በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

“እውነቱ ምን እንደሆነ ራሴ እንዳረጋግጥ ፈልገው ነበር”

“እውነቱ ምን እንደሆነ ራሴ እንዳረጋግጥ ፈልገው ነበር”
  • የትውልድ ዘመን፦ 1982
  • የትውልድ አገር፦ ዶሚኒካን ሪፑብሊክ
  • የኋላ ታሪክ፦ በሞርሞን ሃይማኖት ውስጥ ያደገ

የቀድሞ ሕይወቴ፦

የተወለድኩት በሳንቶ ዶሚንጎ፣ ዶሚኒካን ሪፑብሊክ ውስጥ ሲሆን ከአራት ልጆች መካከል የመጨረሻው ነኝ። ወላጆቼ የተማሩ ሰዎች ናቸው፤ እኛንም ጥሩ አድርገው ያሳደጉን ሲሆን መልካም ሥነ ምግባር ካላቸውና ሐቀኛ ከሆኑ ሰዎች ጋር እንድንቀራረብ ለማድረግ ይጥሩ ነበር። ከመወለዴ ከአራት ዓመታት በፊት ወላጆቼ ከሞርሞን ሚስዮናውያን ጋር ተገናኙ። ወላጆቼ በዚህ እምነት ውስጥ ባሉ ወጣት ወንዶች የፀጉር አያያዝ፣ አለባበስና መልካም ምግባር ስለተደነቁ ቤተሰባችን የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የሚባለው የሞርሞን ቤተ ክርስቲያን አባላት እንዲሆን ወሰኑ፤ ቤተሰባችን በዶሚኒካን ሪፑብሊክ ውስጥ ከመጀመሪያዎቹ የዚህ ቤተ ክርስቲያን አባላት መካከል አንዱ ነው።

እያደግኩ ስሄድ ቤተ ክርስቲያኑ በሚያደርገው ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች እደሰት ጀመር፤ እንዲሁም የቤተሰብ ሕይወትንና የሥነ ምግባር መመሪያዎችን በተመለከተ ለሚሰጠው ትምህርት አክብሮት ነበረኝ። ሞርሞን በመሆኔ እኮራ የነበረ ሲሆን ሚስዮናዊ ለመሆንም ግብ አወጣሁ።

ዕድሜዬ 18 ዓመት ሲሆን የኮሌጅ ትምህርት መከታተል እንድችል ቤተሰቤ በዩናይትድ ስቴትስ መኖር ጀመረ። አንድ ዓመት ገደማ ካለፈ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑት አክስቴና ባለቤቷ ሊጎበኙን ወደ ፍሎሪዳ መጡ። እነሱም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት በሚሰጥበት አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ እንድንገኝ ጋበዙን። በስብሰባው ላይ፣ በዙሪያዬ ያሉት ሁሉ ጥቅስ እያወጡ ሲከታተሉና ማስታወሻ ሲይዙ በመመልከቴ ተደነቅሁ። እኔም እስክሪብቶና ወረቀት ጠይቄ እንደነሱ መጻፍ ጀመርኩ።

ሚስዮናዊ የመሆን ፍላጎት ያለኝ እንደመሆኑ መጠን አክስቴና ባለቤቷ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ነገሮችን እንዳውቅ ሊረዱኝ እንደሚችሉ ከስብሰባው በኋላ ነገሩኝ። በወቅቱ በደንብ የማውቀው የሞርሞንን መጽሐፍ እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን ስላልሆነ ሐሳባቸው ጥሩ እንደሆነ ተሰማኝ።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

ከአክስቴና ከባለቤቷ ጋር በስልክ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት በምናደርግበት ወቅት ሁልጊዜ እምነቴን መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ትምህርት ጋር እንዳነጻጽር ያበረታቱኝ ነበር። እውነቱ ምን እንደሆነ ራሴ እንዳረጋግጥ ፈልገው ነበር።

 በሞርሞን እምነት ውስጥ የተቀበልኳቸው ብዙ ትምህርቶች ቢኖሩም ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር ትክክል ስለመሆናቸው ግን እርግጠኛ አልነበርኩም። አክስቴ ስለ ሞርሞን እምነት የሚናገሩ አንዳንድ ርዕሶችን የያዘውንና በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የኅዳር 8, 1995 ንቁ! መጽሔት (እንግሊዝኛ) ላከችልኝ። ብዙ የማላውቃቸው የሞርሞን ትምህርቶች እንዳሉ ሳውቅ ተገረምኩ። ይህም በሞርሞኖች ሕጋዊ ድረ ገጽ አማካኝነት ምርምር ለማድረግና በንቁ! መጽሔቱ ላይ የተገለጸው ነገር እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ አነሳሳኝ። ደግሞም መጽሔቱ ላይ ያለውን ሐሳብ እውነት ሆኖ አገኘሁት። ከዚህም ሌላ በዩታ የሚገኙትን የሞርሞን ሙዚየሞች ስጎበኝ በመጽሔቱ ላይ ስለተገለጹት ሐሳቦች ትክክለኝነት ተጨማሪ ማረጋገጫ አገኘሁ።

