በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ጸሎትህን እንዲሰማ እንዴት መጸለይ ይኖርብሃል?

አምላክ ጸሎትህን እንዲሰማ እንዴት መጸለይ ይኖርብሃል?

ይሖዋ “ጸሎት ሰሚ” አምላክ ነው። (መዝሙር 65:2) በማንኛውም ሰዓትና ቦታ በልባችንም ሆነ ጮክ ብለን እሱን ማነጋገር እንችላለን። ይሖዋ፣ ‘አባት’ ብለን እንድንጠራው ይፈልጋል፤ ደግሞም ከእሱ የተሻለ አባት ልናገኝ አንችልም። (ማቴዎስ 6:9) ይሖዋ ስለሚወደን ጸሎታችን ተሰሚነት እንዲያገኝ ከፈለግን እንዴት መጸለይ እንዳለብን ያስተምረናል።

በኢየሱስ ስም ወደ ይሖዋ አምላክ ጸልይ

“አብን ማንኛውንም ነገር በስሜ ብትጠይቁት ይሰጣችኋል።”​—ዮሐንስ 16:23

ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት ይሖዋ በምስሎች፣ በቅዱሳን፣ በመላእክት ወይም በሞቱ ሰዎች በኩል ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ወደ እሱ እንድንጸልይ እንደሚፈልግ በግልጽ ያሳያሉ። በኢየሱስ ስም ወደ አምላክ ስንጸልይ ኢየሱስ የሚጫወተውን ወሳኝ ሚና እንደተገነዘብን እናሳያለን። ኢየሱስ “በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” በማለት ተናግሯል።—ዮሐንስ 14:6

የልብህን አውጥተህ ተናገር

“ልባችሁን በፊቱ አፍስሱ።”​—መዝሙር 62:8

ወደ ይሖዋ ስንጸልይ አፍቃሪ የሆነን አባት በምናነጋግርበት መንገድ ልናነጋግረው ይገባል። የተጻፈ ነገር እያነበብን ወይም የተሸመደደ ነገር እየደገምን ከመጸለይ ይልቅ በአክብሮት የልባችንን አውጥተን ለአምላክ መንገር ይኖርብናል።

ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ጸልይ

“የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ ይሰማናል።”​—1 ዮሐንስ 5:14

ይሖዋ አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እሱ ለእኛ የሚያደርጋቸውን ነገሮችና እኛ እንድናደርግ የሚፈልጋቸውን ነገሮች አሳውቆናል። ጸሎታችን በአምላክ ዘንድ ተሰሚነት እንዲያገኝ ከፈለግን “ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ” መለመን ይኖርብናል። ይህን ማድረግ እንድንችል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት እሱን በሚገባ ማወቅ ያስፈልገናል። እንዲህ ማድረጋችን አምላክን የሚያስደስት ጸሎት ለማቅረብ ያስችለናል።

ስለ የትኞቹ ነገሮች መጸለይ እንችላለን?

የሚያስፈልጉህን ነገሮች ለማግኘት ጸልይ። አምላክ እንደ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ያሉ መሠረታዊ ፍላጎቶቻችንን እንዲያሟላልን ልንጸልይ እንችላለን። በተጨማሪም ትክክለኛ ውሳኔ ለማድረግ የሚያስችል ጥበብና ፈተናዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ ለማግኘት መጸለይ እንችላለን። አምላክ እምነት እንዲጨምርልን፣ ኃጢአታችንን ይቅር እንዲለንና እንዲረዳን መጸለያችንም አስፈላጊ ነው።—ሉቃስ 11:3, 4, 13፤ ያዕቆብ 1:5, 17

ስለ ሌሎች ሰዎች ጸልይ። አፍቃሪ ወላጆች ልጆቻቸው እርስ በርስ ሲዋደዱ ደስ ይላቸዋል። ይሖዋም በምድር ላይ ያሉ ልጆቹ እርስ በርስ እንዲተሳሰቡ ይፈልጋል። ከዚህ አንጻር ለትዳር ጓደኛችን፣ ለልጆቻችን፣ ለቤተሰባችንና ለወዳጆቻችን መጸለይ ተገቢ ነው። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “አንዳችሁ ለሌላው ጸልዩ” ብሏል።—ያዕቆብ 5:16

ምስጋናህን ግለጽ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፈጣሪያችን ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “ከሰማይ ዝናብ በማዝነብና ፍሬያማ ወቅቶችን በመስጠት እንዲሁም የተትረፈረፈ ምግብ በማቅረብና ልባችሁን በደስታ በመሙላት መልካም ነገር አድርጓል።” (የሐዋርያት ሥራ 14:17) አምላክ ስላደረገልን በርካታ ነገሮች ስናስብ እሱን በጸሎት ለማመስገን እንነሳሳለን። እርግጥ ነው፣ ለአምላክ ያለንን አመስጋኝነት በአኗኗራችንም ልናሳይ ይገባል።—ቆላስይስ 3:15

