በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ከዕፅ ሱስ ለመላቀቅ ሊረዳህ ይችላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ከዕፅ ሱስ ለመላቀቅ ሊረዳህ ይችላል?

 ሕገ ወጥ ዕፆችን ጨምሮ አንዳንድ ንጥረ ነገሮችን ያለአግባብ መጠቀም በየዓመቱ ለሚሊዮኖች ሞት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ምክንያት እየሆነ ነው። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ደግሞ ይህ ችግር ይበልጥ ተባብሷል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጥበብ ያዘለ ምክር ብዙዎችን ከዕፅ ሱስ እንዲላቀቁ ረድቷቸዋል። አንተም እንዲህ ካለው ችግር ጋር እየታገልክ ከሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ሊረዳህ ይችላል። a

በዚህ ርዕስ ውስጥ

 መጽሐፍ ቅዱስ ከዕፅ ሱስ ለመላቀቅ የሚረዳህ እንዴት ነው?

 ተመራማሪዎች፣ ሱስ ብዙውን ጊዜ እንደ ብቸኝነት፣ ውጥረት፣ ጭንቀት እና ድብርት ካሉ ሥር የሰደዱ ችግሮች ጋር ተያያዥነት እንዳለው ደርሰውበታል። መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ሱስ ሊያመሩ የሚችሉ ስሜቶችን ለማሸነፍ የሚያስችል እምነት እንድታዳብር ይረዳሃል። በተጨማሪም ከአምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት የምትችለው እንዴት እንደሆነ ያስተምራል። (መዝሙር 25:14) በራስህ አቅም መፍታት የማትችላቸውን ችግሮች በአምላክ እርዳታ ማሸነፍ ትችላለህ።—ማርቆስ 11:22-24

 ከሱስ ለመላቀቅ የሚረዱ አራት መጽሐፍ ቅዱሳዊ እርምጃዎች

  1.  1. ይሖዋ አምላክን እወቅ። b (ዮሐንስ 17:3) ይሖዋ ፈጣሪ ከመሆኑም ሌላ ገደብ የለሽ ኃይል አለው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ይሖዋ የሚወድህ አባትህ ነው። ከአንተ ጋር የቅርብ ዝምድና መመሥረት እንዲሁም ኃይሉን ተጠቅሞ አንተን መርዳት ይፈልጋል። (ኢሳይያስ 40:29-31፤ ያዕቆብ 4:8) ከእሱ ፍቅር ለመጠቀም ከመረጥክ ግሩም የወደፊት ተስፋ አዘጋጅቶልሃል።—ኤርምያስ 29:11፤ ዮሐንስ 3:16

  2.  2. የይሖዋን እርዳታ ጠይቅ። ሱስህን በማሸነፍ ‘ቅዱስ [ወይም ንጹሕ] እና በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ያለው’ ሰው መሆን እንድትችል እንዲረዳህ አምላክን በጸሎት ለምነው። (ሮም 12:1) በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ” ኃይል ይሰጥሃል። (2 ቆሮንቶስ 4:7፤ ሉቃስ 11:13) እሱ የሚሰጥህ ኃይል ከዕፅ ሱስ እንድትላቀቅና ከእሱ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ‘አዲስ ስብዕና’ እንድታዳብር ይረዳሃል።—ቆላስይስ 3:9, 10

  3.  3. አእምሮህን በአምላክ ሐሳብ ሙላ። (ኢሳይያስ 55:9) አምላክ ‘አእምሮህን የሚያሠራው ኃይል እየታደሰ እንዲሄድ’ ማለትም የምታስብበትን መንገድ እንድትቀይር ይረዳሃል፤ ይህ ደግሞ ከሱስ ለመላቀቅ ያስችልሃል። (ኤፌሶን 4:23) የአምላክ ሐሳብ የሚገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሆነ አዘውትረህ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብህ አስፈላጊ ነው። (መዝሙር 1:1-3) ብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች ለመረዳት የሌሎችን እርዳታ ማግኘታቸው በእጅጉ ጠቅሟቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች አሳታፊ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በነፃ ይሰጣሉ። (የሐዋርያት ሥራ 8:30, 31) በተጨማሪም በስብሰባዎቻችን ላይ እንድትገኝ እንጋብዝሃለን፤ በስብሰባዎቻችን ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚያስተምር እንዲሁም ትምህርቶቹን በሕይወታችን ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንማራለን።

