በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | አምላክ ያስፈልገናል?

አምላክ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

አምላክ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

የሥነ አእምሮ ጤና ባለሙያዎች፣ ሰዎች እውነተኛ ደስታ እንዲያገኙ ከተፈለገ መንፈሳዊ እሴቶች እንደሚያስፈልጓቸው ይናገራሉ። ሰዎች ራሳቸውን ለአንድ ነገር መስጠት ወይም ከእነሱ የሚበልጥን አካል ማገልገል የሚፈልጉ መሆናቸው የዚህን እውነተኝነት ያሳያል። አንዳንድ ሰዎች ይህን ፍላጎታቸውን ለማርካት ሲሉ ትርፍ ጊዜያቸውን ለተፈጥሮ፣ ለኪነ ጥበብ፣ ለሙዚቃ፣ ወዘተ ያውላሉ። ሆኖም አብዛኞቹ ሰዎች እንዲህ ዓይነቶቹን ነገሮች በማሳደድ እውነተኛና ዘላቂ የሆነ እርካታ አያገኙም።

የአምላክ ፍላጎት የሰው ልጆች አሁንም ሆነ ለዘላለም ደስተኞች እንዲሆኑ ነው

ሰዎች በተፈጥሯቸው መንፈሳዊ ፍላጎት ያላቸው መሆኑ መጽሐፍ ቅዱስን ለሚያነብቡ ሰዎች እንግዳ ነገር አይደለም። የዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያዎቹ ምዕራፎች እንደሚጠቁሙት አምላክ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት ከፈጠረ በኋላ ከእነሱ ጋር አዘውትሮ ይነጋገር ነበር፤ ይህም ከእሱ ጋር መንፈሳዊ ዝምድና እንዲመሠርቱ አስችሏቸዋል። (ዘፍጥረት 3:8-10) አምላክ ሰዎችን የፈጠረው ከእሱ ተነጥለው እንዲኖሩ አልነበረም፤ በመሆኑም የግድ ከፈጣሪያቸው ጋር የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ጉዳይ አስፈላጊ መሆኑን በተደጋጋሚ ይናገራል።

ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ” ማለትም መንፈሳዊ ነገር እንደሚያስፈልጋቸው የሚገነዘቡ ሰዎች “ደስተኞች” መሆናቸውን ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:3) ከዚህ ሐሳብ መረዳት እንደምንችለው ደስታና እርካታ የሞላበት ሕይወት ለመምራት ወሳኝ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ተፈጥሯዊ የሆነውን መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ማርካት ነው። ታዲያ ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ “ሰው ከይሖዋ አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ ሊኖር አይችልም” ብሎ ሲናገር የዚህን ጥያቄ መልስ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 4:4) ታዲያ ከአምላክ አፍ የሚወጡ ቃላት ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹት የአምላክ ሐሳቦችና መመሪያዎች አስደሳችና ትርጉም ያለው ሕይወት እንድንመራ የሚያስችሉን እንዴት ነው? እስቲ ሦስት ዋና ዋና መንገዶችን እንመልከት።

ጥሩ መመሪያ ያስፈልገናል

በዛሬው ጊዜ ስለ ወዳጅነት፣ ፍቅር፣ የቤተሰብ ሕይወትና ደስታ እንዲሁም ግጭቶችን መፍታት ስለሚቻልበት መንገድ አልፎ ተርፎም ስለ ሕይወት ትርጉም ምክር ለመስጠት ዝግጁ ሆነው የሚጠብቁ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ባለሙያዎች አሉ። ይሁንና የሰው ልጆች ፈጣሪ ከሆነው ከይሖዋ አምላክ ሌላ በእነዚህ መስኮች ጥሩና ሚዛናዊ መመሪያ ለመስጠት ከሁሉ የላቀ ብቃት ያለው ማን ይኖራል?

ልክ እንደ አንድ የተጠቃሚ መመሪያ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስም የሕይወት መመሪያ ነው

እስቲ ነገሩን በምሳሌ ለማየት እንሞክር፦ እንደ ካሜራ ወይም ኮምፒውተር ያለ አንድ አዲስ ዕቃ ስትገዛ ዕቃውን በአግባቡና ለአንተ  እርካታ በሚያመጣ መንገድ መጠቀም የምትችለው እንዴት እንደሆነ የሚገልጽ መመሪያ አብሮት እንደሚኖር ትጠብቃለህ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ካለው መመሪያ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምራቹ ማለትም የሰብዓዊ ሕይወት ፈጣሪ የሆነው አምላክ ለተጠቃሚዎቹ ማለትም ለእኛ ያዘጋጀልን መመሪያ ነው። የተጠቃሚ መመሪያ አንድ ዕቃ የተመረተበትን ዓላማና አጠቃቀሙን እንደሚገልጽ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስም ሰዎች የተፈጠሩበት ዓላማ ምን እንደሆነና ሕይወታቸውን ስኬታማ በሆነ መንገድ መምራት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ያብራራል።

