በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

ብዙ ጊዜ ብሸነፍም በመጨረሻ ተሳካልኝ

ብዙ ጊዜ ብሸነፍም በመጨረሻ ተሳካልኝ
  • የትውልድ ዘመን፦ 1953

  • የትውልድ አገር፦ አውስትራሊያ

  • የኋላ ታሪክ፦ የፖርኖግራፊ ሱሰኛ የነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ፦

በ1949 አባቴ ከጀርመን ወደ አውስትራሊያ ሄዶ በዚያ መኖር ጀመረ። ወደ አውስትራሊያ የሄደው በማዕድን ማውጫና ኃይል ማመንጫ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ሥራ ለመፈለግ ሲሆን ኑሮውን በገጠራማዋ ቪክቶሪያ አደረገ። በዚያም ከእናቴ ጋር ትዳር መሠረተ፤ በ1953 ደግሞ እኔ ተወለድኩ።

ከጥቂት ዓመታት በኋላ እናቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስለጀመረች ከልጅነት ትዝታዎቼ መካከል የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ይገኙበታል። አባቴ ግን ሃይማኖቶችን ይጠላ ነበር። ዓመፀኛና ጉልበተኛ ስለነበር እናቴ በጣም ትፈራዋለች። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን በድብቅ ማጥናቷን ቀጠለች፤ እናቴ ለምትማራቸው ነገሮች ፍቅር ነበራት። አባቴ ቤት በማይኖርበት ጊዜ የተማረችውን ነገር ለእኔና ለእህቴ ታካፍለናለች። ወደፊት ስለሚመጣው ምድራዊ ገነት እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ከጠበቅን ደስተኛ እንደምንሆን ትነግረን ነበር።—መዝሙር 37:10, 29፤ ኢሳይያስ 48:17

በአባቴ ዓመፀኝነት የተነሳ በ18 ዓመቴ ከቤት ለመውጣት ተገደድኩ። እናቴ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያስተማረችኝን ነገር ባምንበትም ምን ያህል ዋጋ እንዳለው አልተረዳሁም ነበር። በመሆኑም የተማርኩትን ነገር ተግባራዊ አላደረግኩም። ከጊዜ በኋላ በድንጋይ ከሰል ማውጫዎች ውስጥ የኤሌክትሪክ ሠራተኛ ሆኜ ተቀጠርኩ። ሃያ ዓመት ሲሆነኝ ትዳር መሠረትኩ። ከተጋባን ከሦስት ዓመት በኋላ የመጀመሪያ ልጃችን ተወለደች፤ በዚህ ጊዜ በሕይወቴ ውስጥ ለምን ነገር ትልቅ ቦታ መስጠት እንዳለብኝ መለስ ብዬ አሰብኩ። መጽሐፍ ቅዱስ ቤተሰባችንን ሊጠቅም እንደሚችል ስለማውቅ ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ። ባለቤቴ ግን የይሖዋ ምሥክሮችን በጣም ትቃወም ነበር። አንድ ቀን የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ ከተገኘሁ በኋላ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴን እንዳቆም አለዚያ ደግሞ ቤቱን ለቅቄ እንድወጣ ነገረችኝ። ምንም ምርጫ እንደሌለኝ ስለተሰማኝ ለጥያቄዋ በመሸነፍ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያለኝን ግንኙነት አቋረጥኩ። ይሁን እንጂ ትክክል እንደሆነ የማውቀውን ነገር ሳላደርግ በመቅረቴ ውሎ አድሮ ተቆጭቼበታለሁ።

አንድ ቀን የሥራ ባልደረቦቼ ፖርኖግራፊ (የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች) እንድመለከት ጋበዙኝ። ያየሁት ነገር በአንድ በኩል ትኩረት የሚስብ በሌላው በኩል ደግሞ የሚያቅለሸልሽ ነበር፤ በመሆኑም በጥፋተኝነት ስሜት እንድዋጥ አደረገኝ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተማርኩትን ነገር ሳስታውስ አምላክ እኔን መቅጣቱ እንደማይቀር አምን ነበር። ይሁን እንጂ የብልግና ምስሎችን ማየቴን ስቀጥል ለፖርኖግራፊ የነበረኝ አመለካከት ተለወጠ። ከጊዜ በኋላ ሱሰኛ ሆንኩ።

በቀጣዮቹ 20 ዓመታት ቀስ በቀስ እናቴ ካስተማረችኝ ትምህርት እየራቅኩ ሄድኩ። ወደ አእምሮዬ የማስገባው ነገር በምግባሬም ላይ መታየት ጀመረ። ንግግሬ ጸያፍ የነበረ ሲሆን የብልግና ቀልዶችን እቀልድ ነበር። ለፆታ ግንኙነት የተዛባ አመለካከት አዳበርኩ። በወቅቱ የምኖረው ከባለቤቴ ጋር ቢሆንም ከሌሎች ሴቶች ጋር የፆታ ብልግና እፈጽም ነበር። አንድ ቀን መልኬን በመስታወት ውስጥ ስመለከት ራሴን በጣም ጠላሁት። ለራሴ የነበረኝ አክብሮት ሙሉ በሙሉ ጠፍቶ ራሴን እጸየፍ ጀመር።

ትዳሬ ፈረሰ፤ ሕይወቴም ተመሰቃቀለ። በዚህ ጊዜ የልቤን አፍስሼ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። ከሁለት አሥርተ ዓመታት በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴን ቀጠልኩ። በዚያ ወቅት አባቴ በሕይወት አልነበረም፤ እናቴ ደግሞ ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ሆና ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

