በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዛሬም የሚሠራ ጥንታዊ ጥበብ

በነፃ ይቅር በሉ

በነፃ ይቅር በሉ

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እንኳ . . . በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ። ይሖዋ በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ።”—ቆላስይስ 3:13

ይህ ምን ማለት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ኃጢአትን ከዕዳ ጋር፣ ይቅር ባይነትን ደግሞ ዕዳን ከመሰረዝ ጋር ያመሳስለዋል። (ሉቃስ 11:4) አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ “ይቅር ማለት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ዕዳን ሳያስከፍሉ በነፃ መተው” የሚል ትርጉም አለው። በመሆኑም የበደለንን ሰው ይቅር ለማለት ስንወስን ግለሰቡ በአጸፋው ምንም ነገር እንዲያደርግልን አንጠብቅም ማለት ነው። ይቅር ለማለት ፈቃደኛ መሆናችን የተፈጸመውን መጥፎ ድርጊት እንደምንደግፍ ወይም ያስከተለብንን ጉዳት አቅልለን እንደምንመለከት አያሳይም። ከዚህ ይልቅ ‘ቅር የተሰኘንበት ነገር’ ቢኖርም እንኳ ቂም ከመያዝ እንቆጠባለን ማለት ነው።

ይህ ምክር ዛሬም ይሠራል? ሁላችንም ፍጽምና ስለሚጎድለን ኃጢአት እንሠራለን። (ሮም 3:23) በመሆኑም ሌሎችን ይቅር ለማለት ዝግጁ መሆናችን ጥበብ ነው፤ ምክንያቱም ይዋል ይደር እንጂ እኛም ይቅር እንዲሉን ሌሎችን መጠየቃችን አይቀርም። ከዚህም በላይ ይቅር ባይ መሆናችን ራሳችንን ይጠቅመናል። እንዴት?

ይቅር ማለት ተስኖን፣ ተናደንና ተቀይመን የምንቆይ ከሆነ ራሳችንን እንጎዳለን። እንዲህ ያሉ አፍራሽ ስሜቶች ደስታ ሊነፍጉን፣ ነፃነት ሊያሳጡንና ሕይወታችንን ሊያመሰቃቅሉብን ይችላሉ። በተጨማሪም ከባድ የጤና ችግር ሊያስከትሉብን ይችላሉ። ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ኮሌጅ ኦቭ ካርዲዮሎጂ ላይ የወጣ በዶክተር ዮኢቺ ቺዳ እና የሥነ ልቦና ጥናት ፕሮፌሰር በሆኑት አንድሩ ስቴፕቶ የተዘጋጀ አንድ ሪፖርት እንዲህ ይላል፦ “በቅርቡ የተደረሰባቸው የጥናት ውጤቶች፣ ንዴትና ጥላቻ ለልብ በሽታ እንደሚያጋልጡ ይጠቁማሉ።”

በአንጻሩ ደግሞ ይቅር ማለት ያሉትን ጥቅሞች እንመልከት። ሌሎችን በነፃ ይቅር የምንል ከሆነ አንድነታችንና ሰላማችን ይጠበቃል፤ በዚህ መንገድ ወዳጅነታችን እየተጠናከረ ይሄዳል። ከምንም በላይ ደግሞ፣ ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞችን በነፃ ይቅር የሚለውንና እኛም እንዲሁ እንድናደርግ የሚጠብቅብንን አምላክ እንደምንመስል እናሳያለን።—ማርቆስ 11:25፤ ኤፌሶን 4:32፤ 5:1