በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ከኮረብቶቿ መዳብ ቆፍረህ ታወጣለህ’

‘ከኮረብቶቿ መዳብ ቆፍረህ ታወጣለህ’

አንድ የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች ቡድን በይሁዳ ምድረ በዳ የሚገኙትን ሸለቆዎችና ዋሻዎች እያሰሰ ነበር። እነዚህ ባለሙያዎች በዚህ ወቅት ጭው ባለ ገደል ላይ አንድ ዋሻ አገኙ። ታዲያ በዚያ ውድ ነገሮችን ምናልባትም ጥንታዊ ቁሳቁሶችን ወይም እንደ ሙት ባሕር ጥቅልሎች ያሉ በእጅ የተጻፉ ጽሑፎችን ያገኙ ይሆን? የሚገርመው ነገር፣ በርካታ ውድ ቅርሶችን ያገኙ ሲሆን በኋላ ላይ ቦታው የናሐል ሚሽማር የከበሩ ነገሮች ክምችት ተብሎ ተሰይሟል።

በዋሻው ግድግዳ ላይ በሚገኝ ስንጥቅ ውስጥ በኬሻ ተጠቅልለው የተሸጎጡ ከ400 በላይ ቁሳቁሶች መጋቢት 1961 የተገኙ ሲሆን አብዛኞቹ የተሠሩት ከመዳብ ነበር። ከእነዚህም መካከል የተለያየ ዓይነት ዘውድ፣ በትረ መንግሥት፣ የእጅ መሣሪያ፣ ዘንግ፣ የጦር መሣሪያ ብሎም ሌሎች ቁሳቁሶች ይገኙበታል። ዘፍጥረት 4:22 ቱባልቃይን “ከብረትና ከናስ ልዩ ልዩ መሣሪያዎችን እየቀረጸ የሚሠራ” ሰው እንደነበር ስለሚናገር የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎቹ ያገኙት ክምችት የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢያንን ትኩረት የሚስብ ነው።

ከዚህ የውድ ቅርስ ክምችት አመጣጥና የኋላ ታሪክ ጋር በተያያዘ መልስ ያልተገኘላቸው ብዙ ጥያቄዎች አሉ። ያም ሆነ ይህ የክምችቱ መገኘት መዳብ (በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነሐስ ተብሎም ተተርጉሟል) ቆፍሮ ማውጣት፣ ማቅለጥና ቅርጽ ማውጣት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጠቀሱ ቦታዎች ከጥንት ጀምሮ ይታወቅ እንደነበረ ይጠቁማል።

በተስፋይቱ ምድር ውስጥ መዳብ የሚወጣባቸው ቦታዎች

እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሊገቡ ሲሉ ሙሴ “ከኰረብቶቿም መዳብ ቈፍረህ ልታወጣ የምትችልባት ምድር ናት” በማለት ነግሯቸው ነበር። (ዘዳግም 8:7-9) የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች በእስራኤልና በዮርዳኖስ በርካታ ጥንታዊ የማዕድን ማውጫና ማቅለጫ ስፍራዎችን አግኝተዋል፤ ከእነዚህ መካከል ኪርባት ኢን ናሐስ፣ ቲምናዕ እና ፌይናን ይገኙበታል። እነዚህ ስፍራዎች መገኘታቸው ምን የሚገልጸው ነገር አለ?

