በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጉባኤው ውስጥ ከሚገኙ ወጣቶች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያስደስተኛል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

ከምንም ነገር በላይ የሚያስደስተኝ ቤዝቦል መጫወት ነበር!

ከምንም ነገር በላይ የሚያስደስተኝ ቤዝቦል መጫወት ነበር!
  • የትውልድ ዘመን: 1928

  • የትውልድ አገር: ኮስታ ሪካ

  • የኋላ ታሪክ: በስፖርትና በቁማር ተጠምደው የነበሩ

የቀድሞ ሕይወቴ

ያደግኩት በኮስታ ሪካ ምሥራቃዊ ጠረፍ ላይ በምትገኝ ፖርቶ ሊሞን የተባለች የወደብ ከተማ አካባቢ ነው። ወላጆቼ ስምንት ልጆች የነበሯቸው ሲሆን እኔ ሰባተኛ ልጅ ነኝ። የስምንት ዓመት ልጅ ሳለሁ አባቴ ሞተ። ከዚያ በኋላ እናቴ ያሳደገችን ብቻዋን ነው።

ቤዝቦል የሕይወቴ ክፍል ነበር። በልጅነቴ በዚህ ስፖርታዊ ውድድር መካፈል እወድ ነበር። በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ ሳለሁ በአማተር ሊግ የሚወዳደር ቡድን አባል ሆንኩ። በ20ዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለሁ ለአማተር ሊጉ እጫወት በነበረበት ወቅት በኒካራጓ ለሚገኝ ፕሮፌሽናል ቡድን እንድጫወት ተመለመልኩ። ሆኖም በወቅቱ እናቴ ጥሩ ጤንነት ስላልነበራትና የምንከባከባት እኔ ስለነበርኩ ወደ ኒካራጓ መሄድ አልፈለግኩም። በመሆኑም ግብዣውን ሳልቀበል ቀረሁ። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ከአማተር ሊግ በተመረጡ ተጫዋቾች ለተዋቀረው የኮስታ ሪካ ብሔራዊ ቡድን እንድጫወት ተመለመልኩ። በዚህ ወቅት ግን ግብዣውን ተቀበልኩ። ከ1949 እስከ 1952 ድረስ በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ ተጫውቻለሁ፤ በኩባ፣ በሜክሲኮና በኒካራጓ በተደረጉ ጨዋታዎች ላይ ተካፍያለሁ። በቡድኑ ውስጥ ቤዝማን ሆኜ እጫወት ነበር፤ በተከታታይ 17 ጨዋታዎችን አንድም ስህተት ሳልሠራ ተጫውቻለሁ። ተመልካቹ ስሜን እየጠራ ሲጮኽ መስማት በጣም ያስደስተኝ ነበር!

የሚያሳዝነው ነገር፣ ሕይወቴ ሥነ ምግባር የጎደለው ነበር። አንዲት የሴት ጓደኛ የነበረችኝ ቢሆንም ከተለያዩ ሴቶች ጋር እወጣለሁ። በተጨማሪም በጣም እጠጣለሁ። እንዲያውም አንድ ቀን በጣም ከመስከሬ የተነሳ በቀጣዩ ቀን ከእንቅልፌ ስነቃ እንዴት ወደ ቤት እንደተመለስኩ ራሱ ማስታወስ ተስኖኝ ነበር! ከዚህም ሌላ ቁማር እጫወት ነበር።

በዚህ ወቅት እናቴ የይሖዋ ምሥክር ሆነች። ስለ እምነቷ ልትነግረኝ ሞክራ የነበረ ቢሆንም መጀመሪያ ላይ አልተሳካላትም፤ ምክንያቱም በስፖርቱ በጣም ተጠምጄ ነበር። በምግብ ሰዓትም እንኳ ሥልጠና ላይ ከሆንኩ ረሃብ አይሰማኝም ነበር! አእምሮዬ የሚያተኩረው በጨዋታው ላይ ብቻ ነበር። ከምንም ነገር በላይ የሚያስደስተኝ ቤዝቦል መጫወት ነበር!

ሆኖም በ29 ዓመቴ ጨዋታ ላይ እያለሁ ኳስ ለመያዝ ስሞክር ከባድ ጉዳት ደረሰብኝ። ካገገምኩ በኋላ በቡድን ታቅፌ መጫወት አቆምኩ። ይሁንና በቤቴ አቅራቢያ የሚገኝን አንድ የአማተር ሊግ ቡድን ተጫዋቾች በማሠልጠን ከቤዝቦል ጋር የተያያዘ ሥራ መሥራቴን ቀጠልኩ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

በ1957 የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ እንድገኝ የቀረበልኝን ግብዣ ተቀበልኩ፤ ስብሰባው የሚካሄደው ከዚያ ቀደም ቤዝቦል በተጫወትኩበት ስታዲየም ውስጥ ነበር። ገብቼ እንደተቀመጥኩ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያሳዩት አክብሮት የተሞላበት ምግባርና በቤዝቦል ጨዋታዎች ላይ ይገኙ የነበሩት ተመልካቾች ያሳዩት በነበረው ሥርዓት የጎደለው ምግባር መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ አስተዋልኩ። በስብሰባው ላይ የተመለከትኩት ነገር ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እንዳጠናና በጉባኤ ስብሰባዎቻቸው ላይ እንድገኝ አነሳሳኝ።

የተማርኳቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች በጣም አስደነቁኝ። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ በመጨረሻዎቹ ቀናት ደቀ መዛሙርቱ የአምላክን መንግሥት ምሥራች በዓለም ዙሪያ እንደሚያውጁ ተንብዮ ነበር። (ማቴዎስ 24:14) በተጨማሪም እውነተኛ ክርስቲያኖች አገልግሎታቸውን የሚያከናውኑት የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት ብለው እንዳልሆነ ተማርኩ። ኢየሱስ “በነፃ እንደተቀበላችሁ በነፃ ስጡ” በማለት ተናግሯል።—ማቴዎስ 10:8

መጽሐፍ ቅዱስን አጠና በነበረበት ወቅት መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ነገር የይሖዋ ምሥክሮች ከሚያደርጉት ነገር ጋር አወዳድር ነበር። የአምላክን መንግሥት ምሥራች በዓለም ዙሪያ ለማስፋፋት የሚያደርጉት ከፍተኛ ጥረት አስደነቀኝ። ኢየሱስ ክርስቲያኖች እንዲያሳዩ ያዘዘውን የልግስና መንፈስ እንደሚያሳዩ አስተዋልኩ። በመሆኑም፣ ኢየሱስ በማርቆስ 10:21 ላይ “መጥተህ ተከታዬ ሁን” በማለት ያቀረበውን ግብዣ ሳነብ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ተነሳሳሁ።

መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ነገር ተግባራዊ ለማድረግ ግን ጊዜ ፈጅቶብኛል። ለምሳሌ ያህል፣ ለበርካታ ዓመታት ያህል በየሳምንቱ በብሔራዊ ሎተሪ “ዕድለኛ” ቁጥሬን በመጠቀም ቁማር እጫወት ነበር። ሆኖም አምላክ “መልካም ዕድል” የተባለውን አምላክ የሚያመልኩትን ሰዎች እንዳወገዘና ስግብግብ ሰዎችን እንደሚጠላ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማርኩ። (ኢሳይያስ 65:11፤ ቆላስይስ 3:5) በመሆኑም ቁማር መጫወት ለማቆም ወሰንኩ። ይህን ውሳኔ ካደረግኩ በኋላ በነበረው የመጀመሪያ እሁድ “ዕድለኛ” ቁጥሬ አሸነፈ! ሰዎች በዚያ ሳምንት ባለመጫወቴ አሾፉብኝ፤ እንዲሁም ድጋሚ መጫወት እንድጀምር በጣም ገፋፉኝ፤ እኔ ግን እንዲህ ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆንኩም። ከዚያ በኋላ ቁማር ተጫውቼ አላውቅም።

የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ በተጠመቅኩበት ቀን “አዲሱን ስብዕና” ለመልበስ ካደረግኩት ውሳኔ ጋር የሚጋጭ ግብዣ ቀረበልኝ። (ኤፌሶን 4:24) በዚያ ቀን ምሽት ወዳረፍኩበት ሆቴል ስመለስ የክፍሌ በር ላይ የቀድሞ የሴት ጓደኛዬ ቆማ ስትጠብቀኝ አገኘኋት። “ሳሚ፣ አብረን እንዝናና!” በማለት ገፋፋችኝ። እኔም ወዲያውኑ “አይሆንም!” አልኳት። አሁን የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች እንደምከተል ነገርኳት። (1 ቆሮንቶስ 6:18) በድንጋጤ “ምን አልክ?” አለችኝ። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር ብልግናን በተመለከተ የሚናገረውን ነገር አጣጥላ ተናገረችና ግንኙነታችንን እንድንቀጥል ወተወተችኝ። እኔ ግን ትቻት ወደ ክፍሌ ገባሁና በሩን ቆለፍኩት። በ1958 የይሖዋ ምሥክር ከሆንኩበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ታማኝ ሆኜ መቀጠል በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ።

ያገኘሁት ጥቅም

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን በመከተሌ ያገኘሁትን ጥቅም ልዘርዝር ብል መጽሐፍ የሚወጣው ይመስለኛል! በርካታ እውነተኛ ጓደኞች፣ ትርጉም ያለው ሕይወትና እውነተኛ ደስታ አግኝቻለሁ፤ እነዚህ ካገኘኋቸው ጥቅሞች ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው።

አሁንም ቤዝቦል እወዳለሁ፤ ሆኖም በሕይወቴ ውስጥ ቅድሚያ የምሰጠው ነገር ተለውጧል። ቤዝቦል ስጫወት በነበረበት ጊዜ ዝናና ሀብት አግኝቻለሁ፤ ሆኖም እነዚህ ነገሮች ለረጅም ጊዜ አልዘለቁም። ከይሖዋ ጋር ያለኝ ዝምድናና ያለሁበት የወንድማማች ማኅበር ግን ለዘላለም ይዘልቃሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለምም ሆነ ምኞቱ ያልፋሉ፤ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” በማለት ይናገራል። (1 ዮሐንስ 2:17) አሁን ከምንም ነገር በላይ የምወደው ይሖዋ አምላክንና ሕዝቦቹን ነው!