በእኔ አኗኗርና ላቅ ባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች መካከል ሰፊ ክፍተት ተፈጥሮ ነበር። በዚህ ጊዜ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጸውን የአእምሮ ሰላም ለማግኘት ቆርጬ ነበር። ንግግሬን ንጹሕ ለማድረግና ግልፍተኝነቴን ለመተው ወሰንኩ። በተጨማሪም የብልግና ሕይወቴን እርግፍ አድርጌ ለመተው እንዲሁም ቁማር መጫወቴን፣ ከልክ በላይ መጠጣቴንና ከአሠሪዬ መስረቄን ለማቆም ቆርጬ ተነሳሁ።

የሥራ ባልደረቦቼ እንዲህ ያለ ትልቅ ለውጥ ማድረግ የፈለግኩት ለምን እንደሆነ ሊገባቸው አልቻለም። ለሦስት ዓመታት ያህል ወደ ቀድሞ ምግባሬ እንድመለስ ለማድረግ ሆን ብለው ይፈትኑኝ ነበር። በቁጣ ከገነፈልኩ፣ መጥፎ ቃል ከተናገርኩ ወይም በትንሹም ቢሆን የቀድሞው ማንነቴ ብቅ ካለ “የቀድሞው ጆ ተመለሰ” በማለት በድል አድራጊነት ስሜት ይጮኹ ነበር። እንዲህ ሲሉኝ ውስጤ በጣም ይጎዳ ነበር! እንዲሁም ዋጋ ቢስ እንደሆንኩ ይሰማኛል።

የሥራ ባልደረቦቼ ከኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ወይም ከወረቀት ላይ ፖርኖግራፊ መመልከታቸው በጣም የተለመደ ነበር። በተደጋጋሚ በኮምፒውተሮቻቸው አማካኝነት የብልግና ምስሎችን ይላላካሉ፤ እኔም ብሆን ቀደም ሲል እንዲህ አደርግ ነበር። ይሄን ሱስ ለማሸነፍ እየታገልኩ የነበረ ቢሆንም እነሱ ግን እኔን ለማደናቀፍ ቆርጠው የተነሱ ይመስል ነበር። ድጋፍና ማበረታቻ ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስጠናኝን ሰው አማከርኩት። እሱም የልቤን አውጥቼ ስነግረው በትዕግሥት አዳመጠኝ። እኔ ላለሁበት ሁኔታ የሚሠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ተጠቅሞ ያለብኝን ሱስ ማሸነፍ የምችለው እንዴት እንደሆነ አሳየኝ፤ እንዲሁም የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት አዘውትሬ እንድጸልይ አበረታታኝ።—መዝሙር 119:37

አንድ ቀን የሥራ ባልደረቦቼን ሰብስቤ አናገርኳቸው። ከዚያም ከአልኮል ሱሰኝነት ጋር እየታገሉ እንደሆነ ለተናገሩ ሁለት የሥራ ባልደረቦቻችን ቢራ እንዲሰጧቸው ነገርኳቸው። በዚህ ጊዜ ሁሉም “ምን ነካህ! እነሱ ለራሳቸው ከሱስ ለመላቀቅ እየታገሉ ነው!” በማለት በተቃውሞ ጮኹብኝ። “አዎ፣ የእኔም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው” ብዬ መለስኩላቸው። ከዚያ ቀን ጀምሮ፣ ይፈታተኑኝ የነበሩት የሥራ ባልደረቦቼ ከፖርኖግራፊ ሱስ ለመላቀቅ እየታገልኩ እንደሆነ ተረዱልኝ፤ በመሆኑም ወደ ቀድሞ አኗኗሬ እንድመለስ ግፊት ማድረጋቸውን አቆሙ።

ከጊዜ በኋላ በይሖዋ እርዳታ የፖርኖግራፊ ሱሴን አሸነፍኩ። በ1999 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ፤ ንጹሕና በደስታ የተሞላ ሕይወት የመምራት ሌላ አጋጣሚ በማግኘቴ በጣም አመስጋኝ ነኝ።

ለረዥም ጊዜ እወዳቸው የነበሩትን ነገሮች ይሖዋ የሚጠላው ለምን እንደሆነ አሁን ገብቶኛል። አፍቃሪ አባት እንደመሆኑ መጠን ፖርኖግራፊ ከሚያስከትለው ጉዳት ሊጠብቀኝ ይፈልጋል። በምሳሌ 3:5, 6 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ምንኛ እውነት ነው! ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “በሙሉ ልብህ በይሖዋ ታመን፤ ደግሞም በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመካ። በመንገድህ ሁሉ እሱን ግምት ውስጥ አስገባ፤ እሱም ጎዳናህን ቀና ያደርገዋል።” የመጽሐፍ ቅዱስ መስፈርቶች ጥበቃ ከማስገኘት ባለፈ ለስኬት ዋስትና ናቸው።—መዝሙር 1:1-3

ያገኘሁት ጥቅም፦

ቀደም ሲል ራሴን እጸየፈው ነበር፤ አሁን ግን ለራሴ አክብሮት ያለኝ ከመሆኑም በላይ ውስጣዊ ሰላም አግኝቻለሁ። በሥነ ምግባር ንጹሕ የሆነ ሕይወት እየመራሁ ሲሆን ይሖዋ ይቅር እንዳለኝና እየደገፈኝ እንደሆነ ይሰማኛል። በ2000 ካሮሊን የምትባል እንደ እኔው ይሖዋን የምትወድ አንዲት ውብ ክርስቲያን እህት አገባሁ። ቤታችን ሰላም የሰፈነበት ቦታ ነው። በመላው ዓለም በሚገኘው ንጹሕና አፍቃሪ ክርስቲያናዊ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ የታቀፍን መሆናችን በእርግጥም መታደል እንደሆነ ይሰማናል።