በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

“አሁን፣ ዓለምን መለወጥ እንዳለብኝ አይሰማኝም”

“አሁን፣ ዓለምን መለወጥ እንዳለብኝ አይሰማኝም”
  • የትውልድ ዘመን፦ 1966

  • የትውልድ አገር፦ ፊንላንድ

  • የኋላ ታሪክ፦ የማኅበራዊ ለውጥ አራማጅ

የቀድሞ ሕይወቴ፦

ከልጅነቴ ጀምሮ ተፈጥሮን አደንቅ ነበር። የምንኖረው በማዕከላዊ ፊንላንድ በምትገኘው ዩዊቫስኩዊላ የምትባል ከተማ ሲሆን በከተማዋ ዙሪያ ወደሚገኙት ውብ ጫካዎችና የሚያማምሩ ሐይቆች በቤተሰብ ሆነን ብዙ ጊዜ ለሽርሽር እንሄድ ነበር። እንስሳትንም በጣም እወዳለሁ። በልጅነቴ፣ ያየሁትን ድመትና ውሻ ሁሉ ማቀፍ እፈልግ ነበር! እያደግሁ ስሄድ ግን ሰዎች በእንስሳት ላይ የሚያደርሱት በደል ያበሳጨኝ ጀመር። ከጊዜ በኋላ የእንስሳት መብት ተሟጋች የሆነ ድርጅት አባል በመሆን እንደ እኔው ዓይነት አስተሳሰብ ካላቸው ሰዎች ጋር መሥራት ጀመርኩ።

ድርጅታችን የእንስሳትን መብት ለማስጠበቅ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያደርግ ነበር። ከዚህ ጋር የተያያዙ መረጃዎች እናሰራጫለን፤ እንዲሁም ከእንስሳት ፀጉር የተሠሩ ነገሮችን የሚሸጡ ሱቆችን እና በቤተ ሙከራዎች ውስጥ በእንስሳት ላይ ሙከራ ማድረግን በመቃወም ትዕይንተ ሕዝብና የተቃውሞ ሰልፍ እናዘጋጃለን። ይህም ብቻ ሳይሆን ለእንስሳት ጥበቃ የሚያደርግ ሌላ ድርጅት እስከ ማቋቋም ደርሰናል። ዓላማችንን ለማራመድ በምናደርገው ጥረት ከበድ ያሉ እርምጃዎችን እንወስድ ስለነበር ብዙውን ጊዜ ከባለሥልጣናት ጋር እንጋጫለን። እኔም በተለያዩ ጊዜያት ተይዤ ፍርድ ቤት ቀርቤያለሁ።

በእንስሳት ላይ የሚደርሰው በደል ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ያሉ ሌሎች ችግሮችም ያስጨንቁኝ ነበር። ውሎ አድሮ፣ እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ግሪንፒስ ያሉ በርካታ ድርጅቶች ውስጥ ገባሁ። እነዚህ ድርጅቶች የሚያካሂዷቸውን እንቅስቃሴዎች በሙሉ ኃይሌ እደግፍ ነበር። የድሆችን፣ የተራቡ ሰዎችንና ሌሎች የተቸገሩ ሰዎችን መብት ለማስከበር እጥር ነበር።

ይሁን እንጂ እየዋለ ሲያድር፣ ዓለምን መለወጥ እንደማልችል ተረዳሁ። እነዚያ ድርጅቶች ትናንሽ ችግሮችን በተወሰነ መጠን መቅረፍ ቢችሉም ትላልቆቹ ችግሮች ጭራሽ እየባሱ እንደሚሄዱ ግልጽ ሆነልኝ። ሁኔታው ሲታይ ክፋት ዓለምን በሙሉ ያጥለቀለቀው ያህል ነበር፤ ስለዚህ ጉዳይም የሚገደው ያለ አይመስልም። በመሆኑም ምንም ማድረግ እንደማልችል ተሰማኝ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

ምንም ማድረግ ባለመቻሌ በጣም አዘንኩ፤ በመሆኑም ስለ አምላክና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማሰብ ጀመርኩ። ቀደም ሲል ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ  ቅዱስን አጥንቼ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮችን በደግነታቸውና ለእኔ ባሳዩኝ አሳቢነት ባደንቃቸውም በወቅቱ አኗኗሬን ለመለወጥ ዝግጁ አልነበርኩም። በዚህ ጊዜ ግን ነገሮች ተለውጠው ነበር።