ከዚህ በፊት፣ የሞርሞን መጽሐፍና መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርስ እንደሚደጋገፉ ይሰማኝ ነበር። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ማንበብ ስጀምር የሞርሞን ትምህርቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንደሚጋጩ አስተዋልኩ። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ በሕዝቅኤል 18:4 ላይ ነፍስ እንደምትሞት ይናገራል። የሞርሞን መጽሐፍ ግን በአልማ 42:9 ላይ “ነፍስ በጭራሽ ልትሞት [አትችልም]” ይላል።

ከመሠረተ ትምህርት ልዩነት በተጨማሪ ሞርሞኖች የሚያስተምሩት ብሔራዊ ስሜት የሚንጸባረቅበት ሐሳብ ይረብሸኝ ነበር። ለምሳሌ ሞርሞኖች ኤደን ገነት በሚዙሪ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በምትገኘው ጃክሰን ካንትሪ ውስጥ እንደነበረች ያምናሉ። በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያኒቱ ነቢያት፣ የአምላክ መንግሥት መግዛት ሲጀምር የዩናይትድ ስቴትስ ባንዲራ ከፍ ብሎ እንደሚውለበለብ እንዲሁም ነፃነትና የእኩልነት መብቶች እንደሚከበሩ ይናገራሉ።

ከዚህ የሞርሞን ትምህርት አንጻር የትውልድ አገሬም ሆነ ሌሎች አገሮች ስለሚኖራቸው ዕጣ ፈንታ አስብ ነበር። አንድ ቀን በሚስዮናዊነት ሥልጠና ላይ የነበረ አንድ የሞርሞን እምነት ተከታይ የሆነ ወጣት ስልክ ሲደውልልኝ ይህን ርዕሰ ጉዳይ አነሳሁለት። የእሱ አገር ከሌላ ጋር ጦርነት ብትገጥም የእምነት አጋሮቹ ከሆኑ ሞርሞኖች ጋር ለመዋጋት ፈቃደኛ ይሆን እንደሆነ በግልጽ ጠየቅሁት። እሱም እንደሚዋጋ ሲገልጽልኝ በጣም ገረመኝ! ሃይማኖቴ የሚያስተምራቸውን ነገሮች በጥልቅ ከመመርመሬም በላይ ጥያቄዎቼን በኃላፊነት ቦታ ላይ ለሚገኙ የሞርሞን ቤተ ክርስቲያን መሪዎች አቀረብኩ። ጥያቄዎቼ ሚስጥር ከሚባሉት ነገሮች መካከል እንደሆኑና አንድ ቀን ብርሃኑ ደምቆ ሲበራ እነዚህ ሚስጥሮች እንደሚፈቱ ተነገረኝ።

እነዚህ ሰዎች የሰጡኝ ማብራሪያ ስላላስደሰተኝ ስለ ራሴም ሆነ የሞርሞን ሚስዮናዊ መሆን ስለፈለግኩበት ምክንያት ቆም ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። በዚህ ጊዜ፣ ሚስዮናዊ ለመሆን የፈለግኩበት አንዱ ምክንያት በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ መሰማራት ስለምፈልግ እንደሆነ ገባኝ። በሰዎች ዘንድ አክብሮት ለማትረፍ ያለኝ ፍላጎትም ሚስዮናዊ ለመሆን እንዳነሳሳኝ ተረዳሁ። አምላክን በተመለከተ የነበረኝ እውቀት ግን በጣም ውስን ነበር። ከዚህ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን ብዙ ጊዜ ባነብበውም ያለውን ዋጋ አልተረዳሁም ነበር። አምላክ ለምድርም ሆነ ለሰው ዘር ስለነበረው ዓላማ የማውቀው ነገር አልነበረም።

ያገኘሁት ጥቅም፦

መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ሳጠና የአምላክ ስም ማን እንደሆነ፣ ስንሞት ምን እንደምንሆንና የአምላክን ዓላማ ከፍጻሜ በማድረስ ረገድ ኢየሱስ ያለውን ሚና ጨምሮ በርካታ ነገሮችን ተምሬያለሁ። በመጨረሻም ይህ ድንቅ መጽሐፍ የያዘውን ሐሳብ በደንብ ማወቅ የቻልኩ ከመሆኑም በላይ የተማርኩትን ነገር ለሌሎች ማካፈል ጀመርኩ። የአምላክን መኖር ተጠራጥሬ ባላውቅም እንደ ቅርብ ወዳጄ አድርጌ በጸሎት አማካኝነት እሱን ማነጋገር የጀመርኩት ግን ከዚህ ጊዜ በኋላ ነበር። ሐምሌ 12, 2004 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩኝ፤ ከስድስት ወራት በኋላ ደግሞ ሙሉ ጊዜዬን በክርስቲያናዊ አገልግሎት ማሳለፍ ጀመርኩ።

ለአምስት ዓመታት ያህል በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ ሠርቻለሁ። በዓለም ዙሪያ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚጠቅሙ መጽሐፍ ቅዱሶችንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በማተሙ ሥራ መካፈል በመቻሌ እንዲሁም ሌሎች ስለ አምላክ እንዲማሩ እየረዳሁ በመሆኔ በጣም ደስተኛ ነኝ።