በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

ሕይወቴ ከድጡ ወደ ማጡ ሄዶ ነበር

ሕይወቴ ከድጡ ወደ ማጡ ሄዶ ነበር
  • የትውልድ ዘመን፦ 1952

  • የትውልድ አገር፦ ዩናይትድ ስቴትስ

  • የኋላ ታሪክ፦ግልፍተኛ የነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ፦

ያደግኩት በሎስ አንጀለስ፣ ካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ሲሆን የሚደባደቡና ዕፅ የሚወስዱ ዱሪዬዎች በሞሉባቸው ሰፈሮች ነው። ወላጆቼ ካሏቸው ስድስት ልጆች መካከል ሁለተኛ ልጅ ነበርኩ።

እናቴ ያሳደገችን የወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች አድርጋ ነበር። ይሁንና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለሁ ሁለት ዓይነት ኑሮ እኖር ነበር። እሁድ እሁድ ከቤተ ክርስቲያን መዘምራን ጋር እዘምራለሁ። የቀሩትን የሳምንቱን ቀናት ግን በጭፈራ፣ ዕፅ በመውሰድና የፆታ ብልግና በመፈጸም አሳልፋለሁ።

ቁጡና ግልፍተኛ ነበርኩ። ከሌሎች ጋር ስጣላ ባገኘሁት ነገር እደባደብ ነበር። በቤተ ክርስቲያን የተማርኩት ነገር ምንም አልረዳኝም። “በቀል የጌታ ነው፤ እኔ ደግም የእሱ መሣሪያ ነኝ!” እል ነበር። በ1960ዎቹ መገባደጃ ላይ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ ብላክ ፓንተርስ (ጥቁሮቹ ግስላዎች) የሚባሉ ሰብዓዊ መብትን ለማስከበር የዓመፅ እርምጃዎችን የሚወስዱ አባላት ካሉት አንድ የፖለቲካ ቡድን ጋር ተቀላቀልኩ። ከዚያም ለሰብዓዊ መብቶች የሚሟገት አንድ የተማሪዎች ኅብረት አባል ሆንኩ። በተደጋጋሚ ጊዜ ትምህርት ቤቱን ዘግተን የተቃውሞ ሰልፍ እንወጣ ነበር።

በዚህ መንገድ ተቃውሞዬን ብገልጽም በውስጤ ያለው ቁጣ ሊበርድልኝ አልቻለም። በመሆኑም በጭፍን ጥላቻ በሚፈጸሙ ወንጀሎች መካፈል ጀመርኩ። ለምሳሌ በአንድ ወቅት እኔና ጓደኞቼ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በአፍሪካውያን ባሮች ላይ ይፈጸም ስለነበረው ግፍ የሚያሳዩ ፊልሞች ተመለከትን። በፊልሙ ላይ ባየነው ግፍ ስለተበሳጨን እዚያው ፊልም ቤት ውስጥ የነበሩትን ነጭ ወጣቶች መደብደብ ጀመርን። ከዚያም ሌሎች ነጮችን ለመደብደብ እነሱ ወደሚኖሩበት ሰፈር ሄድን።

በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ ሳለሁ እኔና ወንድሞቼ የታወቀ የዓመፀኞች ቡድን አባል ሆንን። ብዙ ጊዜ ከፖሊሶች ጋር እንጋጭ ነበር። ከታናሽ ወንድሞቼ መካከል አንዱ የአንድ የታወቀ የዱሪዬዎች ቡድን አባል ስለነበረ እኔም ከዚህ ቡድን ጋር ተቀላቀልኩ። ሕይወቴ ከድጡ ወደ ማጡ ሄዶ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

አንድ ጓደኛዬ ወላጆቹ የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። በጉባኤ ስብሰባዎቻቸው ላይ እንድገኝ ሲጋብዙኝ እኔም ግብዣውን ተቀበልኩ። ገና ከጅምሩ የይሖዋ ምሥክሮች የተለዩ እንደሆኑ ማስተዋል ችዬ ነበር። ሁሉም መጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው ሲሆን በስብሰባቸውም ላይ ይጠቀሙበታል። ወጣቶችም እንኳ በፕሮግራሙ ላይ ንግግር አቅርበው ነበር! አምላክ ስም እንዳለው ይኸውም ስሙ ይሖዋ እንደሆነ ማወቄና በስሙ ሲጠሩት መስማቴ በጣም አስደነቀኝ። (መዝሙር 83:18) ጉባኤው የተለያየ ዘር ያላቸው ሰዎች የሚገኙበት ቢሆንም ምንም ዓይነት የዘር ልዩነት እንደሌለ በግልጽ ይታይ ነበር።

መጀመሪያ ላይ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት አልፈለግኩም፤ ይሁንና ወደ ስብሰባዎቻቸው መሄድ ደስ ይለኝ ነበር። አንድ ቀን ምሽት እኔ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ እያለሁ ጓደኞቼ ደግሞ ወደ አንድ የሙዚቃ ትርኢት ሄደው ነበር። በዚያም አንድ ወጣት የቆዳ ጃኬቱን ሊሰጣቸው ፈቃደኛ ባለመሆኑ ደብድበው ገደሉት። በማግስቱ፣ ስለፈጸሙት ግድያ በጉራ ይናገሩ ነበር። እንዲያውም ፍርድ ቤት በቀረቡበት ጊዜ የፈጸሙትን ወንጀል በማቃለል ያሾፉ ነበር። አብዛኞቹ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደባቸው። እኔ ያን ቀን ማታ አብሬያቸው ባለመሆኔ በጣም ደስ አለኝ። ሕይወቴን ለመለወጥና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ወሰንኩ።