አንድ በጥሩ መንገድ የተዘጋጀ መመሪያ ዕቃውን ሊያበላሽ ከሚችል አጠቃቀም እንድንጠነቀቅ እንደሚጠቁመን ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስም ሕይወታችንን አስተማማኝ በሆነ መንገድ መምራት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይነግረናል። ሌሎች የሚሰጡት ምክር ወይም አቋራጭ መንገድ፣ ጥሩና ሕይወታችንን ቀላል የሚያደርግ ሊመስል ይችላል፤ ይሁንና የሠሪውን መመሪያዎች መከተል ከሁሉ የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝና ችግሮችን ለማስወገድ እንደሚረዳ ማሰቡ ምክንያታዊ አይደለም?

“እኔ እግዚአብሔር አምላክህ፣ የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ፣ መሄድ በሚገባህ መንገድ የምመራህ ነኝ። ትእዛዜን ሰምተህ ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር።” —ኢሳይያስ 48:17, 18

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚያስፈልገንን መመሪያና እርዳታ ማግኘት እንችላለን

ይሖዋ አምላክ መመሪያዎችንና ትእዛዛትን ቢሰጠንም እንድንቀበላቸው አያስገድደንም። ከዚህ ይልቅ ስለሚወደንና ሊረዳን ስለሚፈልግ በፍቅር በመገፋፋት የሚከተለውን ግብዣ ያቀርብልናል፦ “እኔ እግዚአብሔር አምላክህ፣ የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ፣ መሄድ በሚገባህ መንገድ የምመራህ ነኝ። ትእዛዜን ሰምተህ ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር።” (ኢሳይያስ 48:17, 18) በአጭሩ፣ የአምላክን መመሪያ የምንከተል ከሆነ ጥሩ ሕይወት እንመራለን። በሌላ አባባል፣ ጥሩ ሕይወት ለመምራትና ደስተኛ ለመሆን አምላክ ያስፈልገናል።

በሕይወታችን ውስጥ ለሚነሱብን ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ያስፈልገናል

አንዳንዶች አምላክ እንደማያስፈልጋቸው የሚሰማቸው፣ አፍቃሪ ነው ብሎ ከማመን ጋር የሚቃረኑ ብዙ ግራ የሚያጋቡ ጥያቄዎች ስለሚፈጠሩባቸው ነው። ለምሳሌ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ያነሱ ይሆናል፦ ‘ጥሩ ሰዎች መከራ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?’ ‘ምንም ጥፋት ያልሠሩ ሕፃናት አካል ጉዳተኛ ሆነው የሚወለዱት ለምንድን ነው?’ ‘ሕይወት ኢፍትሐዊ በሆኑ ነገሮች የተሞላው ለምንድን ነው?’ እነዚህ በእርግጥም አሳሳቢ ጥያቄዎች ናቸው፤ ለጥያቄዎቹ አጥጋቢ መልስ ማግኘታችን በሕይወታችን ላይ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ይሁን እንጂ እንዲህ ላሉት ችግሮች አምላክን ተጠያቂ ለማድረግ ከመቸኮል ይልቅ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ብርሃን እንደሚፈነጥቅ እንመልከት።

ይሖዋ አምላክ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ ፍሬ እንዳይበሉ አዝዟቸው ነበር፤ ይሁንና ሰይጣን በእባብ በመጠቀም ይህን ትእዛዝ እንዲጥሱና በአምላክ ላይ እንዲያምፁ ለማድረግ እንደፈለገ በዘፍጥረት መጽሐፍ ሦስተኛ ምዕራፍ ላይ እናነብባለን። በዚህ ጊዜ ሰይጣን “መሞት እንኳ አትሞቱም” በማለት ለሔዋን ነገራት። አክሎም “ከፍሬው በበላችሁ ጊዜ ዐይናችሁ እንደሚከፈትና መልካምና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር እንደምትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው” አላት።—ዘፍጥረት 2:16, 17፤ 3:4, 5

