በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የቤተሰብ ሕይወትና ጓደኝነት

የቤተሰብ ሕይወትና ጓደኝነት

አንዳንድ ሰዎች ከቤተሰቦቻቸውና ከጓደኞቻቸው ጋር ተስማምተው መኖር ይከብዳቸዋል። ማኅበራዊ ሕይወትን ለማሻሻል የሚረዱ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን እስቲ እንመልከት።

ራስ ወዳድ አትሁን

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።”—ፊልጵስዩስ 2:4

ምን ማለት ነው? ከሌሎች ጋር ጥሩ ወዳጅነት መመሥረት የምትችለው ተቀባይ ከመሆን ይልቅ ሰጪ ስትሆን ነው። ራስ ወዳድ ከሆንክ ከሌሎች ጋር ያለህ ዝምድና ይበላሻል። ለምሳሌ አንድ ባል ራስ ወዳድ ከሆነ ለሚስቱ ያለውን ታማኝነት ሊያጎድል ይችላል። በተጨማሪም አንድ ሰው ስለ ንብረቱ ወይም ስለ እውቀቱ ሁልጊዜ ጉራ የሚነዛ ከሆነ ማንም ሰው የእሱ ጓደኛ መሆን አይፈልግም። ዘ ሮድ ቱ ካራክተር የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው “ራስ ወዳድነት ለብዙ ችግር ይዳርጋል።”

ምን ማድረግ ትችላለህ?

  • ሌሎችን እርዳ። እውነተኛ ጓደኛሞች እርስ በርስ ይተማመናሉ እንዲሁም ይረዳዳሉ። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሌሎችን የሚረዱ ሰዎች በመንፈስ ጭንቀት የመያዝ አጋጣሚያቸው ዝቅተኛ ነው፤ ለራሳቸው ያላቸው ግምትም ይጨምራል።

  • የሌሎችን ስሜት ተረዳ። የሌሎችን ስሜት የሚረዳ ሰው የሰዎች ሥቃይ ይገባዋል። የሌሎችን ስሜት የምትረዳ ከሆነ ስሜታቸውን የሚያቆስል የአሽሙር ንግግር ከመናገር ትቆጠባለህ።

    የሌሎችን ስሜት መረዳትህ ከሰዎች ጋር ተቻችሎ መኖር ቀላል እንዲሆንልህ ያደርጋል። ይህ ባህርይ አድልዎ ላለማድረግና ከአንተ የተለየ ባሕልና አስተዳደግ ካላቸው ሰዎች ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ይረዳሃል።

  • ለሌሎች ጊዜህን ስጥ። ከሌሎች ጋር ጊዜ ባሳለፍክ መጠን ይበልጥ እያወቅካቸው ትሄዳለህ። እውነተኛ ጓደኞች ማፍራት የምትችለው ከሰዎች ጋር ቁም ነገር የምታወራ ከሆነ ነው። ሌሎች ሲናገሩ በጥሞና ማዳመጥ አስፈላጊ ነው። ጓደኞችህ ለሚያሳስቧቸው ነገሮች ትኩረት ስጥ። “ከሌሎች ጋር ትርጉም ያለው ጭውውት ማድረግ ደስታ ለማግኘት አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚችል” በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት ገልጿል።

ጓደኞችህን በጥንቃቄ ምረጥ

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “መጥፎ ጓደኝነት ጥሩውን ሥነ ምግባር ያበላሻል።”—1 ቆሮንቶስ 15:33 የግርጌ ማስታወሻ

ምን ማለት ነው? ጓደኞችህ በአንተ ላይ ጥሩ ወይም መጥፎ ተጽዕኖ ማሳደራቸው አይቀርም። የኅብረተሰብ ጥናት ባለሙያዎች፣ ጓደኞች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ በሰዎች ሕይወት ላይ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ ይገልጻሉ። ለምሳሌ ጓደኞችህ የሚያጨሱ ከሆነ ማጨስ ልትጀምር እንደምትችል፣ ፍቺ ከፈጸሙ ደግሞ አንተም ፍቺ ለመፈጸም ልትነሳሳ እንደምትችል ይናገራሉ።

ምን ማድረግ ትችላለህ? ጥሩ ባሕርያት ያሏቸው እንዲሁም ላቅ ባሉ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች የሚመሩ ጓደኞችን ምረጥ። ለምሳሌ ጥበበኛ፣ ሰው አክባሪ፣ ለጋስና እንግዳ ተቀባይ ከሆኑ ሰዎች ጋር ወዳጅነት መመሥረት ትችላለህ።

ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች

ባለትዳሮች፣ ወጣቶችና ልጆች በቤተሰብ ሕይወታቸው ደስተኛ እንዲሆኑ የሚረዱ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ቪዲዮዎችን ተመልከት

ጎጂ ንግግርን አስወግድ።

“ሳይታሰብበት የሚነገር ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል።”​—ምሳሌ 12:18

ለጋስ ሁን።

“ለጋስ ሰው ይበለጽጋል።”​—ምሳሌ 11:25

ሌሎች እንዲያደርጉልህ የምትፈልገውን ነገር አድርግላቸው።

“ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም አድርጉላቸው።”​—ማቴዎስ 7:12