በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች ፕሮቴስታንቶች ናቸው?

የይሖዋ ምሥክሮች ፕሮቴስታንቶች ናቸው?

 አይደሉም። የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያኖች ናቸው፤ ያም ቢሆን ፕሮቴስታንቶች አይደለንም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

 ፕሮቴስታንት ለሚለው ቃል “የሮም ካቶሊክን የሚቃወም” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። እርግጥ ነው፣ የይሖዋ ምሥክሮች የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረውን ትምህርት አይደግፉም፤ ያም ቢሆን በሚከተሉት ምክንያቶች የተነሳ ፕሮቴስታንት አይደለንም፦

  1.   በርካታ የፕሮቴስታንት ትምህርቶች ከትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር ይጋጫሉ። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው “አንድ አምላክ” እንዳለ ነው፤ በመሆኑም የሥላሴ ትምህርት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ የለውም። (1 ጢሞቴዎስ 2:5፤ ዮሐንስ 14:28) በተጨማሪም አምላክ ክፉዎችን የሚቀጣው በገሃነመ እሳት በማቃጠል ሳይሆን ለዘላለም ከሕልውና ውጭ እንዲሆኑ በማድረግ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል።—መዝሙር 37:9፤ 2 ተሰሎንቄ 1:9

  2.   የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንንም ሆነ ሌላ ማንኛውንም ሃይማኖታዊ ቡድን አንቃወምም ወይም ሃይማኖቱን ለማሻሻል አንሞክርም። በአንጻሩ የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበክ ሰዎች በምሥራቹ ላይ እምነት እንዲኖራቸው ለማድረግ እንሞክራለን። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) ዓላማችን ሌሎች ሃይማኖታዊ ቡድኖችን ማሻሻል ሳይሆን ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ስለ አምላክና ስለ ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ እውነቱን ማስተማር ነው።—ቆላስይስ 1:9, 10፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:24, 25