፓረንትስ በሚለው መጽሔት ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “ሕፃናት የፍትሕ ጉዳይ ያንገበግባቸዋል። ይህም ስለ ፍትሕ መጓደል ለማስተማር የሚያስችል ጥሩ መሠረት ይሆናል።”

“አምላክ [አያዳላም]። ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።”የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35

  •   ልጆች። ከ6 እስከ 12 ዓመት ባለው ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ልጆች የማወቅ ጉጉት አላቸው፤ አንዳንድ ጊዜም ከባድ ጥያቄዎችን ይጠይቃሉ። አቅማችሁ በፈቀደ መጠን ጥያቄዎቻቸውን መልሱላቸው። ልጆቻችሁን በትምህርት ቤት እንዲሁም በቴሌቪዥንና በኢንትርኔት ላይ ስለሚያዩት ነገር አዋሯቸው። እንዲሁም ይህን አጋጣሚ ተጠቅማችሁ የዘር መድልዎ ተገቢ እንዳልሆነ አስተምሯቸው።

“የአስተሳሰብ አንድነት ይኑራችሁ፤ የሌላውን ስሜት የምትረዱ ሁኑ፤ የወንድማማች መዋደድ ይኑራችሁ፤ ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ፤ ትሑታን ሁኑ።”1 ጴጥሮስ 3:8

  •   ወጣቶች። ወጣቶች ይበልጥ ውስብስብ የሆኑ ጉዳዮችን መረዳት ይችላሉ። በመሆኑም በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኘው ልጃችሁ ጋር ስለ ዘር መድልዎ በሚገልጹ ዜናዎች ላይ መወያየት ትችላላችሁ።

‘ጎልማሳ ሰዎች ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታቸውን በማሠራት አሠልጥነዋል።’ዕብራውያን 5:14

 “ከልጆቻችን ጋር ስለ ዘረኝነት እናወራለን፤ ምክንያቱም የሚኖሩት የትም ይሁን የት፣ የሆነ ወቅት ላይ የዘረኝነት ድርጊት ሊፈጸምባቸው ወይም በሌሎች ላይ ሲፈጸም ሊያዩ ይችላሉ። ቤት ውስጥ ስለዚህ ጉዳይ ካልተማሩ የሌሎች አመለካከት ሊጋባባቸው ይችላል። ብዙ ሰዎች ለልጆቻችን የተሳሳቱ መረጃዎችን እውነት አስመስለው ሊያቀርቡ ይችላሉ።”—ታንያ

 ጥሩ ምሳሌ መሆን የምትችሉት እንዴት ነው?

 ልጆች ምሳሌነታችሁን ይመለከታሉ፤ በመሆኑም ስለ ንግግራችሁና ስለ ምግባራችሁ ቆም ብላችሁ ማሰባችሁ አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ፦

  •   ከእናንተ የተለየ ዘር ስላላቸው ሰዎች የሚገልጹ ቀልዶችን ታወራላችሁ? ወይም እነዚህን ሰዎች ታቃልላላችሁ? አሜሪካን አካደሚ ኦቭ ቻይልድ ኤንድ አዶለሰንት ሳይካትሪ እንዲህ ይላል፦ “ልጆቻችሁ ይመለከቷችኋል እንዲሁም ይሰሟችኋል፤ ደግሞም እናንተን መኮረጃቸው አይቀርም።”

  •   ከሌላ የዓለም ክፍል ከመጡ ሰዎች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያስደስታችኋል? የሕፃናት ሐኪም የሆኑት አላና ንዞማ እንዲህ ብለዋል፦ “ልጆቻችሁ . . . ከእነሱ የተለየ አስተዳደግና ባሕል ካላቸው ሰዎች ጋር [ጥሩ] ዝምድና እንዲኖራቸው ከፈለጋችሁ እናንተም ተመሳሳይ ነገር ስታደርጉ ሊያዩአችሁ ይገባል።”

“ሁሉንም ዓይነት ሰው አክብሩ።”1 ጴጥሮስ 2:17

 “ባለፉት ዓመታት ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ ሰዎችን በቤታችን አስተናግደናል። ስለ ምግባቸውና ስለ ሙዚቃቸው ተምረናል፤ ባሕላዊ ልብሳቸውንም ለብሰናል። ከልጆቻችን ጋር ስለ ሰዎች ስናወራ በዘራቸው ላይ ትኩረት አናደርግም። ስለ ራሳችን ባሕል ጉራ ከመንዛትም እንቆጠብ ነበር።”—ካታሪና

 ልጃችሁ የዘር መድልዎ ቢፈጸምበትስ?

