በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በእምነታቸው ምሰሏቸው | ጢሞቴዎስ

‘በጌታ ልጄ የሆነው የምወደውና ታማኝ የሆነው ጢሞቴዎስ’

‘በጌታ ልጄ የሆነው የምወደውና ታማኝ የሆነው ጢሞቴዎስ’

ጢሞቴዎስ ቀዬውን ትቶ ወደ ሩቅ አገር ለመሄድ ጉዞ ጀምሯል፤ በዚህ ወቅት ግን ሙሉ በሙሉ ትኩረቱ ያረፈው ከፊቱ በሚጠብቀው ነገር ላይ ነው። የጉዞ ጓደኞቹ፣ ጢሞቴዎስ በደንብ የሚያውቃቸውን የእርሻ ቦታዎች እያቋረጡ ከፊት ከፊቱ እየሄዱ ነው። ሸለቆ ውስጥ ባለ ሜዳ፣ በአነስተኛ ኮረብታ አናት ላይ ከምትገኘው የልስጥራ ከተማ ቀስ በቀስ እየራቁ ሄዱ። ጢሞቴዎስ እናቱንና አያቱን ተሰናብቶ ሲሄድ ፊታቸው ላይ ይነበብ የነበረውን የኩራት ስሜት አስታውሶ ፈገግ አለ፤ እናቱና አያቱ ይህን ያደረጉት እንባቸውን ተቆጣጥረው እንደሚሆን ግልጽ ነው። ታዲያ ለመጨረሻ ጊዜ ዞሮ ይሰናበታቸው ይሆን?

ሐዋርያው ጳውሎስ አልፎ አልፎ ወደ ጢሞቴዎስ እየዞረ ፈገግ በማለት ያበረታታዋል። ጳውሎስ ወጣቱ ጢሞቴዎስ አሁንም ቢሆን በተወሰነ መጠን ያለበትን ዓይናፋርነት ማሸነፍ እንደሚኖርበት ቢያውቅም ይህ ወጣት ባሳየው ቅንዓት በጣም ተደስቷል። ጢሞቴዎስ ገና ልጅ እግር ነው፤ ምናልባትም በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ወይም በሃያዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኝ ወጣት ሳይሆን አይቀርም። ይህም ሆኖ ለሐዋርያው ጳውሎስ ከፍተኛ አክብሮትና ፍቅር አለው። በአሁኑ ሰዓት ጢሞቴዎስ ከቤቱ ወጥቶ ብርቱና ታማኝ ከሆነው ከዚህ ሰው ጋር በብዙ መቶ ኪሎ ሜትሮች ወደሚርቅ ቦታ እየተጓዘ ነው። በእግርም ሆነ በመርከብ ብዙ መጓዝ ይጠበቅባቸዋል፤ በጉዟቸው ላይ ደግሞ የሚያጋጥሟቸውን በርካታ አደገኛ ሁኔታዎች መጋፈጥ ይኖርባቸዋል። ጢሞቴዎስ ከዚህ በኋላ ወደ ቤቱ ይመለስ አይመለስ በእርግጠኝነት የሚያውቀው ነገር የለም።

ይህ ወጣት ይህን የሕይወት ጎዳና እንዲመርጥ ያነሳሳው ምንድን ነው? እንዲህ ዓይነት መሥዋዕትነት ለመክፈል የተነሳሳው ምን ወሮታ ለማግኘት ነው? የጢሞቴዎስ እምነት የእኛን እምነት ሊገነባ የሚችለው እንዴት ነው?

