በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከባለቤቴ ከታቢታ ጋር በስብከቱ ሥራ ስንካፈል

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

አምላክ እንደሌለ ይሰማኝ ነበር

አምላክ እንደሌለ ይሰማኝ ነበር
  • የትውልድ ዘመን፦ 1974

  • የትውልድ አገር፦ የጀርመን ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ

  • የኋላ ታሪክ፦ በአምላክ መኖር የማያምን

የቀድሞ ሕይወቴ

የተወለድኩት የጀርመን ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ትባል በነበረችው አገር ውስጥ ሳክሰኒ በተባለች መንደር ነው። ቤታችን ፍቅር የሞላበትና ደስ የሚል መንፈስ የሰፈነበት ሲሆን ወላጆቼም ጥሩ የሥነ ምግባር እሴቶችን አስተምረውኛል። የጀርመን ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ የኮሚኒዝምን ርዕዮተ ዓለም ትከተል ስለነበረ አብዛኞቹ የሳክሰኒ ነዋሪዎች ለሃይማኖት ግድ አልነበራቸውም። እኔም አምላክ እንደሌለ ይሰማኝ ነበር። አሥራ ስምንት ዓመት እስኪሆነኝ ድረስ በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳደሩት ጽንሰ ሐሳቦች አምላክ የለሽነትና ኮሚኒዝም ነበሩ።

ኮሚኒዝምን የወደድኩት ለምንድን ነው? ሰዎች ሁሉ እኩል ናቸው የሚለውን ሐሳብ ስለወደድኩት ነው። በተጨማሪም ማንኛውም ሀብት እኩል መከፋፈል እንዳለበት አምን ነበር፤ እንዲህ ዓይነት የሀብት ክፍፍል መኖሩ በአንድ በኩል እጅግ የናጠጡ ሀብታሞች በሌላ በኩል ደግሞ በከፋ ድህነት የሚማቅቁ ሰዎች እንዳይኖሩ ያደርጋል። ስለዚህ በወጣት ኮሚኒስት ድርጅት ውስጥ በመሥራት ብዙ ጊዜ አሳልፍ ነበር። በ14 ዓመቴ፣ የተጣሉ ወረቀቶችን እንደገና ጥቅም ላይ በማዋል አካባቢን ለመንከባከብ በተቋቋመ ፕሮጀክት ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ አድርጌያለሁ። የምኖርባት የአወ ከተማ ባለሥልጣናት ላደረግኩት ጥረት አድናቆታቸውን ለመግለጽ ሽልማት ሰጥተውኛል። በወቅቱ ገና ወጣት የነበርኩ ቢሆንም የጀርመን ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ አንዳንድ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን መተዋወቅ ችዬ ነበር። በትክክለኛው አቅጣጫ እየተጓዝኩ እንደሆነና መጪ ሕይወቴም ብሩህ እንደሆነ ተሰምቶኝ ነበር።

ይሁንና ሁሉ ነገር በድንገት ተለዋወጠ። በ1989 የበርሊን ግንብ ሲወድቅ የምሥራቅ አውሮፓው የኮሚኒስት ጎራም ፈረሰ። ያጋጠመኝ አስደንጋጭ ነገር ይህ ብቻ አልነበረም። በጀርመን ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ውስጥ የፍትሕ መዛባት ተስፋፍቶ እንደነበረ ብዙም ሳይቆይ ተገነዘብኩ። ለምሳሌ ያህል፣ ኮሚኒዝምን የማይደግፉ ሰዎች እንደ ሁለተኛ ደረጃ ዜጎች ይቆጠሩ ነበር። ‘ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ኮሚኒስቶች፣ ሰዎች ሁሉ እኩል እንደሆኑ እናምን የለም እንዴ? ኮሚኒዝም ተጨባጭ ያልሆነ ሐሳብ ብቻ ነበር ማለት ነው?’ የሚሉ ጥያቄዎች ተፈጠሩብኝ። ይህ ጉዳይ በጣም አስጨነቀኝ።

በመሆኑም በሕይወቴ ውስጥ ቅድሚያ የምሰጠውን ነገር በመቀየር በሙዚቃና በሥዕል ላይ አተኮርኩ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን የተማርኩት በሙዚቃ ትምህርት ቤት ስለሆነና ዩኒቨርሲቲም በተመሳሳይ መስክ መቀጠል እችል ስለነበር በሙዚቀኝነትና በሠዓሊነት ሙያ ለመሠማራት አሰብኩ። በተጨማሪም በልጅነቴ በተማርኳቸው የሥነ ምግባር እሴቶች መመራት አቆምኩ። በወቅቱ ትልቅ ቦታ የምሰጠው ነገር መዝናናት ሲሆን በአንድ ጊዜ ከተለያዩ ሴቶች ጋር የፍቅር ጓደኝነት መሥርቼ ነበር። ይሁን እንጂ ሙዚቃ፣ ሥዕልና ልቅ አኗኗር ጭንቀቴን ሊያቀሉልኝ አልቻሉም። የምሠራቸው ሥዕሎችም እንኳ ውስጤ ፍርሃት እንዳለ የሚያንጸባርቁ ነበሩ። ‘ወደፊት ምን ይመጣ ይሆን? የሕይወት ዓላማስ ምንድን ነው?’ እያልኩ እጨነቅ ነበር።

በመጨረሻ ለጥያቄዎቼ መልስ አገኘሁ፤ ሆኖም ያገኘሁት መልስ በጣም አስገረመኝ። በሙዚቃ ትምህርት ቤቱ ውስጥ አንድ ምሽት ላይ ከአንዳንድ ወጣቶች ጋር ቁጭ ብለን ስለ ወደፊቱ ጊዜ እንወያይ ነበር። ማንዲ * የተባለችው ተማሪ የይሖዋ ምሥክር ነበረች። ማንዲ በዚያ ምሽት ጥሩ ምክር ሰጠችኝ። “አንድሪአስ፣ ስለ ሕይወትና ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለተፈጠሩብህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ከፈለግክ መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ መርምር” አለችኝ።

