በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፍቺ የሚያስከትለውን ጫና መቋቋም

ፍቺ የሚያስከትለውን ጫና መቋቋም

“የምይዘው የምጨብጠው ጠፍቶኝ ነበር። ጥሩ ሕይወት እየመራሁ እያለ ሁሉ ነገር በድንገት እንዳልነበረ ሆነ።”—ማርክ፣ * ከተፋታ አንድ ዓመት የሆነው

“ባለቤቴ የልጃችን እኩያ ከሆነች ሴት ጋር አመነዘረ። የግልፍተኝነት ባሕርይ ስለነበረው በተፋታን ጊዜ እፎይታ ቢሰማኝም እንደተዋረድኩና ዋጋ ቢስ እንደሆንኩ ተሰምቶኝ ነበር።”—ኤመሊን፣ ከተፋታች 17 ዓመት የሆናት

አንዳንዶች የሚፋቱት ሕይወታቸው ከዚያ በኋላ የተሻለ እንደሚሆን አስበው ነው፤ ሌሎች ግን ትዳራቸው እንዲቀጥል ቢፈልጉም የትዳር ጓደኛቸው አብሯቸው ለመኖር ባለመፈለጉ ለመፋታት ይገደዳሉ። በዚያም ሆነ በዚህ፣ አብዛኞቹ ፍቺ የፈጸሙ ሰዎች ሕይወታቸው ከጠበቁት በላይ አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። በቅርብ ጊዜ ፍቺ ፈጽማችሁ ከሆነ አሁን ያላችሁበት ሁኔታ በሕይወታችሁ ውስጥ ካጋጠሟችሁ ችግሮች ሁሉ ይበልጥ ከባድ እንደሆነ ተሰምቷችሁ ይሆናል። ስለዚህ ፍቺ የሚያስከትላቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መወጣት እንድትችሉ የሚረዷችሁን አንዳንድ ጠቃሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች መመርመራችሁ ጥሩ ነው።

ተፈታታኝ ሁኔታ 1፦ አሉታዊ ስሜቶች

በገንዘብ ረገድ የሚያጋጥሙ ችግሮች፣ የወላጅነት ኃላፊነትና ብቸኝነት የሚያስከትሉት ውጥረት ነገሮች ከአቅማችሁ በላይ እንደሆኑ እንዲሰማችሁ ሊያደርግ ይችላል፤ እንዲህ ዓይነቱን ስሜት ለማስወገድ ደግሞ ጊዜ ይወስድ ይሆናል። ሟቿ የሥነ ልቦና ባለሙያ ጁዲት ዋለርስታይን እንደገለጹት አንዳንዶች ከተፋቱ ከበርካታ ዓመታት በኋላ እንኳ እንደተከዱና እንደተተዉ ይሰማቸዋል፤  “ሕይወት ፍትሐዊ እንዳልሆነና ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነ ያስባሉ፤ እንዲሁም ብቸኝነት ይሰማቸዋል።”

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

  • ስላጣችሁት ነገር ማዘናችሁ ስህተት እንደሆነ አታስቡ። ምናልባት የትዳር ጓደኛችሁን አሁንም ስለምትወዱት ሊናፍቃችሁ ይችላል። የትዳር ሕይወታችሁ ጥሩ እንዳልነበረ ብታውቁም እንኳ ከትዳር እንዳሰባችሁት ደስታ ማግኘት አለመቻላችሁ በእጅጉ ያሳዝናችሁ ይሆናል። (ምሳሌ 5:18) በዚህ ጊዜ “ማልቀስ” ብትፈልጉ ሊያሳፍራችሁ አይገባም።—መክብብ 3:1, 4

  • ራሳችሁን አታግልሉ። ሐዘናችሁ እንዲወጣላችሁ ብቻችሁን መሆን ብትፈልጉም ረዘም ላለ ጊዜ ራስን ማግለል ጥሩ አይሆንም። (ምሳሌ 18:1) ከወዳጆቻችሁ ጋር በምትጨዋወቱበት ጊዜ አዎንታዊ የሆኑ ነገሮችን ተናገሩ፤ በቀድሞ የትዳር ጓደኛችሁ ላይ ያላችሁን ቅሬታ (እውነት ቢሆንም እንኳ) አዘውትሮ ማውራት ሰዎች እንዲርቋችሁ ሊያደርግ ይችላል። ከተፋታችሁ ብዙም ሳትቆዩ ከበድ ያሉ ውሳኔዎችን ማድረግ ካለባችሁ እምነት የምትጥሉበትን ሰው ከማማከር ወደ ኋላ አትበሉ።