“ከጨቅላነትህ ጀምሮ”

ሁለት ወይም ሦስት ዓመት ወደኋላ ተመልሰን፣ ጢሞቴዎስ የትውልድ ከተማው እንደሆነች በሚታመነው በልስጥራ እንዳለ አድርገን እናስብ። ልስጥራ ውኃ እንደልብ በሚገኝበት ሸለቆ ውስጥ ያለችና ገለል ብላ የምትገኝ የገጠር ከተማ ናት። ነዋሪዎቹ ግሪክኛ እንደሚችሉ ይገመታል፤ ይሁንና አሁንም ቢሆን የሚግባቡት በአካባቢው በሚነገረው በሊቃኦንያ ቋንቋ ነው። ይህች ሰላማዊ ከተማ አንድ ቀን በሁከት ታመሰች። ሚስዮናውያን የሆኑት ክርስቲያኖቹ ሐዋርያው ጳውሎስና የጉዞ ጓደኛው በርናባስ ብዙም ከማትርቀው ኢቆንዮን ከምትባል ተለቅ ያለች ከተማ ወደ ልስጥራ መጥተዋል። በአደባባይ እየሰበኩ ሳሉ ጳውሎስ አንድ አካል ጉዳተኛ ተመለከተ፤ ግለሰቡ ደግሞ እውነተኛ እምነት እንዳለው አሳየ። በመሆኑም ጳውሎስ ሰውየውን በተአምር ፈወሰው!—የሐዋርያት ሥራ 14:5-10

ከተከሰተው ሁኔታ መረዳት እንደሚቻለው በርካታ የልስጥራ ነዋሪዎች፣ ድሮ ድሮ አማልክት ሰው መስለው ወደዚያ ይመጡ እንደነበር በአካባቢያቸው በሚነገሩት አፈ ታሪኮች ያምናሉ። በመሆኑም ሰዎቹ ጳውሎስን ከሄርሜስ ጋር፣ በርናባስን ደግሞ ከዙስ ጋር አመሳሰሏቸው! እነዚህ ሁለት ትሑት ክርስቲያኖች ሰዎቹ መሥዋዕት እንዳያቀርቡላቸው ለመከልከል ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ጠይቆባቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 14:11-18

ይሁንና ጥቂት የልስጥራ ነዋሪዎች፣ አፈ ታሪክ የወለዳቸው አረማውያን አማልክት እንደመጡ አልተሰማቸውም፤ ለእነሱ ያዩት ነገር በእውን የተፈጸመና እጅግ የሚያስደንቅ ክስተት ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ አማኝ ያልሆነ ግሪካዊ * ባል የነበራት ኤውንቄ የምትባል አንዲት አይሁዳዊና እናቷ ሎይድ፣ ወንጌላውያኑ ጳውሎስና በርናባስ ያስተማሩትን ትምህርት በከፍተኛ ጉጉትና በደስታ አዳምጠዋል። በእርግጥም፣ እያንዳንዱ ታማኝ አይሁዳዊ ለመስማት የሚጓጓው ምሥራች ደረሳቸው። አዎን፣ የመሲሑን መምጣትም ሆነ ስለ እሱ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የሰፈሩት በርካታ ትንቢቶች መፈጸማቸውን ተረዱ!

ጢሞቴዎስ፣ ጳውሎስ እሱ ወደሚኖርበት ከተማ በመምጣቱ ሕይወቱ ምን ያህል እንደተለወጠ አስብ። ጢሞቴዎስ ለዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ፍቅር እንዲያዳብር ‘ከጨቅላነቱ ጀምሮ’ ትምህርት ሲሰጠው ቆይቷል። (2 ጢሞቴዎስ 3:15) እንደ እናቱና ሴት አያቱ ሁሉ ጢሞቴዎስም ጳውሎስና በርናባስ ስለ መሲሑ የተናገሩት ነገር እውነት መሆኑን መገንዘብ ችሎ ነበር። ጳውሎስ ስለፈወሰው እግሩ ሽባ የሆነ ሰው ደግሞ አስብ። ጢሞቴዎስ ከልጅነቱ አንስቶ ሰውየውን በልስጥራ መንገዶች ላይ ነጋ ጠባ ሳያየው አልቀረም። አሁን ግን ይህ ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲራመድ እያየ ነው! በመሆኑም ኤውንቄና ሎይድ እንዲሁም ጢሞቴዎስ ክርስትናን መቀበላቸው አያስገርምም። ዛሬም አያቶችና ወላጆች ከሎይድና ከኤውንቄ ብዙ ነገር መማር ይችላሉ። አንተስ በወጣቶች ላይ በጎ ተጽዕኖ ማሳደር ትችላለህ?