የፌይናንና የቲምናዕ መልክዓ ምድር ቢያንስ ለ2,000 ዓመታት መዳብ ሲወጣባቸው የነበሩ ጥልቀት የሌላቸው ጉዳጓዶች በብዛት የሚገኙበት ቦታ ነው። በዛሬው ጊዜም እንኳ አካባቢውን የሚጎበኝ አንድ ሰው፣ አረንጓዴ ነጠብጣብ ያለባቸውንና መዳብ የያዙ የማዕድን ድንጋዮችን ሊያገኝ ይችላል። የጥንቶቹ ማዕድን አውጪዎች በዐለቱ ላይ ተጣብቆ የሚያገኙትን መዳብ በድንጋይ መሣሪያ ተጠቅመው እየፈለፈሉ ያወጡ ነበር። እነዚህ የመዳብ ምንጮች ሲያልቁባቸው ደግሞ በብረት መሣሪያዎች ተጠቅመው ጥልቅ ጉድጓዶችን በመቆፈር ሰፋፊ ዋሻዎችን ይሠራሉ፤ እንዲሁም ወደ ላይና ወደ ጎን በመሰርሰር መሿለኪያዎች ያበጁ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው የኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ በዚህ መልክ ስለሚካሄድ ማዕድን የማውጣት ሥራ ተገልጾ እናገኛለን። (ኢዮብ 28:2-11) ይህ አድካሚ የጉልበት ሥራ ነበር፤ እንዲያውም ከሦስተኛው መቶ ዘመን ጀምሮ እስከ አምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ሮማውያን ባለሥልጣናት ከባድ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎችና ሌሎች እስረኞች በፌይናን በሚገኘው የመዳብ ማውጫ ውስጥ እንዲሠሩ ይፈርዱባቸው ነበር።

በኪርባት ኢን ናሐስ (“የመዳብ ቅሪት” ማለት ነው) በኢንዱስትሪ ደረጃ መዳብ የማቅለጥ ሥራ ይካሄድ እንደነበረ የሚያመለክት  ከፍተኛ መጠን ያለው የመዳብ ቅሪት ተገኝቷል። ምሁራን፣ የማዕድን ድንጋዮቹ የሚመጡት እንደ ፌይናንና ቲምናዕ ካሉ በአቅራቢያው ከሚገኙ የማዕድን ማውጫዎች እንደሆነ ያምናሉ። ከዐለቱ ውስጥ መዳቡን ለይቶ ለማውጣት ድንጋዩን የከሰል እሳት ላይ ያደርጉታል፤ ከዚያም ሙቀቱ 1,200 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ እስኪደርስ ድረስ ከስምንት እስከ አሥር ለሚጠጉ ሰዓታት በትንፋሽና በእግር ወናፍ ያራግቡታል። አንድ ኪሎ ግራም የመዳብ ጥፍጥፍ ለማውጣት አብዛኛውን ጊዜ አምስት ኪሎ ግራም የማዕድን ድንጋይ ያስፈልግ የነበረ ሲሆን ከዚያ በኋላ የቀለጠው መዳብ በቅርጽ ማውጫ አማካኝነት የተለያዩ ዕቃዎችን ለመሥራት ያገለግላል።

የመዳብ ጥቅም በጥንቷ እስራኤል

ይሖዋ አምላክ የማደሪያ ድንኳኑን ለመሥራት ከአካባቢው በሚወጣው በዚህ አብረቅራቂ ማዕድን እንዲጠቀሙ በሲና ተራራ ላይ ግልጽ ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር፤ ከጊዜ በኋላም በኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ ሲሠራ ይህንን ማዕድን ተጠቅመዋል። (ዘፀአት ምዕራፍ 27) እስራኤላውያን ወደ ግብፅ ከመውረዳቸው በፊት የብረት ሥራ ሙያ ሳይኖራቸው አይቀርም፤ አሊያም ደግሞ በግብፅ ሳሉ ሙያውን ቀስመው ሊሆን ይችላል። ከግብፅ ከወጡ ብዙም ሳይቆይ የጥጃ ምስል መሥራታቸው ችሎታው እንደነበራቸው ያሳያል። በተጨማሪም ለማደሪያው ድንኳን አገልግሎት የሚያስፈልጉ ለምሳሌ ገንዳ፣ ድስት፣ መጥበሻ፣ አካፋ፣ ሹካ እና የመሳሰሉትን የመዳብ ዕቃዎችን መሥራት ችለው ነበር።—ዘፀአት 32:4