እኔን ጨምሮ ጓደኞቼ በሙሉ ከፍተኛ የዘር ጥላቻ ስለነበረን በይሖዋ ምሥክሮች መካከል የማየው ነገር በጣም አስገረመኝ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ነጭ የይሖዋ ምሥክር ወደ ውጭ አገር ሲሄድ ልጆቹን እንዲጠብቁለት አደራ የሰጠው ለአንድ ጥቁር ቤተሰብ ነበር። እንዲሁም አንድ ነጭ ቤተሰብ መኖሪያ የሌለውን አንድ ጥቁር ወጣት ከእነሱ ጋር እንዲኖር አድርገዋል። በዮሐንስ 13:35 ላይ የሚገኘውን “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” የሚለውን ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ ተግባራዊ የሚያደርጉት የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ እርግጠኛ ሆንኩ። እውነተኛ የወንድማማች ፍቅር ያላቸው እነማን እንደሆኑ አወቅኩ።

መጽሐፍ ቅዱስን ሳጠና አስተሳሰቤን መለወጥ እንደሚያስፈልገኝ ተገነዘብኩ። አስተሳሰቤን የለወጥኩት እንዲሁ ሰላማዊ መሆን ስላለብኝ ብቻ ሳይሆን ከሁሉ የተሻለው የሕይወት መንገድ ይህ መሆኑንም ስለተገነዘብኩ ነው። (ሮም 12:2) ቀስ በቀስ እድገት አደረግኩ። ጥር 1974 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።

አስተሳሰቤን የለወጥኩት እንዲሁ ሰላማዊ መሆን ስላለብኝ ብቻ ሳይሆን ከሁሉ የተሻለው የሕይወት መንገድ ይህ መሆኑንም ስለተገነዘብኩ ነው

ይሁን እንጂ ከተጠመቅኩ በኋላም ግልፍተኝነቴን ለመተው ጥረት ማድረግ አስፈልጎኝ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ቀን ከቤት ወደ ቤት በመሄድ መጽሐፍ ቅዱስን እየሰበክሁ ሳለሁ ከመኪናዬ ውስጥ ሬዲዮ ሲሰርቅ ያገኘሁትን ሌባ አሯሩጬ ለመያዝ ሞክሬ ነበር። ልይዘው ስል ሬዲዮውን ጥሎ አመለጠ። የተሰረቀብኝን ሬዲዮ እንዴት እንዳስጣልኩ አብረውኝ ለነበሩት ስነግራቸው በአገልግሎት ቡድኑ ውስጥ የነበረ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ “ስቲቨን፣ ሌባውን ይዘኸው ቢሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?” ብሎ ጠየቀኝ። ይህ ጥያቄ ቆም ብዬ እንዳስብና ሰላማዊ ለመሆን ይበልጥ ጥረት እንዳደርግ አነሳስቶኛል።

ከጥቅምት 1974 ጀምሮ መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማሩ ሥራ በየወሩ 100 ሰዓት በማሳለፍ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆንኩ። በኋላም በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ፈቃደኛ ሠራተኛ በመሆን የማገልገል መብት አገኘሁ። በ1978 እናቴን ለማስታመም ወደ ሎስ አንጀለስ ተመለስኩ። ከሁለት ዓመት በኋላ ውዷ ባለቤቴን አራንዳን አገባሁ። እናቴ እስከሞተችበት ዕለት ድረስ እሷን በመንከባከብ ረገድ ባለቤቴ ትልቅ ድጋፍ ሆናልኛለች። ከጊዜ በኋላ እኔና አራንዳ በጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ገብተን ከተማርን በኋላ ፓናማ ተመደብን፤ በዚያም በሚስዮናዊነት ማገልገላችንን ቀጠልን።

ከተጠመቅኩበት ጊዜ አንስቶ ለድብድብ የሚጋብዙ ብዙ ሁኔታዎች አጋጥመውኛል። ለጠብ ሊያነሳሱኝ የሚሞክሩ ሰዎች ሲያጋጥሙኝ ትቻቸው መሄድን አሊያም ነገሩን በሌላ መንገድ ለማብረድ ጥረት ማድረግን ተምሬያለሁ። ባለቤቴን ጨምሮ ብዙ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙኝ የወሰድኳቸውን እርምጃዎች ተመልክተው አመስግነውኛል። አንዳንድ ጊዜ ያደረግኩት ለውጥ እኔ ራሴም ይገርመኛል! እንዲህ ዓይነት የባሕርይ ለውጥ በማድረጌ ልመሰገን የሚገባኝ እኔ አይደለሁም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት የመለወጥ ኃይል እንዳለው የሚያሳይ ማስረጃ እንደሆነ ይሰማኛል።—ዕብራውያን 4:12

ያገኘሁት ጥቅም፦

መጽሐፍ ቅዱስ ዓላማ ያለው ሕይወት እንድኖር ከማድረጉም ሌላ ሰላማዊ እንድሆን አስችሎኛል። አሁን ሰዎችን አልደበድብም፤ ከዚህ ይልቅ በመንፈሳዊ እንዲፈወሱ እረዳቸዋለሁ። እንዲያውም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለሁ ጠላቴ የነበረውን ሰው መጽሐፍ ቅዱስ አስጠንቼዋለሁ! እሱ ከተጠመቀ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ አብረን ኖረናል። እስካሁንም ድረስ የቅርብ ጓደኛሞች ነን። እስከዛሬ ድረስ እኔና ባለቤቴ ከ80 የሚበልጡ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስን በማስጠናት የይሖዋ ምሥክሮች እንዲሆኑ ረድተናል።

እውነተኛ የወንድማማች ፍቅር ባለው ሕዝብ መካከል ትርጉም ያለው ሕይወት እንድመራና ደስተኛ እንድሆን ስለረዳኝ ይሖዋን በጣም አመሰግነዋለሁ።