ይህ አባባል እንደሚያሳየው ሰይጣን የተናገረው፣ አምላክ ውሸታም መሆኑን ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ፍጥረታቱን የሚገዛበት መንገድ ትክክል እንዳልሆነም በተዘዋዋሪ ገልጿል። ዲያብሎስ፣ የሰው ዘሮች እሱን ቢሰሙት የተሻለ ሕይወት እንደሚመሩ ተከራክሯል። ታዲያ እነዚያ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው? ይሖዋ፣ በእሱ ላይ የተሰነዘሩት ክሶች እውነት ወይም ሐሰት መሆናቸውን ሁሉም ማሰብ የሚችሉ ፍጥረታት  በሂደት እንዲያዩ ለማስቻል ሲል ጊዜ መስጠትን መረጠ። አምላክ፣ ሰዎች ያለ እሱ ጣልቃ ገብነት ጥሩ ሕይወት መኖር መቻላቸውን እንዲያረጋግጡ ለሰይጣንና ከእሱ ጎን ለተሰለፉ ሁሉ አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል ሊባል ይችላል።

ሰይጣን ላስነሳው ክርክር ፍርድ ስጥ ብትባል ምን መልስ ትሰጣለህ? ሰዎች ያለ አምላክ ጣልቃ ገብነት ጥሩ ሕይወት መምራትና ራሳቸውን በተሳካ ሁኔታ ማስተዳደር ይችላሉ? ላለፉት ብዙ መቶ ዘመናት በሰው ልጆች ላይ የደረሰው መከራ፣ የፍትሕ መዛባት፣ በሽታና ሞት እንዲሁም ወንጀል፣ የሥነ ምግባር ውድቀት፣ ጦርነት፣ የዘር ማጥፋት ዘመቻና ሌሎች የጭካኔ ድርጊቶች ሰው ከአምላክ ተነጥሎ ራሱን ለማስተዳደር ያደረገው ጥረት እንደከሸፈ በግልጽ የሚያሳዩ ማንም ሊያስተባብላቸው የማይችል ማስረጃዎች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ በሰው ዘር ላይ ለደረሰው ሥቃይ ተጠያቂው አምላክ እንደሆነ አይገልጽም፤ ከዚህ ይልቅ ‘ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው’ በማለት አንዱን ዋነኛ መንስኤ ለይቶ ይጠቅሳል።—መክብብ 8:9

ከዚህ አንጻር፣ የሰዎችን አእምሮ ለሚያስጨንቁ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ብቻ ሳይሆን መፍትሔ ፍለጋም ጭምር ፊታችንን ወደ አምላክ ማዞር እንደሚያስፈልገን ግልጽ አይደለም? ታዲያ አምላክ ምን ያደርጋል?

የአምላክ እርዳታ ያስፈልገናል

ሰዎች ከበሽታ፣ ከእርጅናና ከሞት ነፃ ለመውጣት ለዘመናት ሲናፍቁ ኖረዋል። ይሁንና ምንም ለውጥ ላያመጡ ነገር፣ ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ ፍለጋ በከንቱ ይህ ነው የማይባል ጊዜ፣ ጉልበትና ሀብት አጥፍተዋል። አንዳንዶች፣ ምትሐታዊ ኃይል ያለው መድኃኒት በመውሰድ፣ ወጣትነትን መልሶ ያጎናጽፋል የሚባል የምንጭ ውኃ በመጠጣት ወይም ሻንግሪላ የሚባል እንደ ገነት ያለ ምናባዊ ቦታ በማሰስ የተመኙትን ነፃነት ለማግኘት ተስፋ አድርገው ነበር። እነዚህ ምኞቶች በሙሉ ግን መና ሆነው ቀርተዋል።

