በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወረርሽኝ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወረርሽኝ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 መጽሐፍ ቅዱስ በመጨረሻዎቹ ቀናት ቸነፈር (ወረርሽኞችን ጨምሮ ተላላፊ በሽታዎች) እንደሚከሰት አስቀድሞ ተናግሯል። (ሉቃስ 21:11) እንዲህ ያሉት ወረርሽኞች አምላክ እየቀጣን እንዳለ የሚያሳዩ አይደሉም። እንዲያውም አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት ወረርሽኞችን ጨምሮ ሁሉንም የጤና ችግሮች በቅርቡ ያስወግዳል።

 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወረርሽኝ አስቀድሞ ተናግሯል?

 መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ኮቪድ-19፣ ኤድስ ወይም የኅዳር በሽታ ያሉ ወረርሽኞችን በስም ጠቅሶ ትንቢት አይናገርም። ሆኖም “ቸነፈር” እና “ገዳይ መቅሰፍት” እንደሚከሰት አስቀድሞ ተናግሯል። (ሉቃስ 21:11፤ ራእይ 6:8) እነዚህ ክንውኖች ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ ወይም “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት” ገጽታዎች ናቸው።—2 ጢሞቴዎስ 3:1፤ ማቴዎስ 24:3

 አምላክ ሰዎችን በበሽታ የቀጣበት ጊዜ አለ?

 መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ሰዎችን በበሽታ የቀጣባቸው ጊዜያት እንዳሉ ይገልጻል። ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎችን በሥጋ ደዌ ቀጥቷል። (ዘኁልቁ 12:1-16፤ 2 ነገሥት 5:20-27፤ 2 ዜና መዋዕል 26:16-21) ሆኖም በእነዚህ ጊዜያት ሰዎችን የቀጣው በጅምላ አልነበረም፤ ጥፋት ያልሠሩ ሰዎች በበሽታው አልተያዙም። ከዚህ ይልቅ አምላክ የቀጣው በእሱ ላይ ያመፁ ሰዎችን ለይቶ ነው።

 በዛሬው ጊዜ ያሉት ወረርሽኞች አምላክ እየቀጣን እንዳለ ያሳያሉ?

 አያሳዩም። አንዳንድ ሰዎች አምላክ በዛሬው ጊዜ ሰዎችን በወረርሽኞችና በሌሎች በሽታዎች እንደሚቀጣ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሐሳብ አይደግፍም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

 አንደኛው ምክንያት ጥንትም ሆነ በዛሬው ጊዜ ያሉ አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች በበሽታ መያዛቸው ነው። ለምሳሌ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ የሆነው ጢሞቴዎስ ‘በተደጋጋሚ የሚነሳ ሕመም’ ያሠቃየው ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 5:23) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው መታመሙ የአምላክን ሞገስ እንዳጣ የሚያሳይ እንደሆነ አይናገርም። በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ሊታመሙ ወይም በበሽታ ሊያዙ ይችላሉ። ይህ ማንም ሰው ሊያጋጥመው የሚችል ነገር ነው።—መክብብ 9:11

 በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ክፉዎችን የሚቀጣበት ጊዜ ገና እንዳልደረሰ ይገልጻል። ከዚህ ይልቅ አሁን የምንኖረው ‘በመዳን ቀን’ ማለትም አምላክ ሰዎች ሁሉ ወደ እሱ እንዲቀርቡና እንዲድኑ ግብዣ እያቀረበ ባለበት ጊዜ ውስጥ ነው። (2 ቆሮንቶስ 6:2) አምላክ “የመንግሥቱ ምሥራች” በዓለም ዙሪያ እንዲሰበክ በማድረግ ይህን ግብዣ አቅርቧል።—ማቴዎስ 24:14

 ወረርሽኞች የሚወገዱበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

 አዎ። መጽሐፍ ቅዱስ ማንም ሰው የማይታመምበት ጊዜ በቅርቡ እንደሚመጣ አስቀድሞ ተናግሯል። አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት ሁሉንም በሽታዎች ያስወግዳል። (ኢሳይያስ 33:24፤ 35:5, 6) መከራ፣ ሥቃይና ሞትን ያስቀራል። (ራእይ 21:4) ከዚህም ሌላ ሰዎችን ከሞት በማስነሳት ገነት በሆነች ምድር ላይ ጥሩ ጤና አግኝተው እንዲኖሩ ያደርጋል።—መዝሙር 37:29፤ የሐዋርያት ሥራ 24:15

 ስለ በሽታ የሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች

 ማቴዎስ 4:23፦ “[ኢየሱስ] በምኩራቦቻቸው እያስተማረና የመንግሥቱን ምሥራች እየሰበከ እንዲሁም በሕዝቡ መካከል ያለውን ማንኛውንም ዓይነት በሽታና ማንኛውንም ዓይነት ሕመም እየፈወሰ በመላዋ ገሊላ ተዘዋወረ።”

 የሚያስተላልፈው መልእክት፦ ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት የአምላክ መንግሥት በቅርቡ ለሰው ልጆች ሁሉ ምን እንደሚያደርግ በተወሰነ ደረጃ ያሳያሉ።

 ሉቃስ 21:11 “ቸነፈር ይሆናል።”

 የሚያስተላልፈው መልእክት፦ በስፋት የተሰራጩ የጤና ችግሮች የመጨረሻዎቹ ቀናት ምልክት ገጽታዎች ናቸው።

 ራእይ 6:8 “እነሆ ግራጫ ፈረስ ነበር፤ በእሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበር። መቃብርም በቅርብ ይከተለው ነበር። ሞትና መቃብርም . . . በገዳይ መቅሰፍት . . . እንዲገድሉ . . . ሥልጣን ተሰጣቸው።”

 የሚያስተላልፈው መልእክት፦ በራእይ መጽሐፍ ላይ የተጠቀሱትን አራት ፈረሰኞች አስመልክቶ የተነገረው ትንቢት ወረርሽኞች እኛ ባለንበት ዘመን እንደሚከሰቱ ይጠቁማል።