  • ጤንነታችሁን ተንከባከቡ። ፍቺ የሚያስከትለው ውጥረት ብዙውን ጊዜ እንደ ከፍተኛ የደም ግፊት ወይም እንደ ማይግሬን ያሉ የጤና ችግሮችን ያስከትላል። በሚገባ ተመገቡ፤ ስፖርት ሥሩ እንዲሁም በቂ እንቅልፍ ለማግኘት ጥረት አድርጉ።—ኤፌሶን 5:29

  • በቀድሞ የትዳር ጓደኛችሁ እንድትበሳጩ የሚያደርጓችሁንና የማያስፈልጓችሁን ነገሮች አስወግዱ፤ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ግን አትጣሉ። እንደ ሠርግ ፎቶግራፍ ያሉ ነገሮች መጥፎ ትዝታ የሚያመጡባችሁ ከሆነ በካርቶን አድርጋችሁ ለልጆቻችሁ አስቀምጡላቸው።

  • አፍራሽ ሐሳቦችን ለማስወገድ ጥረት አድርጉ። ባሏ ምንዝር በመፈጸሙ ምክንያት የተፋታችው ኦልጋ “‘ከእኔ ምን ቢያጣ ነው እሷ ጋር የሄደው?’ እያልኩ ሁልጊዜ ራሴን እጠይቃለሁ” ብላለች። ይሁንና ኦልጋ ከጊዜ በኋላ እንደተገነዘበችው በአፍራሽ ሐሳቦች ላይ ማውጠንጠን ‘መንፈስን ይሰብራል።’—ምሳሌ 18:14

    ብዙዎች፣ በአእምሯቸው የሚመላለሱትን ነገሮች በጽሑፍ ማስፈራቸው ስሜታቸውን በትክክል መረዳትና አስተሳሰባቸውን መቆጣጠር እንዲችሉ እንደረዳቸው ይናገራሉ። አሉታዊ በሆኑት ሐሳቦች ፈንታ አዎንታዊ የሆኑ ነገሮችን ለማሰብ ሞክሩ። (ኤፌሶን 4:23) ሁለት ምሳሌዎችን እንመልከት፦

    አሉታዊ፦ ባሌ፣ ሌላ ሴት ጋር የሄደው በእኔ ጥፋት ነው።

    አዎንታዊ፦ እኔ ጉድለት ቢኖርብኝም እንኳ ባሌ ሌላ ሴት ጋር መሄዱ ተገቢ ነው ማለት አይደለም።

    አሉታዊ፦ የወጣትነት ጊዜዬን ከማይሆን ሰው ጋር አባከንኩ።

    አዎንታዊ፦ ስላለፈው ሳይሆን ስለ ወደፊቱ ባስብ ይበልጥ ደስተኛ መሆን እችላለሁ።

  • ጎጂ ለሆኑ አስተያየቶች ጆሯችሁን አትስጡ። አንዳንድ ወዳጆቻችሁና ዘመዶቻችሁ፣ ሊጎዷችሁ አስበው ባይሆንም እንኳ ስሜት የሚያቆስሉ ወይም ትክክል ያልሆኑ ነገሮችን ሊናገሩ ይችላሉ፤ ለምሳሌ ‘ቀድሞም ቢሆን ላንቺ የሚሆን ሰው አልነበረም’ ወይም ‘አምላክ መፋታትን ይጠላል’ ይሏችሁ ይሆናል። * መጽሐፍ ቅዱስ “የሚነገረውን ቃል ሁሉ ለማዳመጥ አትሞክር” ያለው ያለምክንያት አይደለም። (መክብብ 7:21) ከተፋታች ሁለት ዓመት የሆናት ማርቲና እንዲህ ብላለች፦ “ጎጂ የሆኑ ንግግሮችን እያሰብኩ ከመብሰልሰል ይልቅ ነገሮችን በአምላክ አመለካከት ለማየት እሞክራለሁ። የእሱ ሐሳብ ከእኛ እጅግ ከፍ ያለ ነው።”—ኢሳይያስ 55:8, 9

