በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

በሕይወቴ የቀረብኝ ነገር እንደሌለ ይሰማኝ ነበር

በሕይወቴ የቀረብኝ ነገር እንደሌለ ይሰማኝ ነበር
  • የትውልድ ዘመን፦ 1982

  • የትውልድ አገር፦ ፖላንድ

  • የኋላ ታሪክ፦ ዓመፀኛና የዕፅ ሱሰኛ የነበረ እንዲሁም ትልቅ ቦታ ላይ ለመድረስ ምኞት የነበረው

የቀድሞ ሕይወቴ፦

የተወለድኩት ፖላንድ ውስጥ በምትገኝ ትንሽ ከተማ ውስጥ ሲሆን ቦታው ከጀርመን ድንበር ብዙም አይርቅም። አካባቢው በእርሻ እና በዛፎች የተከበበ ሲሆን በዚያ ሰላማዊ ሕይወት እኖር ነበር። አፍቃሪ የሆኑት ወላጆቼ ጥሩ ሰውና ጎበዝ ተማሪ እንድሆን እንዲሁም ጥሩ ሥራ እንድይዝ ያበረታቱኝ ነበር።

ዩኒቨርስቲ ገብቼ ሕግ ለመማር ወደ ቭሮትዝዎቭ ከተማ በሄድኩ ጊዜ በሕይወቴ ውስጥ ችግሮች መከሰት ጀመሩ። ከወላጆቼ ርቄ ከሄድኩ በኋላ ከመጥፎ ልጆች ጋር ጓደኝነት ገጠምኩ። ምንጊዜም ለእግር ኳስ ፍቅር ነበረኝ፤ ይሁንና በዚያ ያገኘኋቸው አዳዲስ ጓደኞቼ ባሳደሩብኝ ተጽዕኖ የተነሳ ቀንደኛ ደጋፊ ሆንኩ። እኔ የምደግፈው ቡድን የሚመጣው ከዋርሶ ነው፤ በተለይ ቅዳሜ እና እሁድ ግጥሚያ በሚኖራቸው ጊዜ በሚሄዱበት ቦታ ሁሉ ተከትያቸው እሄድ ነበር። አብረናቸው በምንጓዝበት ወቅት በጣም እንጠጣ፣ ዕፅ እንወስድ አልፎ አልፎም ከተጋጣሚ ቡድን ደጋፊዎች ጋር እንደባደብ ነበር። ይህን ሁኔታ የዕለት ተዕለት ሕይወት ከሚያስከትለው ውጥረት ማምለጫ አድርጌ እመለከተው የነበረ ቢሆንም ፖሊስ ቢይዘኝ የሕግ ሙያዬን ሊያበላሽብኝ እንደሚችል አውቅ ነበር።

እኔና ጓደኞቼ የምሽት ክለቦችና ጭፈራ ቤቶች መሄድ እንወድ ነበር። እዚያ ከሄድን በኋላ አብዛኛውን ጊዜ መንገድ ላይ እንደባደባለን። ፖሊሶች በተደጋጋሚ ይዘውኛል፤ ሆኖም ሕግ ፊት ቀርቤ የከፋ ችግር ውስጥ ከመግባት ምንጊዜም አመልጥ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የምለቀቀው ጉቦ ሰጥቼ ነው። በወቅቱ በሕይወቴ የቀረብኝ ነገር እንደሌለ ይሰማኝ ነበር፤ ውስጤ ግን የማደርገው ነገር ትክክል እንዳልሆነ ይነግረኛል። በመሆኑም የሕሊና እረፍት ለማግኘት ስል በየሳምንቱ እሁድ ቤተ ክርስቲያን እሄድ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

በ2004 ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ቤቴ መጥተው አነጋገሩኝ፤ እኔም ከእነሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለመወያየት ፈቃደኛ ሆንኩ። እውነተኛ ክርስቲያን መሆን ምን ማለት እንደሆነ እየተረዳሁ ስመጣ ሕሊናዬ እረፍት ይነሳኝ ጀመር። ከመጠን በላይ መጠጣት፣ ዕፅ መውሰድ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ከማይከተሉ ሰዎች ጋር ያለኝን ግንኙነት ማቋረጥ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። ከዚህ በተጨማሪ የጠበኝነትና የዓመፀኝነት ባሕሪዬን ማስተካከል እንደሚያስፈልገኝ ተገነዘብኩ። ለውጥ ማድረግ እንዳለብኝ ብረዳም መጥፎ ሕይወት ውስጥ ተዘፍቄ ነበር።

በሕይወቴ ላይ ለውጥ ለማድረግ የቆረጥኩት፣ አንድ ቀን ማታ ከስምንት ሰዎች ጋር በተጣላሁ ጊዜ ነበር። መንገድ ላይ ወድቄ ሰዎቹ በቡጢና በእርግጫ አናቴን ሲመቱኝ አስታውሳለሁ። በዚያን ወቅት የምሞት ስለመሰለኝ እንዲህ ብዬ ጸለይኩ፦ “ይሖዋ ሆይ፣ ቃልህን ባለማክበሬ ይቅር በለኝ። በሕይወት ከተረፍኩ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናትና ሕይወቴን ለማስተካከል ቃል እገባለሁ።” የሚገርመው ነገር ከሞት ተረፍኩ። በመሆኑም ቃል በገባሁት መሠረት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ።