ይህን ስትለኝ በአንድ በኩል ጥርጣሬ በሌላ በኩል ደግሞ የማወቅ ጉጉት አደረብኝ፤ ይሁን እንጂ የማወቅ ጉጉቴ አሸነፈ። ማንዲ ዳንኤል ምዕራፍ 2⁠ን ያሳየችኝ ሲሆን ያነበብኩት ነገር አስደነቀኝ። ይህ ትንቢት በተከታታይ ስለሚነሱ ኃያላን መንግሥታት የሚገልጽ ሲሆን መንግሥታቱ እስከ ዘመናችን የሚደርስ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖራቸዋል። ማንዲ የወደፊት ሕይወታችንን የሚመለከቱ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችንም አሳየችኝ። በመጨረሻ ለጥያቄዎቼ መልስ ማግኘት ቻልኩ! ‘ይሁን እንጂ እነዚያን ትንቢቶች የጻፋቸው ማን ነው? ደግሞስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ እንደዚህ በትክክል መተንበይ የሚችለው ማን ነው? አምላክ ይኖር ይሆን እንዴ?’ ብዬ አሰብኩ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

ማንዲ፣ ሆርስትና አንጂሊካ ከሚባሉ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያገናኘችኝ ሲሆን እነዚህ ባልና ሚስት የአምላክን ቃል ይበልጥ እንዳውቅ ረዱኝ። ይሖዋ የሚለውን የአምላክ የግል ስም አዘውትረው የሚጠቀሙበትና ለሰዎችም የሚያሳውቁት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ እንደሆኑ ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደብኝም። (መዝሙር 83:18፤ ማቴዎስ 6:9) ይሖዋ አምላክ፣ ለሰው ዘሮች ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንደሰጣቸው ተማርኩ። መዝሙር 37:9 “ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉ ግን ምድርን ይወርሳሉ” በማለት ይናገራል። ይህ ተስፋ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጹት የአምላክ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው ለመኖር ጥረት ለሚያደርጉ ሁሉ የተዘረጋ መሆኑ አስደሰተኝ።

ይሁን እንጂ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ስል አኗኗሬን መለወጥ ቀላል አልነበረም። በሙዚቀኛነትና በሥዕል መስክ ስኬታማ መሆኔ ኩራት እንዲያድርብኝ አድርጎ ነበር፤ በመሆኑም በመጀመሪያ ትሕትና መማር አስፈልጎኛል። ከዚህም በላይ በሥነ ምግባር ረገድ ልቅ የሆነ አኗኗሬን መተው ለእኔ ቀላል አልነበረም። ይሖዋ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ተግባራዊ ለማድረግ የሚችሉትን ያህል ለሚጥሩ ሰዎች ትዕግሥትና ምሕረት የሚያሳይ እንዲሁም ሁኔታቸውን የሚረዳላቸው በመሆኑ በጣም አመስጋኝ ነኝ!

አሥራ ስምንት ዓመት እስኪሆነኝ ድረስ በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳደሩት ኮሚኒዝምና አምላክ የለም የሚሉት ጽንሰ ሐሳቦች ናቸው፤ ከዚያ ወዲህ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን እየለወጠው ነው። የተማርኩት ነገር ስለ ወደፊቱ ጊዜ የነበረኝን ጭንቀት ያጠፋልኝ ሲሆን ሕይወቴም ዓላማ እንዲኖረው አድርጓል። በ1993 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ፤ በ2000 ደግሞ ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክር የሆነችውን ታቢታን አገባሁ። እኔና ታቢታ፣ ሌሎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያውቁ በመርዳት በተቻለን መጠን ብዙ ጊዜ እናሳልፋለን። የምናገኛቸው ብዙዎቹ ሰዎች ልክ እንደ እኔ ኮሚኒዝምን የሚደግፉና አምላክ የለሽ የነበሩ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ይሖዋን ማወቅ እንዲችሉ መርዳት በመቻሌ ጥልቅ እርካታ ይሰማኛል።

ያገኘሁት ጥቅም

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ስጀምር ወላጆቼ ደንግጠው ነበር። ይሁን እንጂ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናቴ በሕይወቴ ላይ ያመጣውን በጎ ውጤት መመልከት ቻሉ። አሁን መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነብቡ ከመሆኑም ሌላ በይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ፤ ይህም በጣም አስደስቶኛል።

እኔና ታቢታ መጽሐፍ ቅዱስ ለባለትዳሮች የሚሰጠውን ምክር በጥብቅ ለመከተል ስለምንጥር ጥሩ ትዳር አለን። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ለትዳር ጓደኛ ታማኝ ስለመሆን የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን ትዳራችን ጠንካራ እንዲሆን ረድቶናል።—ዕብራውያን 13:4

አሁን ሕይወት አያስፈራኝም እንዲሁም ስለ ወደፊቱ ጊዜ አልጨነቅም። እውነተኛ ሰላምና አንድነት ያለው ዓለም አቀፍ ቤተሰብ አባል እንደሆንኩ ይሰማኛል። በዚህ ቤተሰብ ውስጥ ማናችንም አንዱን ከአንዱ አናበላልጥም። ይህም፣ መሆን እንዳለበት የማምነውና ስፈልገው የነበረ ነገር ነው።

^ አን.12 ስሟ ተቀይሯል።