  4.  4. ጥሩ ጓደኞች ምረጥ። ከሱስ ለመላቀቅ በምታደርገው ትግል ጓደኞችህ ጥሩ ወይም መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብህ ይችላሉ። (ምሳሌ 13:20) አምላክ እሱን ከሚያመልኩ ሰዎች መካከል ጥሩ ጓደኞች እንድታገኝ ይረዳሃል፤ ከእነሱ ጋር ወዳጅ በመሆን እንድትጠቀምም ይፈልጋል። (መዝሙር 119:63፤ ሮም 1:12) በተጨማሪም በመዝናኛ ምርጫህ ረገድ ጠንቃቃ ሁን፤ ምክንያቱም የምታያቸውን፣ የምትሰማቸውን ወይም የምታነብባቸውን ገጸ ባሕርያት ጓደኛ እያደረግካቸው ነው ሊባል ይችላል። ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ያለህን ቁርጠኝነት ከሚያዳክምብህ ከማንኛውም ነገር ራቅ።—መዝሙር 101:3፤ አሞጽ 5:14

 ከሱስ እንድትላቀቅ ሊረዱህ የሚችሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች

 መዝሙር 27:10 “የገዛ አባቴና እናቴ ቢተዉኝ እንኳ ይሖዋ ራሱ ይቀበለኛል።”

 “ወላጅ አባቴን አላውቀውም፤ በዚህም ምክንያት የባዶነት ስሜት ይሰማኝ ነበር። ይሖዋ አምላክ ከልቡ የሚወደኝ እውን አካል እንደሆነ ስማር ግን ሕይወቴ ትርጉም ያለው ሆነ፤ ሱሴን ማሸነፍም ቻልኩ።”—ዊልቢ፣ ከሄይቲ

 መዝሙር 50:15 “በጭንቅ ቀን ጥራኝ። እኔ እታደግሃለሁ።”

 “ሱሴ በሚያገረሽብኝ ጊዜም ጭምር መታገሌን እንድቀጥል ይህ ጥቅስ በተደጋጋሚ ብርታት ሰጥቶኛል። ይሖዋ እንደ ቃሉ አድርጎልኛል።”—ሴርሂ፣ ከዩክሬን

 ምሳሌ 3:5, 6 “በሙሉ ልብህ በይሖዋ ታመን፤ ደግሞም በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመካ። በመንገድህ ሁሉ እሱን ግምት ውስጥ አስገባ፤ እሱም ጎዳናህን ቀና ያደርገዋል።”

 “ይህ ጥቅስ በራሴ ሳይሆን በይሖዋ እንድታመን ረድቶኛል። እሱ በሚሰጠኝ ብርታት ሕይወቴን ሙሉ በሙሉ መቀየር ችያለሁ።”—ሚኬሌ፣ ከጣሊያን

 ኢሳይያስ 41:10 “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ። እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ። አበረታሃለሁ፤ አዎ እረዳሃለሁ፤ በጽድቅ ቀኝ እጄ አጥብቄ እይዝሃለሁ።”

 “ዕፅ ካልወሰድኩ በከፍተኛ ጭንቀት እዋጥ ነበር። ይህ ጥቅስ፣ አምላክ ጭንቀቴን ለማሸነፍ እንደሚረዳኝ እንድተማመን አድርጎኛል፤ ደግሞም አምላክ ረድቶኛል።”—አንዲ፣ ከደቡብ አፍሪካ

 1 ቆሮንቶስ 15:33 የግርጌ ማስታወሻ፦ “አትታለሉ። መጥፎ ጓደኝነት ጥሩውን ሥነ ምግባር ያበላሻል።”

 “ዕፅ መውሰድ ያስጀመሩኝና ወደ ሱስ የመሩኝ መጥፎ ጓደኞች ናቸው። ከሱሴ መላቀቅ የቻልኩት ከእነሱ ጋር ያለኝን ጓደኝነት ካቋረጥኩና የሚደነቅ ንጹሕ አኗኗር ካላቸው ሰዎች ጋር ጓደኝነት ከመሠረትኩ በኋላ ነው።”—አይዛክ፣ ከኬንያ

 2 ቆሮንቶስ 7:1 “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ።”

 “እነዚህ ቃላት ሰውነቴን ለማንጻት በማደርገው ትግል እንድቀጥል እንዲሁም ወደ ቀድሞው የሱስና የጥፋት ጎዳና እንዳልመለስ አነሳስተውኛል።”—ሮዛ፣ ከኮሎምቢያ

 ፊልጵስዩስ 4:13 “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ።”