በኋላም በምድረ በዳ ጉዟቸው ወቅት ምናልባትም መዳብ በብዛት በሚገኝባት ፋኖን (የዘመናችን ፌይናን ሳትሆን አትቀርም) ሲደርሱ ሊሆን ይችላል፣ ሕዝቡ በሚቀርብላቸው መና እና ውኃ ምክንያት አጉረመረሙ። ይሖዋም እነሱን ለመቅጣት መርዛማ እባቦችን የላከ ሲሆን በዚህ ምክንያት ብዙ ሰዎች ሞቱ። እስራኤላውያን ንስሐ ሲገቡ ሙሴ ይሖዋን ለመነላቸው፤ በዚህ ጊዜ ይሖዋ የመዳብ እባብ ሠርቶ በእንጨት ላይ እንዲሰቅለው አዘዘው። ዘገባው ከዚያ በኋላ የሆነውን ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “በእባብ የተነደፈ ማናቸውም ሰው ወደ ናሱ እባብ በተመለከተ ጊዜ ይድን ነበር።”—ዘኍልቍ 21:4-10፤ 33:43

የንጉሥ ሰለሞን መዳብ

ኢየሩሳሌም በነበረው ቤተ መቅደስ ውስጥ የነበሩት ብዙዎቹ ዕቃዎች የተሠሩት ከመዳብ ነበር

ንጉሥ ሰለሞን በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ በሚገነባበት ወቅት ከፍተኛ መጠን ያለው መዳብ ተጠቅሟል። አብዛኛው መዳብ የተገኘው አባቱ ዳዊት ከሶርያ ጋር በተዋጋ ጊዜ ካገኘው ምርኮ ነው። (1 ዜና መዋዕል 18:6-8) ካህናቱ ለመታጠብ የሚጠቀሙበት “ከቀለጠ” መዳብ የተሠራው ግዙፍ የመታጠቢያ ገንዳ 66,000 ሊትር የሚይዝና እስከ 30,000 ኪሎ ግራም የሚመዝን ነበር። (1 ነገሥት 7:23-26, 44-46) ከዚያም በቤተ መቅደሱ መግቢያ ላይ የቆሙ ሁለት ትላልቅ የመዳብ ምሰሶዎች ነበሩ። እነዚህ ምሰሶዎች ቁመታቸው 8 ሜትር ሲሆን ምሰሶዎቹ አናት ላይ 2.2 ሜትር ርዝመት ያላቸው ጉልላቶች ነበሩ፤ ውስጣቸው ክፍት የሆኑት እነዚህ ምሰሶዎች ውፍረታቸው 7.5 ሴንቲ ሜትር ዲያሜትራቸው ደግሞ 1.7 ሜትር ነበር። (1 ነገሥት 7:15, 16፤ 2 ዜና መዋዕል 4:17) እነዚህን ነገሮች ለመሥራት ብቻ የዋለውን የመዳብ መጠን ማስላት ናላ የሚያዞር ነው።

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ሰዎች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸውም ጭምር መዳብን በስፋት ይጠቀሙበት ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ከመዳብ የተሠሩ የጦር መሣሪያዎች፣ ሰንሰለቶች፣ የሙዚቃ መሣሪያዎችና በሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰው እናገኛለን። (1 ሳሙኤል 17:5, 6፤ 2 ነገሥት 25:7፤ 1 ዜና መዋዕል 15:19፤ መዝሙር 107:16) በተጨማሪም ኢየሱስ በቦርሳ ስለሚያዝ “የመዳብ” ገንዘብ የተናገረ ሲሆን ሐዋርያው ጳውሎስም “የነሐስ አንጥረኛው እስክንድር” በማለት ጠቅሷል።—ማቴዎስ 10:9፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:14

የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎችና የታሪክ ምሁራን በጥንት ዘመን የነበሩ መዳብ የሚወጣባቸውን ቦታዎችና እንቆቅልሽ የሆነውን የናሐል ሚሽማርን የከበሩ ነገሮች ክምችት በሚመለከት ገና መልስ ያላገኙላቸው ብዙ ጥያቄዎች አሉ። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ የሚያረጋግጠው አንድ ሐቅ አለ፦ እስራኤላውያን የወረሷት ምድር ‘ከኮረብቶቿ መዳብ ቆፍረው ሊያወጡባት የሚችሉ መልካም ምድር ነበረች።’—ዘዳግም 8:7-9