በትዕግሥት መጸለይህን ቀጥል

አንዳንድ ጊዜ፣ ላቀረብነው ከልብ የመነጨ ጸሎት ቶሎ ምላሽ ባለማግኘታችን ልናዝን እንችላለን። ታዲያ በዚህ ጊዜ አምላክ ለእኛ ግድ እንደሌለው ልናስብ ይገባል? በፍጹም! ቀጥሎ የተጠቀሱት ተሞክሮዎች መጸለያችንን መቀጠላችን አስፈላጊ መሆኑን ያሳያሉ።

በመጀመሪያው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ስቲቭ “ወደ አምላክ ባልጸልይ ኖሮ ገና ድሮ በሕይወቴ ተስፋ እቆርጥ ነበር” በማለት ተናግሯል። ስቲቭ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቱና ሳይታክቱ የመጸለይን አስፈላጊነት መማሩ ለውጥ እንዲያደርግ ረድቶታል። እንዲህ ብሏል፦ “ውድ ወዳጆቼ ላሳዩኝ ፍቅርና ድጋፍ ሁሉ አምላክን በጸሎት አመሰግነዋለሁ። አሁን ከምንጊዜውም ይበልጥ ደስተኛ ነኝ።”

አምላክ ጸሎቴን ይሰማል ብላ መጠበቅ እንደሌለባት ታስብ የነበረችውን የጄኒን ተሞክሮም እንመልከት። “ዋጋ ቢስ እንደሆንኩ የሚሰማኝ ስሜት በጣም ያየለበት ወቅት ነበር፤ በዚህ ወቅት፣ እንዲህ የሚሰማኝ ለምን እንደሆነ መገንዘብ እንድችል እንዲረዳኝ አምላክን ለመንኩት” ብላለች። እንዲህ ማድረጓ የረዳት እንዴት ነው? እንዲህ ብላለች፦ “የሚሰማኝን ስሜት ለአምላክ መናገሬ ለራሴ ሚዛናዊ አመለካከት እንድይዝ ረድቶኛል። ልቤ ቢኮንነኝም አምላክ ግን እንደማይኮንነኝ እንዳስተውል አድርጎኛል። በተጨማሪም ተስፋ እንዳልቆርጥ ብርታት ሰጥቶኛል።” አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ጸሎት ይሖዋ እውን እንዲሆንልኝና እሱን እንደ አፍቃሪ አምላክ፣ አባትና ወዳጅ እንድመለከተው ረድቶኛል። እሱ የሚፈልገውን ነገር ለማድረግ እስከጣርኩ ድረስ ሁሌም ከጎኔ ሆኖ ይረዳኛል።”

ኢሳቤል ልጇ ጄራርድ የአካል ጉዳት እያለበትም በሕይወቱ ደስተኛ እንደሆነ ስትመለከት “አምላክ ከሁሉ በተሻለ መንገድ ጸሎቴን እንደመለሰልኝ ይሰማኛል” ብላለች

ኢሳቤል የተባለች ሴት ያጋጠማትን ሁኔታም እንመልከት። እርጉዝ ሳለች ሐኪሞቿ ልጇ ከባድ እክል ይዞ እንደሚወለድ ነገሯት። ኢሳቤል ይህን ስትሰማ በጣም አዘነች። በወቅቱ አንዳንዶች ጽንሱን እንድታስወርድ መክረዋት ነበር። ኢሳቤል “በጣም ከመጨነቄ የተነሳ የምሞት መስሎኝ ነበር” ብላለች። ታዲያ በዚህ ጊዜ ምን አደረገች? “አምላክ እንዲረዳኝ በተደጋጋሚ ጸለይኩ” ብላለች። ከጊዜ በኋላ ጄራርድ የተባለ ልጅ የወለደች ሲሆን ልጁ የአካል ጉዳት ነበረበት። ኢሳቤል አምላክ ጸሎቷን እንደመለሰላት ይሰማታል? አዎ። በምን መንገድ? ኢሳቤል እንዲህ ብላለች፦ “አሁን 14 ዓመት የሆነው ልጄ የአካል ጉዳት እያለበትም በሕይወቱ ደስተኛ እንደሆነ ስመለከት አምላክ ከሁሉ በተሻለ መንገድ ጸሎቴን እንደመለሰልኝ ይሰማኛል። ልጄ ከይሖዋ አምላክ ያገኘሁት ከሁሉ የላቀ በረከት ነው።”

እንዲህ ያሉ ከልብ የመነጩ አገላለጾች መዝሙራዊው የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ ያስታውሱናል፦ “ይሖዋ ሆይ፣ የዋሆች የሚያቀርቡትን ልመና . . . ትሰማለህ። ልባቸውን ታጸናለህ፤ ደግሞም ትኩረት ትሰጣቸዋለህ።” (መዝሙር 10:17) በእርግጥም ሳናቋርጥ እንድንጸልይ የሚያነሳሱን አጥጋቢ ምክንያቶች አሉን!

ኢየሱስ ያቀረባቸው በርካታ ጸሎቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል በስፋት የሚታወቀው ለደቀ መዛሙርቱ ያስተማራቸው ጸሎት ነው። ከዚህ ጸሎት ምን እንማራለን?