“በብዙ መከራ”

በልስጥራ ክርስትናን ተቀብለው ደቀ መዛሙርት የሆኑት ሰዎች የክርስቶስ ተከታዮች የሚጠብቃቸውን ተስፋ ሲሰሙ እጅግ ሳይደሰቱ አይቀሩም። ይሁንና ደቀ መዝሙር መሆን ዋጋ እንደሚያስከፍላቸውም ተረድተዋል። ከኢቆንዮንና ከአንጾኪያ ወደ ልስጥራ የመጡ አክራሪ አይሁዳውያን በቀላሉ የሚነዳውን ሕዝብ በጳውሎስና በበርናባስ ላይ አሳመፁ። ብዙም ሳይቆይ፣ በቁጣ የገነፈሉ ሰዎች ጳውሎስን እያሳደዱ የድንጋይ ናዳ አወረዱበት፤ ከዚህም የተነሳ መሬት ላይ ወደቀ። ከዚያም ሰዎቹ ከከተማዋ ውጪ ጎትተው ጣሉት፤ የሞተ ስለመሰላቸውም ትተውት ሄዱ።—የሐዋርያት ሥራ 14:19

ይሁን እንጂ በልስጥራ የነበሩት ደቀ መዛሙርት ጳውሎስ የወደቀበት ቦታ መጥተው ከበቡት። ጳውሎስ አለመሞቱን ሲያውቁ እንዲያውም ከተነሳ በኋላ በድፍረት ወደ ልስጥራ ተመልሶ መግባቱን ሲያዩ ከፍተኛ እፎይታ ተሰምቷቸው መሆን አለበት! በማግስቱ እሱና በርናባስ የስብከቱ ሥራቸውን ለመቀጠል ወደ ደርቤ ሄዱ። በዚያም አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ካፈሩ በኋላ በሕይወታቸው ቆርጠው ወደ ልስጥራ ተመለሱ። ምን ለማድረግ? ዘገባው “በእምነት ጸንተው እንዲኖሩ በማበረታታት ደቀ መዛሙርቱን አጠናከሩ” ይላል። ጳውሎስና በርናባስ በልስጥራ ያሉ ክርስቲያኖችን ወደፊት የሚጠብቃቸውን ክብራማ ተስፋ ለማግኘት አሁን የሚከፍሉት መሥዋዕትነት እንደሚክሳቸው በሚያስተምሩበት ጊዜ ወጣቱ ጢሞቴዎስ አፍጥጦ ሲያዳምጣቸው ይታይህ። እነሱም “ወደ አምላክ መንግሥት ለመግባት በብዙ መከራ ማለፍ አለብን” አሏቸው።—የሐዋርያት ሥራ 14:20-22

ጢሞቴዎስ የሐዋርያው ጳውሎስን ትምህርት በአድናቆት ተቀብሏል

ጢሞቴዎስ፣ ጳውሎስ ምሥራቹን ለሌሎች ለማካፈል ሲል የደረሰበትን መከራ በቆራጥነት እየተጋፈጠ ከተናገረው ቃል ጋር በሚስማማ መንገድ እንደኖረ የማየት አጋጣሚ አግኝቷል። ስለዚህ ጢሞቴዎስ የጳውሎስን ምሳሌ የሚከተል ከሆነ የልስጥራ ነዋሪዎች እንደሚቃወሙት ተረድቷል፤ የገዛ አባቱም ቢሆን ሊቃወመው ይችላል። ይሁንና ጢሞቴዎስ እንዲህ ዓይነቱ አስፈሪ ሁኔታ አምላክን ለማገልገል ባደረገው ውሳኔ ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድርበት አልፈቀደም። በዛሬው ጊዜም ጢሞቴዎስን የመሰሉ ብዙ ወጣቶች አሉ። እነሱም የድፍረትና የብርታት ምንጭ የሚሆኗቸውንና ጠንካራ እምነት ያላቸውን ሰዎች ጓደኞች አድርገው በጥበብ ይመርጣሉ። ደግሞም የሚደርስባቸው ተቃውሞ እውነተኛውን አምላክ ከማገልገል ወደ ኋላ እንዲያደርጋቸው አይፈቅዱም!