  • ወደ አምላክ ጸልዩ። አምላክ፣ አገልጋዮቹን በተለይ በከባድ ጭንቀት በሚዋጡበት ወቅት ‘የሚያስጨንቃቸውን ነገር ሁሉ በእሱ ላይ እንዲጥሉ’ አበረታትቷቸዋል።—1 ጴጥሮስ 5:7

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ጠቃሚ ሆነው ያገኛችኋቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ወረቀት ላይ ጻፉና ብዙ ጊዜ ልታዩዋቸው በምትችሉበት ቦታ አስቀምጧቸው። ትዳራቸው በፍቺ የፈረሰ ብዙ ግለሰቦች ከላይ ከተጠቀሱት ጥቅሶች በተጨማሪ የሚከተሉትን ጥቅሶች ጠቃሚ ሆነው አግኝተዋቸዋል፦ መዝሙር 27:10፤ 34:18፤ ኢሳይያስ 41:10 እና ሮም 8:38, 39

አስቸጋሪ በሆኑ ጊዜያት ብርታት ለማግኘት የአምላክን ቃል ተመልከቱ

ተፈታታኝ ሁኔታ 2፦ ከቀድሞ የትዳር ጓደኛችሁ ጋር የሚኖራችሁ ግንኙነት

ለ11 ዓመታት በትዳር የቆየችው ጁልያና እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴን ጥሎኝ እንዳይሄድ ለምኜው ነበር። ከሄደ በኋላ ግን  እሱም ሆነ አብራው የምትኖረው ሴት አስጠሉኝ።” ትዳራቸው በፍቺ የፈረሰ ብዙ ሰዎች፣ በቀድሞ የትዳር ጓደኛቸው ላይ ያደረባቸው የቁጣ ስሜት ለዓመታት ይዘልቃል። ችግሩ ደግሞ በተለይ ልጆች ካሏቸው በየጊዜው መነጋገር የሚጠይቁባቸው ነገሮች ያጋጥሟቸዋል።

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

  • ከቀድሞ የትዳር ጓደኛችሁ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖራችሁ አድርጉ። አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ አተኩሩ፤ ንግግራችሁ አጭር እንዲሆንና ከዋናው ጉዳይ እንዳይወጣ ጥረት አድርጉ። ብዙዎች እንዲህ ያለው አካሄድ ለሰላም አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተገንዝበዋል።—ሮም 12:18

  • የሚያስቆጣ ነገር አትናገሩ። በተለይ ጥቃት እንደተሰነዘረባችሁ በሚሰማችሁ ጊዜ “ዐዋቂ ሰው ንግግሩ ቍጥብ ነው” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ ማድረጉ ጥበብ ነው። (ምሳሌ 17:27) ውይይቱ ሰላማዊ እንዲሆን ያደረጋችሁት ጥረት ካልተሳካላችሁ “ስለ ጉዳዩ ላስብበትና ሌላ ጊዜ እንነጋገር” በሉ።

  • ከቀድሞ የትዳር ጓደኛችሁ ጋር የሚያነካኳችሁን ጉዳዮች በተቻላችሁ መጠን ለመቀነስ ሞክሩ፤ ይህም ከሕግ፣ ከገንዘብና ከሕክምና ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ጉዳዮችን ይጨምራል።

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ከቀድሞ የትዳር ጓደኛችሁ ጋር ስትነጋገሩ ከሁለት አንዳችሁ እየተቆጣችሁ እንደሆነ ወይም ምክንያታዊ እንዳልሆናችሁ ከተሰማችሁ ሁኔታውን ለማስተካከል ሞክሩ። አስፈላጊ ከሆነ ለጊዜው ውይይቱን ለማቋረጥ ሐሳብ አቅርቡ፤ ወይም ጉዳዩን በኢ-ሜይል ተነጋገሩበት።—ምሳሌ 17:14