በ2006 ወደ እንግሊዝ ሄድኩ። ወደዚያ የሄድኩበት ዓላማ በቂ ገንዘብ ካጠራቀምኩ በኋላ ወደ ፖላንድ ተመልሼ ከፍተኛ የሕግ ዲግሪ ለመያዝ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቴን ስቀጥል አንድ ጥቅስ ትልቅ ለውጥ እንዳደርግ አነሳሳኝ። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ስለ ጌታዬ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ከሚገልጸው የላቀ ዋጋ ያለው እውቀት አንጻር ሁሉንም ነገር እንደ ኪሳራ እቆጥረዋለሁ። ለእሱ ስል ሁሉንም ነገር አጥቻለሁ፤ ያጣሁትንም ነገር ሁሉ እንደ ጉድፍ እቆጥረዋለሁ፤ ይህም ክርስቶስን አገኝ ዘንድ ነው።” (ፊልጵስዩስ 3:8) ሐዋርያው ጳውሎስ ልክ እንደ እኔ ሕግ ተምሯል፤ እንዲሁም በጣም ዓመፀኛ ሰው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 8:3) ሆኖም ከዚያ የተሻለ ሕይወት እንዳለ ተገነዘበ፦ ይህም አምላክን ማገልገልና አቅሙ በሚፈቅድለት መጠን የኢየሱስን ምሳሌ መከተል ነው። ጳውሎስ በተወው ምሳሌ ላይ ማሰላሰሌ ጥሩ ሥራም ሆነ የኃይለኝነት ባሕርይን ማንጸባረቅ ደስታ የሚያስገኙ ነገሮች አለመሆናቸውን እንድገነዘብ ረዳኝ። ጳውሎስ ለውጥ ማድረግ ከቻለ እኔም መለወጥ እንደምችል ጽኑ እምነት አደረብኝ። በመሆኑም እንግሊዝ ውስጥ ለመቆየት የወሰንኩ ከመሆኑም ሌላ ተጨማሪ የሕግ ዲግሪ ለመያዝ ያወጣሁትን ግብ ተውኩት።

ስለ ይሖዋ እያወቅኩ በሄድኩ መጠን ይበልጥ ወደ እሱ እየቀረብኩ እንደሆነ ተሰማኝ። ይሖዋ ከልብ ለመለወጥ ጥረት የሚያደርጉ ሰዎችን ይቅር ለማለት የገባው ቃል ልቤን ነካው። (የሐዋርያት ሥራ 2:38) በ1 ዮሐንስ 4:16 ላይ በሚገኘው “አምላክ ፍቅር ነው” በሚለው ሐሳብ ላይ ሳሰላስል አምላክ ዓመፅን ለምን እንደሚጠላ ተገነዘብኩ።

የይሖዋ ምሥክሮችን ያቀፈው ደስተኛ የወንድማማች ማኅበር አባል የመሆን ፍላጎት አደረብኝ

በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች የሚያሳዩት ምግባር ልቤን ነካው። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙትን የላቁ የሥነ ምግባር መመሪያዎች አክብረው ለመኖር ጥረት እንደሚያደርጉ በግልጽ ማየት ችዬ ነበር። እነሱ ያሉበት ደስተኛ የወንድማማች ማኅበር አባል የመሆን ፍላጎት አደረብኝ። በሕይወቴ ውስጥ አንዳንድ ያታገሉኝና ለውጥ ማድረግ የጠየቁብኝ ነገሮች ቢኖሩም በ2008 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።

እኔና ኤስተር የፖላንድ ቋንቋ ተናጋሪዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስተማራችን እውነተኛ ደስታ አስገኝቶልናል

ያገኘሁት ጥቅም፦

ትልቅ ቦታ ላይ ለመድረስ የምጓጓ፣ ዓመፀኛ፣ የዕፅ ሱሰኛ፣ ኃይለኛ ጠጪና የእግር ኳስ አፍቃሪ የነበርኩ ብሆንም መጽሐፍ ቅዱስ መማሬ ለውጥ አድርጌ ለሰዎች የአምላክን ቃል በማስተማር የምደሰት የአምላክ አገልጋይ እንድሆን አስችሎኛል። አሁንም ቢሆን እግር ኳስ ማየት ያስደስተኛል፤ ሆኖም ሚዛኔን ለመጠበቅ ቆርጫለሁ።

ኤስተር የተባለች ይሖዋን የምታመልክ ቆንጆ እህት ያገባሁ ሲሆን አስደሳች ትዳርም አለኝ። እኔና ኤስተር በሰሜናዊ ምዕራብ እንግሊዝ የሚኖሩ የፖላንድ ቋንቋ ተናጋሪዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስተማራችን እውነተኛ ደስታ አስገኝቶልናል። በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥልቅ እርካታ አግኝቻለሁ፤ ንጹሕ ሕሊና ያለኝ ከመሆኑም ሌላ አርኪና ትርጉም ያለው ሕይወት እየመራሁ ነው።