መጽሐፍ ቅዱሴን አንስቼ ማንበብ ጀመርኩ። ያነበብኩት ነገር በጣም አጽናናኝ። እንስሳትን በደግነት እንድንይዝ የሚያስተምሩ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መኖራቸውን አስተዋልኩ። ለአብነት ያህል፣ ምሳሌ 12:10 “ደግ ሰው ለቤቱ እንስሳት ክብካቤ ያደርጋል” በማለት ይናገራል። (የ1980 ትርጉም) በተጨማሪም በዓለም ላይ ያሉትን ችግሮች ያመጣው አምላክ እንዳልሆነ ተገነዘብኩ። ችግሮቻችን እየተባባሱ የሄዱት አብዛኞቹ ሰዎች የእሱን አመራር ስለማይከተሉ እንደሆነ ተረዳሁ። ስለ ይሖዋ ፍቅርና ትዕግሥት ሳውቅ ልቤ ተነካ።—መዝሙር 103:8-14

በዚያው ጊዜ አካባቢ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተሰኘው መጽሐፍ እንዲላክልኝ መጠየቂያ ቅጽ አገኘሁና ሞልቼ ላክሁት። ብዙም ሳይቆይ ባልና ሚስት የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤቴ መጡና መጽሐፍ ቅዱስን አብሬያቸው እንዳጠና ጋበዙኝ፤ እኔም ግብዣውን ተቀበልኩ። በተጨማሪም በመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉት ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርኩ። በዚህም የተነሳ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በልቤ ውስጥ ሥር መስደድ ጀመረ።

ለመጽሐፍ ቅዱስ ምስጋና ይግባውና በሕይወቴ ውስጥ ብዙ ለውጦች ማድረግ ቻልኩ። ማጨስና ከልክ በላይ መጠጣት አቆምኩ። ንጽሕናዬን መጠበቅ ጀመርኩ፤ አነጋገሬንም ቀየርኩ። ከዚህም ሌላ ለባለሥልጣናት የነበረኝን አመለካከት አስተካከልኩ። (ሮም 13:1) ቀደም ሲል የነበረኝን ልቅ የሆነ አኗኗርም ተውኩ።

ከሁሉ በላይ የከበደኝ ነገር ለሌሎች መብት ስለሚታገሉ ድርጅቶች ያለኝን አመለካከት ማስተካከል ነበር። ይህን ለውጥ ያደረግሁት በአንድ ጀምበር አይደለም። መጀመሪያ ላይ፣ ከእነዚህ ድርጅቶች ለቅቄ መውጣት እነሱን እንደ መክዳት ሆኖ ተሰምቶኝ ነበር። ይሁን እንጂ ለዓለማችን ችግሮች ብቸኛው እውነተኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት መሆኑን ተገነዘብኩ። በመሆኑም ሙሉ ኃይሌን ይህን መንግሥት ለመደገፍና ሌሎችን ስለዚህ መንግሥት በማስተማሩ ሥራ ለማዋል ወሰንኩ።—ማቴዎስ 6:33

ያገኘሁት ጥቅም፦

የለውጥ አራማጅ በነበርኩበት ወቅት ሰዎችን ሁሉ ወይ ጥሩ አሊያም መጥፎ ብዬ በሁለት ጎራዎች እፈርጃቸው ነበር፤ እንዲሁም መጥፎ እንደሆኑ በማስባቸው ሰዎች ላይ እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ አልልም። ይሁን እንጂ ማንንም ሰው ይህን ያህል አጥብቄ መጥላት እንደሌለብኝ ከመጽሐፍ ቅዱስ ስለተማርኩ አመስጋኝ ነኝ። ከዚህ ይልቅ ለሁሉም ሰው ክርስቲያናዊውን ፍቅር ለማሳየት ጥረት አደርጋለሁ። (ማቴዎስ 5:44) ይህን ፍቅር ከማሳይባቸው መንገዶች አንዱ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሌሎች ማካፈል ነው። ይህ መልካም ሥራ ሰዎች ሰላም፣ ደስታና እውነተኛ ተስፋ እንዲኖራቸው የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ስመለከት ደስ ይለኛል።

የሚያስጨንቁኝን ነገሮች ለይሖዋ በመተው የአእምሮ ሰላም አግኝቻለሁ። ይሖዋ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን እንስሳትም ሆኑ ሰዎች ለዘላለም በደል እንዲደርስባቸው ወይም ውቧ ምድራችን እንድትጠፋ እንደማይፈቅድ እርግጠኛ ነኝ። እንዲያውም የደረሰውን ጉዳት ሁሉ በመንግሥቱ አማካኝነት በቅርቡ ያስተካክላል። (ኢሳይያስ 11:1-9) እነዚህን እውነቶች በማወቅ ብቻ ሳልወሰን ሌሎችም እንዲያምኑባቸው መርዳት መቻሌ ትልቅ ደስታ ይሰጠኛል። አሁን፣ ዓለምን መለወጥ እንዳለብኝ አይሰማኝም።