ተፈታታኝ ሁኔታ 3፦ ልጆቻችሁ ሁኔታውን እንዲለምዱት መርዳት

ማርያ ከባለቤቷ ጋር የተፋታች ሰሞን ሁኔታው ምን ይመስል እንደነበረ ስታስታውስ እንዲህ ብላለች፦ “ትንሿ ልጄ ሁልጊዜ ታለቅስ ነበር፤ እንደገና አልጋ ላይ መሽናትም ጀመረች። ትልቋ ልጄ ስሜቷን ለመደበቅ ብትሞክርም እሷም ላይ ለውጥ መኖሩን ማየት እችል ነበር።” የሚያሳዝነው ደግሞ ልጆቻችሁ የእናንተ እርዳታ በጣም በሚያስፈልጋቸው በዚህ ጊዜ ይህን ለማድረግ ጊዜውም ሆነ ጥንካሬው እንደሌላችሁ ይሰማችሁ ይሆናል።

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

  • ልጆቻችሁ ስሜታቸውን አውጥተው እንዲናገሩ አበረታቷቸው፤ አንዳንድ ጊዜ ‘ኃይለ ቃል’ ቢናገሩ እንኳ ስሜታቸውን መግለጻቸው ተገቢ ነው።—ኢዮብ 6:2, 3

  • የራሳችሁን ድርሻ ተወጡ። ስሜታዊ ድጋፍ የሚሰጣችሁ ሰው ቢያስፈልጋችሁና ልጃችሁም እንዲህ ዓይነቱን ድጋፍ ለመስጠት ፈቃደኛ ቢሆን እንኳ ልጅ በትላልቅ ሰዎች ችግር ውስጥ ገብቶ እንዲያግዝ መጠየቅ ተገቢም ሆነ ጠቃሚ አይደለም። (1 ቆሮንቶስ 13:11) ልጃችሁ ሚስጥረኛችሁ እንዲሆን ወይም በእናንተና በቀድሞ የትዳር ጓደኛችሁ መካከል አስታራቂ ወይም መልእክተኛ እንዲሆን አታድርጉ።

  • ፍቺው የልጆቻችሁን ሕይወት እንዳያተራምሰው ጥረት አድርጉ። ቤታችሁን አለመቀየራችሁ እና የቀድሞ ፕሮግራማችሁ እንዲቀጥል ማድረጋችሁ ጠቃሚ ነው፤ ከሁሉ በላይ ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብንና የቤተሰብ አምልኮን ጨምሮ ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ እንዲኖራችሁ ጥረት አድርጉ።—ዘዳግም 6:6-9

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ በዚህ ሳምንት ውስጥ፣ ለልጆቻችሁ እንደምትወዷቸው ንገሯቸው፤ እንዲሁም ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር የተፋታችሁት በእነሱ ምክንያት እንዳልሆነ አረጋግጡላቸው። ሌላውን የትዳር ጓደኛ ሳትወቅሱ ጥያቄዎቻቸውን መልሱላቸው።

ትዳራችሁ ቢፈርስም ፍቺ የሚያስከትለውን ጫና ተቋቁማችሁ ሕይወታችሁን መምራት ትችላላችሁ። ለ16 ዓመታት በትዳር የቆየችው ሜሊሳ “ከባለቤቴ ጋር ስፋታ ‘እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጥመኛል ብዬ ጨርሶ አልጠበቅሁም ነበር’ ብዬ አሰብኩ” በማለት ተናግራለች። አሁን ግን ያጋጠማትን ሁኔታ ተቋቁማ እርካታ ያለው ሕይወት መምራት ችላለች። “ያለፈውን ጊዜ ለመለወጥ መሞከሬን ስተው ስሜቴ ተረጋጋ” ብላለች።

^ አን.2 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.18 አምላክ፣ የትዳር ጓደኛን በማታለል እና በተንኮል የሚፈጸሙ ፍቺዎችን ይጠላል። ይሁንና አንደኛው ወገን ዝሙት ከፈጸመ ንጹሕ የሆነው ወገን የመፍታት ነፃነት እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ሚልክያስ 2:16፤ ማቴዎስ 19:9) በየካቲት 8, 1994 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?—አምላክ የሚጠላው ምን ዓይነት ፍቺን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

ራሳችሁን እንዲህ እያላችሁ ጠይቁ . . .

  • በፍቺው ምክንያት የተሰማኝ ሐዘን እንዲወጣልኝ ለራሴ ጊዜ ሰጥቻለሁ?

  • በቀድሞ የትዳር ጓደኛዬ ላይ ያለኝን ቅሬታ መተው የምችለው እንዴት ነው?