አምላክ ሰዎች ጥሩ ሕይወት እንዲመሩና ደስተኞች እንዲሆኑ ይፈልጋል። ሰዎችን የፈጠረበት ዓላማም ይህ ነበር፤ አሁንም ቢሆን ዓላማውን አልረሳውም። (ዘፍጥረት 1:27, 28፤ ኢሳይያስ 45:18) ይሖዋ አምላክ ምንም ይሁን ምን የተናገረውን ነገር ከግቡ የሚያደርስ መሆኑን ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (ኢሳይያስ 55:10, 11) አምላክ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ያጡትን የገነት ሕይወት መልሶ ለማምጣት ቃል መግባቱን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። በመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ የሚከተለውን ሐሳብ እናገኛለን፦ “እሱም [ይሖዋ አምላክ] እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።” (ራእይ 21:4) ታዲያ አምላክ ይህን አስደናቂ ተስፋ የሚፈጽመው እንዴት ነው? ደግሞስ እኛ ከዚህ ተስፋ ተካፋዮች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክ ፈቃድ ይፈጸም ዘንድ እንዲጸልዩ ተከታዮቹን አስተምሯቸው ነበር። ብዙዎች የጌታ ጸሎት ብለው የሚጠሩትን ይህን ጸሎት በርካታ ሰዎች ያውቁታል፤ እንዲያውም አንዳንዶች ይደግሙታል። ጸሎቱ እንዲህ ይላል፦ “በሰማያት የምትኖር አባታችን፣ ስምህ ይቀደስ። መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን።” (ማቴዎስ 6:9, 10) አዎ፣ ይሖዋ ለብዙ ሰቆቃ መንስኤ የሆነውን ሰብዓዊ አገዛዝ በማስወገድ ቃል የገባውን ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ለማምጣት የሚጠቀመው በዚህ መንግሥት ነው። * (ዳንኤል 2:44፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) ታዲያ አምላክ  ከሰጠው ከዚህ ተስፋ ተጠቃሚዎች ለመሆን ምን ማድረግ አለብን?

ኢየሱስ ክርስቶስ ልንወስደው የሚገባውን ቀላል እርምጃ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ስለሆንከው ስለ አንተና ስለላክኸው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት መቅሰማቸውን መቀጠል አለባቸው።” (ዮሐንስ 17:3) አዎ፣ ቃል በተገባልን አዲስ ዓለም ውስጥ ፍጻሜ የሌለው ሕይወት በአምላክ እርዳታ ማግኘት እንችላለን። ይህ ተስፋ፣ ‘አምላክ ያስፈልገናል?’ ለሚለው ጥያቄ ‘አዎን’ ብለህ እንድትመልስ የሚያነሳሳ ተጨማሪ ምክንያት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።

ወደ አምላክ ዞር ለማለት ጊዜው አሁን ነው

ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት በአቴና ውስጥ አርዮስፋጎስ ወይም የማርስ ኮረብታ በሚባለው ስፍራ ላገኛቸው መፈላሰፍ የሚወድዱ አቴናውያን ስለ አምላክ የሚከተለውን ተናግሮ ነበር፦ “ሕይወትንና እስትንፋስንም ሆነ ማንኛውንም ነገር ለሰው ሁሉ የሚሰጠው እሱ ስለሆነ የሚጎድለው ነገር ያለ ይመስል በሰው እጅ አይገለገልም። ምክንያቱም በእናንተ መካከል ያሉ አንዳንድ ባለቅኔዎች ‘እኛም የእሱ ልጆች ነንና’ ብለው እንደተናገሩት ሁሉ ሕይወት ያገኘነው፣ የምንንቀሳቀሰውና የምንኖረው በእሱ ነው።”—የሐዋርያት ሥራ 17:25, 28

ጳውሎስ ለአቴናውያን የተናገረው ነገር ዛሬም እውነት ነው። ፈጣሪያችን የምንተነፍሰውን አየር፣ የምንመገበውን ምግብ፣ የምንጠጣውን ውኃ ይሰጠናል። ይሖዋ ለመኖር የሚያስፈልጉንን እነዚህን መልካም ነገሮች ባይሰጠን ኖሮ ፈጽሞ መኖር ባልቻልን ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ፣ ስለ እሱ ለሚያስቡም ሆነ ለማያስቡ ሰዎች እንዲህ ያሉትን ዝግጅቶች እያደረገ ያለው ለምንድን ነው? ጳውሎስ ምክንያቱን ሲገልጽልን “ይህን ያደረገው ሰዎች አምላክን እንዲፈልጉትና አጥብቀው በመሻት እንዲያገኙት ብሎ ነው፤ እንዲህ ሲባል ግን እሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ ነው ማለት አይደለም” ብሏል።—የሐዋርያት ሥራ 17:27

አምላክን ይበልጥ ማወቅ ይኸውም ስለ ዓላማዎቹና አሁንም ሆነ ለዘላለም ጥሩ ሕይወት እንድንመራ ስለሚረዱን መመሪያዎቹ የበለጠ መማር ትፈልጋለህ? ከሆነ ይህን መጽሔት የሰጠህን ሰው ወይም የመጽሔቱን አዘጋጆች እንድታነጋግር እናበረታታሃለን። በደስታ ሊረዱህ ዝግጁዎች ናቸው።

^ አን.20 የአምላክ መንግሥት፣ ፈቃዱ በምድር እንዲፈጸም የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 8 ተመልከት፤ መጽሐፉን www.pr418.com/am ከተባለው ድረ ገጽ ላይ ማውረድ ይቻላል።