በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ውጥረት ውስጥ ላሉ የሆስፒታል ሠራተኞች የተሰጠ እርዳታ

ውጥረት ውስጥ ላሉ የሆስፒታል ሠራተኞች የተሰጠ እርዳታ

 በኖርዝ ካሮላይና፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚኖረው ብሪን የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ አባል ነው፤ የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ታካሚዎች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት ከሆስፒታሎች ጋር ተባብረው ይሠራሉ።

 በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ብዙ ሆስፒታሎች፣ ጠያቂዎች እንዳይገቡ ከልክለዋል። ብሪን ለይሖዋ ምሥክር ታካሚዎች እርዳታ መስጠት የሚችለው እንዴት እንደሆነ ለመጠየቅ በአንድ ሆስፒታል ለሚገኝ የሃይማኖታዊ ድጋፍ ዴስክ ኃላፊ ደወለ።

 በዚህ ጊዜ የኃላፊው ረዳት ብሪንን አነጋገረው። ብሪን፣ ጠያቂዎች ወደ ሆስፒታል እንዲገቡ ስለማይፈቀድ የይሖዋ ምሥክሮቹ ታካሚዎች እሱን ማነጋገር እንዲችሉ ስልክ ቁጥሩ ለታካሚዎቹ እንዲሰጣቸው ማድረግ ይቻል እንደሆነ ጠየቀ። የኃላፊው ረዳትም በሐሳቡ ተስማማ።

 ከዚያም ብሪን ስለ ሆስፒታሉ ሠራተኞች ማሰብ ጀመረ። በመሆኑም በሆስፒታሉ የሚከናወነውን ሥራ እንደሚያደንቅና የሠራተኞቹ ደህንነት እንዳሳሰበው ለኃላፊው ረዳት ነገረው። አክሎም ሁሉም ሰዎች፣ በተለይም የሆስፒታል ሠራተኞች በወረርሽኙ የተነሳ ከፍተኛ ውጥረት እንዳጋጠማቸው የሚገልጽ ዘገባ እንዳነበበ ገለጸለት።

 የኃላፊው ረዳትም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሆስፒታሉ ውስጥ ከፍተኛ ውጥረት እንዲነግሥ እንዳደረገ ገለጸ።

 ከዚያም ብሪን እንዲህ አለው፦ “ድረ ገጻችን ውጥረትን መቋቋም ስለሚቻልበት መንገድ የሚገልጽ መረጃ ይዟል። jw.org​ን ከፍተህ በመፈለጊያው ላይ ‘ውጥረት’ ብለህ ብትጽፍ ለሆስፒታሉ ሠራተኞች የሚጠቅሙ አበረታች ጽሑፎችን ማግኘት ትችላለህ።”

 እየተነጋገሩ ሳለ የኃላፊው ረዳት ድረ ገጹን ከፍቶ በመፈለጊያው ላይ “ውጥረት” ብሎ በመጻፍ ጽሑፎቹን አገኘ። በዚህ ጊዜ እንዲህ አለ፦ “በጣም ይገርማል! ይህን ለኃላፊው አሳየዋለሁ። መረጃው ለሠራተኞቻችንም ሆነ ለሌሎች የሚጠቅም ነው። እንዲያውም አትሜ አሰራጨዋለሁ።”

 ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ ብሪን ኃላፊውን አነጋገረው፤ እሱም ድረ ገጹን እንዳየው እንዲሁም ስለ ውጥረትና ተያያዥ ስለሆኑ ሌሎች ጉዳዮች የሚገልጹ ጽሑፎችን እንዳተማቸው ገለጸ። እንዲሁም እነዚህን ጽሑፎች ለነርሶቹና ለሌሎቹ የሆስፒታል ሠራተኞች እንደሰጧቸው ነገረው።

 ብሪን እንዲህ ብሏል፦ “ኃላፊው ለምናከናውነው ሥራ እንዲሁም ግሩም ሆነው ለተዘጋጁት ጽሑፎች ያለውን አድናቆት ገለጸ። ጽሑፎቹ በጣም ጠቃሚ እንደሆኑ ተናግሯል።”