በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በውጤቱ በጣም ተደነቀች

በውጤቱ በጣም ተደነቀች

 ዴሲካር የተባለች አንዲት ነጠላ ወላጅ የዘወትር አቅኚ በመሆን አገልግሎቷን የማስፋት ፍላጎት ነበራት። የምትኖረው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ባጋጠማት በቬኔዙዌላ ነው። ያም ሆኖ አቅኚነት ለመጀመር ቆርጣ ነበር፤ ያደረገችውም ይህንኑ ነው። ይህን ውሳኔ በማድረጓ በጣም ብትደሰትም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተከሰተ።

 ወረርሽኙ እንደተከሰተ አካባቢ ዴሲካር በስብከት ዘዴያችን ላይ የተደረገውን ለውጥ መልመድ ከብዷት ነበር። ደብዳቤዎችን መጻፍ ለእሷ ቀላል አልነበረም። በተጨማሪም በአካባቢዋ የኢንተርኔት አገልግሎት በጣም ውድ ስለሆነ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ማገልገልም አልቻለችም። “በሁኔታው በጣም ተስፋ ቆርጬ ነበር” በማለት ተናግራለች። አክላም “በአገልግሎት የማደርገው እንቅስቃሴ ድንገት ተገደበ። ውጤታማ የዘወትር አቅኚ መሆን እንዳልቻልኩ ተሰማኝ” ብላለች።

 ከዚያ ግን ጥር 2021 ላይ በቬኔዙዌላ ያለው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ልዩ የስብከት ዘመቻ እንዲካሄድ ፈቃድ ሰጠ። በወሩ ውስጥ ባሉት በአምስቱም የሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት፣ የተመረጡ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግሮች 60 በሚያክሉ የሬድዮ ጣቢያዎችና በ7 የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንዲተላለፉ ዝግጅት ተደረገ። የይሖዋ ምሥክሮች ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች እንዲጋብዙ ማበረታቻ ተሰጣቸው። በተጨማሪም ቅርንጫፍ ቢሮው ለእያንዳንዱ ንግግር ጥያቄዎችንና ጥቅሶችን በማዘጋጀት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በደብዳቤ ወይም በስልክ ሲያገለግሉ እንዲጠቀሙባቸው አደረገ። ቅርንጫፍ ቢሮው ወንድሞችና እህቶች የጽሑፍ መልእክት በመጠቀም እንዲያገለግሉም ማበረታቻ ሰጠ፤ ይህ የስብከት ዘዴ በቬኔዙዌላ ላሉ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች አዲስ ነበር።

 ዴሲካር በዚህ ዘመቻ መካፈል በመቻሏ በጣም ተደሰተች። የጽሑፍ መልእክት በመጠቀም አገልግላ ባታውቅም ለመሞከር ወሰነች። ያም ሆኖ ይህን ዘዴ ለመጠቀም እርዳታ አስፈልጓታል። “የቴክኖሎጂ ውጤቶች አጠቃቀም ላይ ጎበዝ አይደለሁም” በማለት በሐቀኝነት ተናግራለች። ስለዚህ እንድታስተምራት ልጇን ጠየቀቻት፤ ብዙም ሳይቆይ ዴሲካር በዘመቻው ለመካፈል ዝግጁ ሆነች።

ዴሲካር

 ዴሲካር፣ ወደምታውቃቸው ብዙ ሰዎች የጽሑፍ መልእክት በመላክ አስቀድመው የተቀዱትን ንግግሮች እንዲያዳምጡ ጋበዘቻቸው። በውጤቱ በጣም ተደነቀች። ከጋበዘቻቸው ሰዎች መካከል ጥቂት የማይባሉት ንግግሮቹን ያዳመጡ ከመሆኑም ሌላ ጥያቄዎችን ጠይቀዋታል። ሌሎች ደግሞ የተላለፈውን ፕሮግራም ማዳመጥ ባይችሉም በንግግሮቹ ላይ ምን ሐሳቦች እንደቀረቡ ዴሲካርን ይጠይቋት ነበር። ዴሲካር “አጠር ያሉ ማስታወሻዎችን ይዤ ሐሳቡን አካፍላቸዋለሁ” በማለት ተናግራለች። አክላም “በወር ውስጥ የማደርገው ተመላልሶ መጠየቅ ከ5 አይበልጥም ነበር፤ በዚህ ዘመቻ መጨረሻ ግን 112 ተመላልሶ መጠየቆችን አድርጌአለሁ!” ብላለች። a

 ዴሲካር የይሖዋ ምሥክር ያልሆነች እህቷንም ንግግሮቹን በሬድዮ እንድታዳምጥ ጋብዛታለች፤ እህቷ የምትኖረው ከእሷ ቤት አጠገብ ነበር። ዴሲካር እንዲህ ብላለች፦ “እህቴ ግብዣውን መቀበሏ አስገረመኝ። በየሳምንቱ እሁድ ከጠዋቱ 2 ሰዓት ላይ ወደ እሷ ቤት እሄድና ንግግሩን አብረን እናዳምጣለን። ፕሮግራሙ እየተላለፈ ባለበት ጊዜም ሆነ ከዚያ በኋላ ብዙ ጥያቄዎችን ትጠይቅ ነበር።” የዴሲካር እህት የኢየሱስን ሞት መታሰቢያም በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ተከታትላለች፤ በተጨማሪም የእሷን ኢንተርኔት፣ ለአገልግሎት እንድትጠቀምበት ለዴሲካር ፈቅዳላታለች።

 ዴሲካር እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋን በጣም አመሰግነዋለሁ። የጉባኤዬ ሽማግሌዎችም ስላበረታቱኝ ከልብ አመሰግናቸዋለሁ። በአገልግሎት የነበረኝን ደስታ መልሼ እንዳገኝ ረድተውኛል።” (ኤርምያስ 15:16) ዴሲካር በአቅኚነት ማገልገሏንም ሆነ በጽሑፍ መልእክት አማካኝነት ያገኘቻቸውን ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ተከታትላ መርዳቷን ቀጥላለች።

a የይሖዋ ምሥክሮች አገልግሎታቸውን የሚያከናውኑት በአካባቢያቸው ያለውን የመረጃ አጠባበቅ ሕግ ተከትለው ነው።