በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በወረርሽኙ ወቅት መስበካቸውን ቀጥለዋል

በወረርሽኙ ወቅት መስበካቸውን ቀጥለዋል

 በቅርቡ በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የሚያጽናና መልእክት ለሰዎች በሚያካፍሉባቸው ዘዴዎች ላይ ማስተካከያ አድርገዋል። ሰዎች ወደሚገኙባቸው አካባቢዎች ወይም ወደየሰዉ ቤት እየሄዱ ከመስበክ ይልቅ መልእክታቸውን በዋነኝነት በስልክና በደብዳቤ አማካኝነት እያካፈሉ ነው። a በርካታ ሰዎች ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላደረጉት ጥረት አድናቆታቸውን ገልጸዋል፤ ይሖዋም ሥራውን እየባረከው እንደሆነ በግልጽ እየታየ ነው። (ምሳሌ 16:3, 4) ከአንዲት ደሴት የተገኙትን አንዳንድ ተሞክሮዎች እንመልከት።

 ከወረርሽኙ በፊት ሄለን አንዲትን ወጣት በተደጋጋሚ እየሄደች ትጠይቃትና መጽሐፍ ቅዱስን ከእሷ ጋር እንድታጠና ታበረታታት ነበር። ወጣቷ ግን የቀረበላትን ግብዣ አልተቀበለችም። ያም ሆኖ በኮቪድ-19 ምክንያት በእንቅስቃሴያቸው ላይ ገደብ ከመጣሉ ከአንድ ቀን በፊት ሄለን ለወጣቷ መጽሐፍ ቅዱስ እና መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል? የሚለውን መጽሐፍ ሰጠቻት። ገደቡ በተጣለበት ወቅት ሄለን ለወጣቷ መጽሐፍ ቅዱስን አብራት እንድታጠና በድጋሚ ግብዣ አቀረበችላት፤ ጥናቱ የሚደረገው በስልክ እንደሆነም ገለጸችላት። በዚህ ጊዜ ወጣቷ ለማጥናት ተስማማች። የሚያደርጉትን ውይይት በጣም ስለወደደችው ብዙም ሳይቆይ በየቀኑ እንድታስጠናት ሄለንን ጠየቀቻት! ወጣቷ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን በስልክ አማካኝነት መከታተልም ጀመረች። የሚገርመው ነገር የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት በሕይወቷ ተግባራዊ ከማድረግ አልፋ የተማረችውን ነገር ለሌሎችም መናገር ጀምራለች።

 በአንድ ጉባኤ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች፣ አገልግሎት ላይ በአካባቢያቸው ላሉ ፖሊሶች ደብዳቤ በመጻፍ ፖሊሶቹ ለሚያከናውኑት ጠቃሚ ሥራ አድናቆታቸውን ገለጹ። ፖሊሶቹ ደብዳቤዎቹን ሲያዩ በጣም ተገረሙ። አንድ ፖሊስ ጄፈርሰን ለተባለ የጉባኤ ሽማግሌ “የይሖዋ ምሥክሮች ፖሊሶችን የሚጠሉ ይመስለኝ ነበር” አለው። ጄፈርሰንም እውነታው ከዚያ ፈጽሞ የተለየ እንደሆነ አስረዳው። ፖሊሶቹ ደብዳቤዎቹ ላይ ባለው የሚያበረታታ ሐሳብ በጣም ስለተደሰቱ ደብዳቤዎቹን በፖሊስ ጣቢያው መግቢያ ላይ ለጠፏቸው። ሌላ ፖሊስ ደግሞ “ምናልባት ሰዎች ይህን ሲያዩ ለእኛ ጥሩ አመለካከት ይኖራቸው ይሆናል” በማለት ተናግሯል።