 “በራሴ አቅም ዕፅ መውሰዴን ማቆም እንደማልችል ተገንዝቤ ስለነበር አምላክ እንዲረዳኝ ጸለይኩ። እሱም የሚያስፈልገኝን ብርታት ሰጥቶኛል።”—ፓትሪሺያ፣ ከጣሊያን

 ተጨማሪ ተሞክሮዎች፦ በመጽሐፍ ቅዱስ እርዳታ ሱስን አሸንፈዋል

 ጆሴፍ ኢሬንቦጌን ያደገው በዓመፅ በታወቀች ከተማ ውስጥ ነው፤ እሱም የአልኮል፣ የሲጋራ፣ የማሪዋና እና የሄሮይን ሱሰኛ ሆነ። ከመጠን በላይ ዕፅ ወስዶ ሞት አፋፍ የደረሰባቸው ብዙ ጊዜያት ነበሩ። ሆኖም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ለውጥ ማድረግ እንደሚችል አሳመነው። የእሱን ተሞክሮ ለማንበብ “ለራሴም ሆነ ለሴቶች አክብሮት ማሳየትን ተማርኩ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

 ዲሚትሪ ኮርሹኖቭ ከመጠጥ ሱስ ለመላቀቅ ቢታገልም ሱሱ በተደጋጋሚ ያገረሽበት ነበር። እንዲሳካለት የረዳው ምን እንደሆነ ለማየት ‘በሕይወቴ ተመረርኩ’ የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።

 መጽሐፍ ቅዱስ ከሱስ ለመላቀቅ ሕክምና መውሰድን ይከለክላል?

 አይከለክልም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም” ይላል። (ማቴዎስ 9:12) በተመሳሳይም የዩናይትድ ስቴትስ የፀረ ዕፅ ሱሰኝነት ብሔራዊ ተቋም እንዲህ ይላል፦ “የዕፅ ሱስ ውስብስብ በሽታ ነው፤ ብዙውን ጊዜ እንዲህ ካለው በሽታ ለመላቀቅ ፍላጎት ወይም ቁርጠኝነት ብቻ በቂ አይደለም።” እርግጥ ነው፣ አምላክ የሚሰጠው ብርታት ከየትኛውም ሰው ቁርጠኝነት የበለጠ ኃይል አለው። ያም ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በመከተል ከዕፅ ሱስ መላቀቅ የቻሉ ብዙ ሰዎች የሕክምና እርዳታም አስፈልጓቸዋል። c ለምሳሌ፣ አለን የተባለ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “አልኮል መጠጣቴን ባቆምኩበት ወቅት በጣም ታምሜ ነበር። ከመንፈሳዊ እርዳታ በተጨማሪ የሕክምና እርዳታ ማግኘት እንዳለብኝ የተገነዘብኩት በዚህ ጊዜ ነበር።”

 መጽሐፍ ቅዱስ ዕፆችን ለሕክምና መጠቀምን ይከለክላል?

 አይከለክልም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንድን ሕመም ለማከም ወይም ሊሞት የተቃረበ ሰው የሚሰማውን ሥቃይ ለማስታገሥ የአልኮል መጠጥ ስለመጠቀም ይናገራል። (ምሳሌ 31:6፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:23) ሆኖም ልክ እንደ አልኮል መጠጥ ሁሉ፣ ሥቃይን ለማስታገሥ በሐኪም ትእዛዝ የሚወሰዱ ዕፆችም ሱስ የማስያዝ ከፍተኛ ኃይል አላቸው። በመሆኑም በሐኪም ትእዛዝ ከሚወሰዱ ማስታገሻዎች ጋር በተያያዘም አደጋውን አስተውሎ ጥንቃቄ ማድረግ የጥበብ እርምጃ ነው።—ምሳሌ 22:3

a ይህ ርዕስ የሚያተኩረው ከዕፅ ሱስ በመላቀቅ ላይ ቢሆንም የተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ሌሎች ሱሶችንም ለማሸነፍ ይረዳሉ፤ ከእነዚህም መካከል የአልኮል መጠጥ፣ የትምባሆ፣ የምግብ፣ የቁማር፣ የፖርኖግራፊ ወይም የማኅበራዊ ሚዲያ ሱስ ይገኙበታል።

b ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

c እርዳታ ሊያበረክቱ የሚችሉ በርካታ የሕክምና ማዕከሎች፣ ሆስፒታሎችና የማገገሚያ ፕሮግራሞች አሉ። እያንዳንዱ ሰው አማራጮቹን በጥንቃቄ መገምገምና የትኛውን ሕክምና ቢወስድ እንደሚሻል መወሰን አለበት።—ምሳሌ 14:15