‘ወንድሞች ስለ መልካም ምግባሩ መሥክረውለታል’

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ጳውሎስ በድጋሚ ወደ ልስጥራ የመጣው ከሁለት ወይም ከሦስት ዓመት በኋላ ሳይሆን አይቀርም። ጳውሎስ (በዚህ ጊዜ የመጣው ከሲላስ ጋር ነው) ልስጥራ ሲደርስ የጢሞቴዎስ ቤተሰቦች ምን ያህል ተደስተው እንደሚሆን ገምት። በዚህ ወቅት ጳውሎስም እንደሚደሰት ምንም ጥያቄ የለውም። በልስጥራ የዘራው የእውነት ዘር ምን ውጤት እንዳስገኘ በገዛ ዓይኑ እያየ ነው። ታማኝ ክርስቲያን ለመሆን ከበቁት መካከል ሎይድና ሴት ልጇ ኤውንቄ ይገኙበታል፤ ጳውሎስ እነዚህ ሴቶች የሚያሳዩትን “ግብዝነት የሌለበት እምነት” በከፍተኛ አድናቆት ተመልክቷል። (2 ጢሞቴዎስ 1:5) ወጣቱ ጢሞቴዎስስ ምን ላይ ደርሶ ይሆን?

ጳውሎስ ካለፈው ጉብኝቱ ወዲህ ይህ ወጣት የሚደነቅ ብስለት እንዳዳበረ ማየት ችሏል። በልስጥራ ብቻ ሳይሆን በስተ ሰሜን ምሥራቅ 32 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በኢቆንዮን ያሉ ወንድሞችም ስለ ጢሞቴዎስ ‘መልካም ምግባር መሥክረዋል።’ (የሐዋርያት ሥራ 16:2) እንዲህ ዓይነት መልካም ስም ሊያተርፍ የቻለው እንዴት ነው?

የጢሞቴዎስ እናትና ሴት አያት ‘ከቅዱሳን መጻሕፍት’ ላይ ‘ከጨቅላነቱ ጀምሮ’ ያስተማሩት ትምህርት ለወጣቶች የሚጠቅም ገንቢና ውጤታማ ምክር ይዟል። (2 ጢሞቴዎስ 3:15) በዚህ ረገድ “በወጣትነትህ ጊዜ ታላቁን ፈጣሪህን አስብ” የሚለውን ምክር ምሳሌ አድርገን መጥቀስ እንችላለን። (መክብብ 12:1) ጢሞቴዎስ ክርስትናን ከተቀበለ በኋላ ለዚህ ምክር ልዩ ትኩረት ሰጥቷል። ታላቁን ፈጣሪውን ለማሰብ የሚያስችለው ከሁሉ የተሻለ መንገድ የአምላክ ልጅ ስለሆነው ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን ምሥራች ለሌሎች መስበክን እንደሚጨምር ተገንዝቧል። በጊዜ ሂደት፣ ጢሞቴዎስ እንቅፋት የሚሆንበትን በተፈጥሮ የወረሰውን ዓይናፋርነት ማሸነፍ ችሏል፤ እንዲሁም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገልጸውን ምሥራች ለሌሎች ለማወጅ ድፍረት አዳብሯል።

