በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የሃሎዊን አመጣጥ ምንድን ነው?

የሃሎዊን አመጣጥ ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ብዙዎች በየዓመቱ ጥቅምት 31 ላይ ሃሎዊን የተባለውን በዓል ያከብራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ በዓል አይናገርም። ይሁንና የሃሎዊን አመጣጥና ከበዓሉ ጋር የተያያዙ ልማዶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር ይጋጫሉ።

በዚህ ርዕስ ውስጥ

 የሃሎዊን አመጣጥና ከበዓሉ ጋር የተያያዙ ልማዶች

  •   ሳምሄን፦ ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደሚገልጸው ሃሎዊን የመጣው “ኬልቶች ከ2,000 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ያከብሩ ከነበረው ከባዕድ አምልኮ ጋር የተያያዘ ጥንታዊ በዓል ነው። ኬልቶች በዚህ በዓል ወቅት ሙታን በሕያዋን መካከል እንደሚመላለሱ ያምኑ ነበር። በሳምሄን ወቅት በሕይወት ያሉ ሰዎች ከሙታን ጋር መገናኘት ይችላሉ።”—“ ሃሎዊን ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው?” የሚለውን ተመልከት።

  •   የሃሎዊን ልብሶች፣ ከረሜላ እና የልጆች ጨዋታ፦ አንድ ምንጭ እንደሚገልጸው፣ ኬልቶች ወዲያ ወዲህ የሚሉ መናፍስት “ከእነሱ እንደ አንዱ ቆጥረው” እንዲተዉአቸው አስፈሪ ልብስ ይለብሱ ነበር። ሌሎች ደግሞ መናፍስቱን ለማስደሰት ሲሉ ጣፋጭ ነገር ያስቀምጡ ነበር። a

     በመካከለኛው ዘመን አውሮፓ ውስጥ ያሉ የካቶሊክ ቀሳውስት ከባዕድ አምልኮ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የአካባቢውን ልማዶች በመቀበል የቤተ ክርስቲያናቸው አባላት ለየት ያለ ልብስ ለብሰው ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ አነስተኛ ስጦታዎችን እንዲጠይቁ አደረጉ።

  •   የሙታን መናፍስት፣ ቫምፓየሮች፣ ጭራቆች፣ ጠንቋዮች እና ዞምቢዎች፦ እነዚህ ነገሮች ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የሚጠቀሱት ከክፉ መናፍስት ጋር ተያይዘው ነው። ሃሎዊን ትሪቪያ የተባለው መጽሐፍ እነዚህ “ምትሃታዊ ፍጥረታት ከሞት፣ ከሙታን ወይም ከሞት ፍርሃት ጋር የቅርብ ተዛማጅነት” እንዳላቸው ይገልጻል።

  •   የሃሎዊን ዱባ፦ በመካከለኛው ዘመን ብሪታንያ ውስጥ “ሰዎች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ምግብ በመጠየቅ በምትኩ ለሙታን ጸሎት እንደሚያቀርቡ ይገልጹ ነበር”፤ እነዚህ ሰዎች ‘ውስጣቸው ተቦርቡሮ የወጣና ሻማ የበራባቸው ቀይ ሥር የመሰሉ አትክልቶችን ይይዙ ነበር፤ ሻማው መንጽሔ ውስጥ የተያዘችን ነፍስ ይወክላል።’ (ሃሎዊን—ፍሮም ፔጋን ሪቹዋል ቱ ፓርቲ ናይት) አንዳንድ ምንጮች እንደሚገልጹት እነዚህ መብራቶች ክፉ መናፍስትን ለማባረር ያገለግሉ ነበር። በ1800ዎቹ ሰሜን አሜሪካ ውስጥ ቀይ ሥሮቹ በዱባ ተተኩ፤ ምክንያቱም ዱባ በብዛት የሚገኝ ከመሆኑም ሌላ ውስጡን ለማውጣትና ለመቅረጽ ቀላል ነው።

 የሃሎዊን አመጣጥ ከባዕድ አምልኮ ጋር የተያያዘ መሆኑ ለውጥ ያመጣል?

 አዎ። አንዳንዶች ሃሎዊን ምንም ጉዳት የሌለው አዝናኝ በዓል እንደሆነ ቢሰማቸውም ከበዓሉ ጋር የተያያዙት ልማዶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር በቀጥታ ይጋጫሉ። ሃሎዊን የተመሠረተው ስለ ሙታንና ስለ መናፍስት ወይም አጋንንት በሚገልጹ የሐሰት እምነቶች ላይ ነው።

 አምላክ ከሃሎዊን ጋር ለተያያዙ እምነቶች ምን አመለካከት እንዳለው ለማየት የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት፦

  •   “መናፍስት ጠሪ፣ ጠንቋይ ወይም ሙታን አነጋጋሪ በመካከልህ አይገኝ።”—ዘዳግም 18:10-12

     ትርጉሙ፦ አምላክ ከሙታን ጋር ለመገናኘት ጥረት እንድናደርግ ወይም ከሙታን ጋር ለመነጋገር እየሞከርን እንዳለን የሚያስመስል ነገር እንድናደርግ አይፈልግም።

  •   “ሙታን . . . ምንም አያውቁም።”—መክብብ 9:5

     ትርጉሙ፦ ሙታን ምንም ስለማያውቁ በሕይወት ካሉ ሰዎች ጋር መገናኘት አይችሉም።

  •   “ከአጋንንት ጋር [አትተባበሩ]። የይሖዋን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ መጠጣት አትችሉም።”—1 ቆሮንቶስ 10:20, 21

     ትርጉሙ፦ የአምላክን ሞገስ ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ከአጋንንት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ሊኖራቸው አይገባም።

  •   “የዲያብሎስን መሠሪ ዘዴዎች [ተቋቋሙ]፤ ምክንያቱም የምንታገለው . . . ከክፉ መንፈሳዊ ኃይሎች ጋር ነው።”—ኤፌሶን 6:11, 12

     ትርጉሙ፦ ክርስቲያኖች ክፉ መንፈሳዊ ኃይሎችን ሊቃወሙ እንጂ ከእነሱ ጋር እንደሚዝናኑ ሊያስመስሉ አይገባም።

a ሃሎዊን፦ አን አሜሪካን ሆሊዴይ፣ አን አሜሪካን ሂስትሪ የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 4⁠ን ተመልከት።