በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በወንዶች ላይ የሚከሰት ጭንቀት—መጽሐፍ ቅዱስ ምን የመፍትሔ ሐሳብ ይሰጣል?

በወንዶች ላይ የሚከሰት ጭንቀት—መጽሐፍ ቅዱስ ምን የመፍትሔ ሐሳብ ይሰጣል?

 ጭንቀት a ስላደረበት ሰው ስታስብ፣ ቶሎ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ፍርሃት ያሽመደመደው፣ ጠዋት ጠዋት ከአልጋ መነሳት የሚጨንቀው ወይም ነጋ ጠባ ስለ ጭንቀቱ የሚያወራ ሰው ሊሆን ይችላል።

 በእርግጥ ጭንቀት ሲሰማቸው እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች ይኖራሉ። ሆኖም ተመራማሪዎች እንደደረሱበት፣ አንዳንዶች በተለይ ደግሞ ወንዶች ጭንቀትን የሚያስተናግዱበት መንገድ ከዚህ የተለየ ሊሆን ይችላል። አንድ ሪፖርት እንደገለጸው፣ ወንዶች “ጭንቀታቸውን ለመርሳት ወደ አልኮል መጠጥ ወይም ወደ ዕፅ ዘወር የማለት አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው፤ ስለዚህ የመጠጥ ችግር እንዳለበት የሚሰማን አንድ ወንድ፣ ዋነኛው ችግሩ ጭንቀት ሊሆን ይችላል። እንዲሁም ብዙውን ጊዜ እንደሚታየው፣ ወንዶች ጭንቀታቸውን የሚገልጹት በቁጣና በብስጭት ነው።”

 እርግጥ ነው፣ ሁሉም ወንድ ጭንቀት ሲሰማው ተመሳሳይ ነገር ያደርጋል ማለት አይደለም። ጭንቀት በሰዎች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ምንም ይሁን ምን፣ በዘመናችን በጣም እየተስፋፋ የመጣ ችግር ሆኗል፤ ምክንያቱም የምንኖረው ‘ለመቋቋም በሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ በሆነ ዘመን’ ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) አንተም ጭንቀትህን ለመርሳት እየታገልክ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳህ ይችላል?

ጭንቀትን ለመቋቋም የሚረዱ ጠቃሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች

 መጽሐፍ ቅዱስ፣ በምንጨነቅበት ወቅት የሚረዱን ብዙ አስተማማኝ ምክሮች ይዟል። እስቲ ሦስት ምሳሌዎችን እንመልከት።

  1.  1. “ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ፤ ምክንያቱም ነገ የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉት። እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለው።”—ማቴዎስ 6:34

     ምን ማለት ነው? ‘እንዲህ ቢሆንስ’ (ወይም ‘እንዲህ ባይሆንስ’) እያልን ስለ ወደፊቱ ጊዜ ከልክ በላይ አለመጨነቃችን ብልህነት ነው። ብዙውን ጊዜ፣ የፈራነው ነገር አይደርስም። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ፣ ሁኔታው ከጠበቅነው በተቃራኒ ጥሩ ሆኖ ይገኛል።

     እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ከዚህ በፊት ‘መጥፎ ነገር ይከሰታል’ ብለህ ፈርተህ በኋላ ላይ እንደጠበቅከው ሳይሆን የቀረበትን ጊዜ አስታውስ። ከዚያም አሁን የሚያስጨንቁህን ነገሮች ገምግም፤ ‘እነዚህ ነገሮች እንደፈራሁት ከባድ ችግር የሚሆኑበት አጋጣሚ ምን ያህል ነው?’ የሚለውን በምክንያታዊነት አስብ።

  2.  2. “ብረት ብረትን እንደሚስል ሁሉ ሰውም ጓደኛውን ይስለዋል።”—ምሳሌ 27:17

     ምን ማለት ነው? የሌሎችን እርዳታ ከጠየቅን፣ ጭንቀታችንን እንድንቋቋም ሊረዱን ይችላሉ። ከራሳቸው የሕይወት ተሞክሮ በመነሳት ጠቃሚ ሐሳቦች ሊያካፍሉን ይችላሉ። ሌላው ቢቀር፣ ያስጨነቀንን ነገር ካላሰብነው አቅጣጫ እንድናየው ሊረዱን ይችላሉ።

     እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ጥሩ ምክር ሊሰጥህ የሚችለው ማን እንደሆነ አስብ፤ ለምሳሌ አንተ ያጋጠመህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞት የሚያውቅ ጓደኛ አለህ? የትኞቹ ነገሮች እንደረዱት፣ የትኞቹ ነገሮች ደግሞ እንዳልጠቀሙት ጠይቀው።

  3.  3. ‘የሚያስጨንቃችሁን [ወይም “የሚያሳስባችሁን፣” የግርጌ ማስታወሻ] ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል።’—1 ጴጥሮስ 5:7

     ምን ማለት ነው? አምላክ በችግር ላይ ላሉ ሰዎች ከልብ ያስባል። የሚያሳስበንን ማንኛውንም ነገር በጸሎት እንድንነግረው ጋብዞናል።

     እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ የሚያስጨንቁህን ነገሮች በዝርዝር ጻፍ። ከዚያም ስለ እነዚህ ነገሮች ወደ አምላክ ጸልይ፤ በምትጸልይበት ጊዜ ስለ እያንዳንዱ ችግር አብራርተህ ተናገር እንዲሁም ችግሩን ለመቋቋም እንዲረዳህ አምላክን ጠይቀው።

የሚያስጨንቅ ነገር የማይኖርበት ጊዜ

 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጭንቀትን ለመቋቋም የሚረዳ ምክር በመስጠት ብቻ አይወሰንም። አሁን የሚያስጨንቁን ነገሮች ለዘላለም የሚወገዱበት ጊዜ በቅርቡ እንደሚመጣ ተስፋ ይሰጠናል። ይህ ተስፋ እውን የሚሆነው እንዴት ነው?

 የአምላክ መንግሥት፣ ለጭንቀት መንስኤ የሚሆኑትን ነገሮች በሙሉ ያስወግዳል። (ራእይ 21:4) እንዲያውም የአምላክ መንግሥት ምድርን በሚገዛበት ወቅት፣ ቀደም ሲል በሕይወታችን ያጋጠሙን አስጨናቂ ነገሮች እንኳ መጥፎ ትዝታ ሆነው አያሠቃዩንም።—ኢሳይያስ 65:17

 “ሰላም የሚሰጠው አምላክ” ወደፊት እንዲህ ዓይነት ሕይወት እንድታገኝ ይፈልጋል። (ሮም 16:20) እንዲህ ሲል ዋስትና ሰጥቶናል፦ “ለእናንተ የማስበውን ሐሳብ በሚገባ አውቀዋለሁ . . . ለእናንተ የማስበው ጥፋትን ሳይሆን ሰላምን እንዲሁም የተሻለ ሕይወትንና ተስፋን ነው።”—ኤርምያስ 29:11

a በዚህ ርዕስ ላይ ስለ ጭንቀት ስንናገር የሕክምና እርዳታ ሊያስፈልገው ስለሚችል ከባድ የጭንቀት ዓይነት እየተናገርን አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ አንድን ሰው በጭንቀት እንዲዋጥ ሊያደርጉ ስለሚችሉ የዕለት ተዕለት ሁኔታዎች እየተናገርን ነው። የጤና እክል የሆነ ከባድ ጭንቀት ያለባቸው ሰዎች፣ የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ሊወስኑ ይችላሉ።—ሉቃስ 5:31