በጉባኤ ውስጥ አመራር የሚሰጡ ወንድሞች፣ ጢሞቴዎስ ያደረገውን እድገት ማስተዋል ችለዋል። ይህ ወጣት የጉባኤውን አባላት ለማነጽና ለማበረታታት የሚያደርገውን ጥረት በመመልከታቸው ልባቸው እንደተነካ ጥርጥር የለውም። ይሁንና ቁም ነገሩ ያለው ይሖዋ የጢሞቴዎስን እድገት መመልከቱ ላይ ነው። አምላክ በመንፈስ መሪነት ስለ ጢሞቴዎስ ትንቢት እንዲነገር አደረገ፤ ይህም ወደፊት ለብዙ ጉባኤዎች የሚሰጠውን አገልግሎት የተመለከተ ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ ልስጥራን በጎበኘበት ወቅት ጢሞቴዎስ ለሚስዮናዊ አገልግሎቱ ጥሩ የጉዞ አጋር ሊሆነው እንደሚችል ተገነዘበ። በልስጥራ ያሉ ወንድሞችም በዚህ ሐሳብ ተስማሙ። በመሆኑም በዚህ ወጣት ላይ እጃቸውን የጫኑ ሲሆን እንዲህ ማድረጋቸው ይሖዋ አምላክን ለማገልገል ልዩ ሹመት እንደተሰጠው ያሳያል።—1 ጢሞቴዎስ 1:18፤ 4:14

ጢሞቴዎስ ይህ ታላቅ አደራና ኃላፊነት ሲሰጠው በድንጋጤ እንደተዋጠና ብቁ አይደለሁም የሚል ስሜት እንዳደረበት መገመት አያዳግትም። ሆኖም ለመሄድ ተዘጋጅቷል። * ይሁንና አማኝ ያልሆነው የጢሞቴዎስ አባት፣ ልጁ ተጓዥ አገልጋይ እንዲሆን መመረጡን ሲሰማ ምን ተሰምቶት ይሆን? ምናልባትም የልጁን የወደፊት ሕይወት በተመለከተ ያቀዳቸው ብዙ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። የጢሞቴዎስ እናትና አያትስ ምን ተሰምቷቸው ይሆን? በአንድ በኩል ኩራት ቢሰማቸውም በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ወጣት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ያደረባቸውን ስጋት ለመደበቅ ሞክረው ይሆን? ይሄ የሚጠበቅ ነገር ነው።

ያም ሆነ ይህ ጢሞቴዎስ አብሯቸው እንደሄደ በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን። በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው አንድ ቀን ጠዋት ላይ ጢሞቴዎስ ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር በመጓዝ የሚያከናውነውን የሚስዮናዊነት ሕይወት ጀመረ። ጠጠሩን እንዲሁም ሣሩን እየረገጠ አንድ እርምጃ በተራመደ ቁጥር በልስጥራ ካለው ቤቱ ይባስ እየራቀ፣ ወደማያውቀው አገር ደግሞ ይበልጥ እየቀረበ ነው። ሦስቱ ሰዎች ቀኑን ሙሉ ሲጓዙ ውለው ኢቆንዮን ደረሱ። ከዚያም ጳውሎስና ሲላስ በኢየሩሳሌም ካለው የበላይ አካል በቅርቡ የደረሷቸውን መመሪያዎች የሚያስተላልፉበትን መንገድና በኢቆንዮን ያሉትን ክርስቲያኖች እምነት ለመገንባት የሚያደርጉትን ጥረት ጢሞቴዎስ በትኩረት መከታተል ጀመረ። (የሐዋርያት ሥራ 16:4, 5) ይህ ግን የሥራው መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ አይደለም።

ሚስዮናውያኑ በገላትያ ያሉትን ጉባኤዎች ከጎበኙ በኋላ ሮማውያን ከገነቧቸው ሰፋፊ ጥርጊያ መንገዶች ወጥተው የተንጣለሉትን የፍርግያ አምባዎች በማቋረጥ በመጀመሪያ ወደ ሰሜን፣ ከዚያም ወደ ምዕራብ አቅጣጫ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ተጓዙ። እንደ ወትሮው ሁሉ አምላክ በቅዱስ መንፈሱ የሚሰጣቸውን አመራር በመከተል ወደ ጥሮአስ ከሄዱ በኋላ መርከብ ተሳፍረው ወደ መቄዶንያ አመሩ። (የሐዋርያት ሥራ 16:6-12) በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ወጣቱ ጢሞቴዎስ በጣም እንደሚጠቅማቸው ተገነዘበ። ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ከሲላስ ጋር በቤርያ ትቶት መሄድ ችሏል። (የሐዋርያት ሥራ 17:14) እንዲያውም ይህን ወጣት ወደ ተሰሎንቄ ለብቻው ልኮታል። በዚያም ጢሞቴዎስ፣ ምሳሌ አድርጎ በትኩረት ሲከታተላቸው የነበሩትን ወንጌላውያን አርዓያ በመከተል ታማኝ የሆኑትን የጉባኤውን አባላት እምነት አጠናከረ።—1 ተሰሎንቄ 3:1-3