 ኤድና እና ኤድናሊን ሁለቱም የዘወትር አቅኚዎች b ናቸው። ቤታቸው ኢንተርኔት ስለሌላቸው የጉባኤ ስብሰባዎችን በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት መከታተል አይችሉም። ስለዚህ የይሖዋ ምሥክር ላልሆነች ጎረቤታቸው ደውለው የእሷን ዋይ-ፋይ መጠቀም ይችሉ እንደሆነ ጠየቋት፤ ክፍያው ላይ የተወሰነ መዋጮ እንደሚያደርጉም ነገሯት። ሴትየዋም በነፃ እንዲጠቀሙ ፈቀደችላቸው። ኤድና እና ኤድናሊን ስብሰባዎቹን እንድትከታተል ሲጋብዟት ተስማማች። በአሁኑ ወቅት ሴትየዋ፣ የሴትየዋ ልጅና ሁለት የልጅ ልጆቿ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እያጠኑና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረው እየተገኙ ነው።

 በአንድ አካባቢ ያሉ ወንድሞችና እህቶች በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት የሚቀርብን ንግግር እንዲከታተሉ ጎረቤቶቻቸውን፣ የሥራ ባልደረቦቻቸውንና ሌሎች ሰዎችን ጋበዙ። በዚያ አካባቢ ባለ ሆስፒታል ውስጥ የምትሠራው ኢሌን መጀመሪያ ላይ የሥራ ባልደረቦቿን ለመጋበዝ አመንትታ ነበር። አንዳንድ ሐኪሞች ለይሖዋ ምሥክሮች አሉታዊ አመለካከት ሊኖራቸው እንደሚችል አስባ ነበር። ያም ሆኖ በሆስፒታሉ ውስጥ ያሉ ሐኪሞችን የጽሑፍ መልእክት በመላክ ጋበዘቻቸው። ኢሌን በተለይ ሁለት ሐኪሞችን መጋበዝ በጣም አስፈርቷት ነበር፤ እነዚህ ሐኪሞች ባልና ሚስት ናቸው። ሆኖም ስለ ጉዳዩ ካሰበችበትና ከጸለየችበት በኋላ የጽሑፍ መልእክት በመላክ ጋበዘቻቸው። ሚስትየዋ “ስለዚህ የእናንተ ሃይማኖት አባል እንድሆን እየጋበዝሽኝ ነው?” በማለት መለሰችላት። ኢሌንም ስብሰባው ለይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ሰዎች ክፍት እንደሆነ ገለጸችላት። በቀጣዩ ቀን ኢሌን ባልና ሚስቱ ስብሰባው ላይ ቀድመው እንደገቡ ስታውቅ በጣም ተገረመች! እንዲህ ብላለች፦ “ስብሰባው ከማለቁ በፊት ሚስትየዋ እንዲህ የሚል የጽሑፍ መልእክት ላከችልኝ፦ ‘በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ስገኝ ይህ የመጀመሪያዬ ነው። ቆንጆ ነበር። በጣም ደስ ብሎኛል። ስለጋበዝሽኝ አመሰግናለሁ።’”

ኢሌን

 ኢሌን 20 ሐኪሞችን ስብሰባው ላይ የጋበዘች ሲሆን 16ቱ እንደተገኙ ስታውቅ በጣም ተደስታለች። ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረውን ሐሳብ በመጥቀስ እንዲህ ብላለች፦ “‘እንደ ምንም ብዬ ድፍረት በማግኘት የአምላክን ምሥራች’ ለሥራ ባልደረቦቼ ስለነገርኩ ደስ ብሎኛል።”—1 ተሰሎንቄ 2:2

 ወረርሽኙ ለሁሉም ሰው ከባድ እንደነበር አይካድም። ሆኖም በዚህች ደሴትም ሆነ በሌሎች የዓለም ክፍሎች ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሌሎችን ለማጽናናትና ለመርዳት ሲሉ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ደስታቸውንና አዎንታዊ አመለካከታቸውን ይዘው መቀጠል ችለዋል።—የሐዋርያት ሥራ 20:35

a የይሖዋ ምሥክሮች አገልግሎታቸውን የሚያከናውኑት ለአካባቢያቸው የሚሠሩ የመረጃ ጥበቃ ሕጎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው።

b አቅኚዎች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆኑ ክርስቲያኖች ናቸው።