 በዓለም ላይ ስለ እኩልነት ብዙ ቢወራም ዘረኝነት አሁንም እንደተስፋፋ ነው። ስለዚህ በተለይም ልጃችሁ ዝቅ ተደርጎ የሚታይ ብሔር አባል ከሆነ መድልዎ ሊፈጸምበት ይችላል። ልጃችሁ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠመው ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

 የተሟላ መረጃ ለማግኘት ሞክሩ። ግለሰቡ በልጃችሁ ላይ በደል ያደረሰበት ሆን ብሎ በክፋት ተነሳስቶ ነው? ወይስ እንዲሁ ሳያመዛዝን በመቅረቱ ነው? (ያዕቆብ 3:2) ግለሰቡን ማነጋገር ያስፈልጋል? ወይስ ሁኔታውን ችላ ብሎ ማለፍ ይቻላል?

 በእርግጥም ሚዛናዊ መሆን በጣም አስፈላጊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ለቁጣ አትቸኩል” የሚል ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምክር ይሰጣል። (መክብብ 7:9) ዘረኝነት በቸልታ ሊታለፍ የሚገባው ችግር አይደለም። ሆኖም ልጃችሁ አንድ ሰው እንደሰደበው ወይም እንደበደለው ስለተሰማው ብቻ የጥላቻ ወንጀል ወይም የዘር መድልዎ ተፈጽሞበታል ማለት አይደለም።

 እርግጥ እያንዳንዱ ሁኔታ የተለያየ ነው። በመሆኑም ምን ዓይነት እርምጃ እንደምትወስዱ ከመወሰናችሁ በፊት የተፈጠረውን ነገር በትክክል አጣሩ።

“እውነታውን ከመስማቱ በፊት መልስ የሚሰጥ ሰው፣ ሞኝነት ይሆንበታል፤ ውርደትም ይከናነባል።”ምሳሌ 18:13

 ጉዳዩን ካጣራችሁ በኋላ እንዲህ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፦

  •   ‘ልጄ ሰዎች ሁሉ መድልዎ እንደሚፈጽሙበት ማሰቡ ወይም በተሰደበ ቁጥር “በዘሬ ምክንያት ነው” የሚል መደምደሚያ ላይ መድረሱ ይጠቅመዋል?’

  •   ‘ልጄ “ሰዎች የሚናገሩትን ነገር ሁሉ ትኩረት ሰጥተህ አትከታተል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ ቢያደርግ ይሻል ይሆን?’—መክብብ 7:21

“ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን።”ፊልጵስዩስ 4:5

 ግለሰቡ በልጃችሁ ላይ በደል የፈጸመበት ሆን ብሎ እንደሆነ ቢሰማችሁስ? ልጃችሁ ለሁኔታዎች የሚሰጠው ምላሽ ሁኔታው እንዲሻሻል ወይም እንዲባባስ ሊያደርግ እንደሚችል እንዲያስተውል እርዱት። አንዳንዶች በሌሎች ላይ የሚያፌዙት፣ የሚሳደቡት ወይም ጥቃት የሚሰነዝሩት ግለሰቡ ተበሳጭቶ የሆነ እርምጃ እንዲወስድ ፈልገው ነው። በዚህ ጊዜ ከሁሉ የተሻለው እርምጃ ጉዳዩን በቸልታ ማለፍ ሊሆን ይችላል።

“እንጨት ከሌለ እሳት ይጠፋል።”ምሳሌ 26:20

 በሌላ በኩል ደግሞ፣ በደህንነቱ ላይ ስጋት የማይፈጥር ከሆነ ልጃችሁ ግለሰቡን ሊያነጋግረው ይችል ይሆናል። ምናልባትም ልጃችሁ በተረጋጋ መንፈስ “የተናገርከው (ወይም ያደረግከው) ነገር ደስ አላለኝም” ሊለው ይችላል።

 ሁኔታውን ሪፖርት ማድረግ ከፈለጋችሁስ? የልጃችሁ ደህንነት አደጋ ላይ ከወደቀ ወይም ሁኔታው በቸልታ መታለፍ እንደሌለበት እንድታስቡ የሚያደርጋችሁ ምክንያት ካለ የትምህርት ቤቱን ኃላፊዎች፣ አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ ፖሊሶችንም ለማነጋገር ነፃነት ይሰማችሁ።