ጳውሎስ ከጊዜ በኋላ ጢሞቴዎስን በተመለከተ “ስለ እናንተ ጉዳይ ከልብ የሚጨነቅ እንደ እሱ ያለ በጎ አመለካከት ያለው ሌላ ማንም የለኝም” ሲል ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 2:20) ጢሞቴዎስ እንዲህ ዓይነት ስም ሊያተርፍ የቻለው በአጋጣሚ አይደለም። ጢሞቴዎስ እንዲህ ሊባልለት የቻለው ትጉ ሠራተኛ በመሆኑ፣ በትሕትና በማገልገሉና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር በታማኝነት በመጽናቱ ነው። ጢሞቴዎስ በዛሬው ጊዜ ላሉ ወጣቶች ግሩም ምሳሌ ነው! መልካም ስም የማትረፍህ ጉዳይ በአብዛኛው የተመካው በአንተ ላይ መሆኑን አትዘንጋ። ወጣት ከሆንክ በሕይወትህ ውስጥ ይሖዋ አምላክን በማስቀደም እንዲሁም ሌሎችን በደግነትና በአክብሮት በመያዝ መልካም ስም ማትረፍ የምትችልበት ግሩም አጋጣሚ አለህ።

“ወደ እኔ ቶሎ ለመምጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ”

ጢሞቴዎስ ከወጣትነት ዕድሜው አንስቶ ሕይወቱን በክርስቲያናዊ አገልግሎት አሳልፏል

በ14 ዓመታት ውስጥ፣ ጢሞቴዎስ ጓደኛው ከሆነው ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር አብሮ በመሥራት ብዙ ጊዜ አሳልፏል። ጳውሎስ ሥራውን ሲያከናውን ያጋጠመውን መከራም ሆነ ደስታ አብዛኛውን ጊዜ ከጎኑ ሳይለይ ተጋርቷል። (2 ቆሮንቶስ 11:24-27) እንዲያውም በሆነ ወቅት ላይ ጢሞቴዎስ በእምነቱ ምክንያት ታስሮ ነበር። (ዕብራውያን 13:23) በተጨማሪም ጳውሎስ ለክርስቲያን ወንድሞቹና እህቶቹ ያለውን ከልብ የመነጨ ፍቅርና ጥልቅ አሳቢነት አንጸባርቋል። በመሆኑም ጳውሎስ ‘እንባህን አስታውሳለሁ’ በማለት ጽፎለታል። (2 ጢሞቴዎስ 1:4) እንደ ጳውሎስ ሁሉ ጢሞቴዎስም ወንድሞችንና እህቶችን ማበረታታትና ማጽናናት ይችል ዘንድ ስሜታቸውን በመጋራት ‘ከሚያለቅሱ ጋር ሳያለቅስ’ አልቀረም። (ሮም 12:15) እኛም እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ለማዳበር ጥረት እናድርግ።

ከጊዜ በኋላ ጢሞቴዎስ የተዋጣለት ክርስቲያን የበላይ ተመልካች መሆኑ የሚያስደንቅ ነገር አይደለም። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ፣ ጉባኤዎችን በመጎብኘት እንዲያጠናክርና እንዲያበረታታ ብቻ ሳይሆን የጉባኤ ሽማግሌና አገልጋይ ሆነው ለማገልገል ብቃቱን ያሟሉ ወንዶችን እንዲሾምም ኃላፊነት ሰጥቶታል።—1 ጢሞቴዎስ 5:22

ጳውሎስ ጢሞቴዎስን በጣም ይወደው ስለነበረ ለዚህ ወጣት ጠቃሚ የሆነ ብዙ መመሪያና አባታዊ ምክር ሰጥቶታል። ጳውሎስ፣ መንፈሳዊ ስጦታዎቹን እንዲያጎለብትና ቀጣይ እድገት በማድረግ እየተሻሻለ እንዲሄድ ጢሞቴዎስን መክሮታል። (1 ጢሞቴዎስ 4:15, 16) ወጣት በመሆኑ ምናልባትም በተፈጥሮ በወረሰው ዓይናፋርነት የተነሳ ለትክክለኛው ነገር ጽኑ አቋም ከመያዝ ወደኋላ ማለት እንደሌለበት በመንገር ጳውሎስ ጢሞቴዎስን አበረታቶታል። (1 ጢሞቴዎስ 1:3፤ 4:6, 7, 11, 12) አልፎ ተርፎም ጳውሎስ ይህ ወጣት በየጊዜው ለሚነሳበት በሽታ (በተደጋጋሚ የሚነሳበት የሆድ ሕመም ሊሆን ይችላል) ምን ማድረግ እንዳለበት ምክር ሰጥቶታል።—1 ጢሞቴዎስ 5:23

ጳውሎስ በቅርቡ ሕይወቱ እንደሚያልፍ ተገንዝቧል፤ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው የሞት ቅጣት ከፊቱ ይጠብቀው ነበር። ለጢሞቴዎስ በመንፈስ መሪነት የጻፈውን የመጨረሻ ደብዳቤ ላከለት። ደብዳቤው “ወደ እኔ ቶሎ ለመምጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ” የሚል ልብ የሚነካ ሐሳብ ይዟል። (2 ጢሞቴዎስ 4:9) ጳውሎስ ጢሞቴዎስን በጣም ይወደዋል፤ እንዲያውም ስለ እሱ ‘በጌታ ልጄ የሆነው የምወደውና ታማኝ የሆነው’ በማለት ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 4:17) ጳውሎስ የሕይወቱ ማብቂያ በተቃረበበት ወቅት ይህ ጓደኛው ከጎኑ እንዲሆን መፈለጉ ምንም አያስደንቅም! ሁላችንም ‘ሰዎች ችግር ሲደርስባቸው መጽናኛ ለማግኘት ወደ እኔ ይመጣሉ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው።

ጢሞቴዎስ፣ ጳውሎስን ገና በሕይወት እያለ አግኝቶት ይሆን? የምናውቀው ነገር የለም። ይሁንና ጢሞቴዎስ ለጳውሎስም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ማጽናኛና ማበረታቻ ለመስጠት የተቻለውን ሁሉ ያደርግ እንደነበረ በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን። ጢሞቴዎስ፣ “አምላክን የሚያከብር” ከሚለው የስሙ ትርጉም ጋር ተስማምቶ ኖሯል። ደግሞም ወጣትም ሆን አረጋዊ፣ ሁላችንም ልንከተለው የሚገባ ድንቅ የእምነት ምሳሌ ይሆነናል።

^ አን.9 በዚህ እትም ላይ የሚገኘውን “ይህን ያውቁ ኖሯል?” የሚለውን ዓምድ ተመልከት።

^ አን.20 ጢሞቴዎስ፣ ጳውሎስ ባቀረበው ሐሳብ በመስማማት ለመገረዝ እንኳ ሳይቀር ፈቃደኛ ሆኗል፤ ጳውሎስ እንዲህ ያደረገው መገረዝ ክርስቲያኖች ሊያሟሉት የሚገባ ብቃት በመሆኑ ሳይሆን ምሥራቹን የሚሰብኩላቸው አይሁዳውያን፣ አባቱ አሕዛብ የሆነው ይህ ወጣት አብሯቸው በመሆኑ ቅር የሚሰኙበት ነገር እንዳይፈጠር ሲል ነው።—የሐዋርያት ሥራ 16:3