በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?

ልጃችሁ የጤና እክል ቢኖርበት

ልጃችሁ የጤና እክል ቢኖርበት

ካርሎ፦ * “ልጃችን አንጀሎ ‘ዳውን ሲንድሮም’ የተባለ በሽታ አለበት። የእሱ መታመም አካላዊ፣ አእምሯዊና ስሜታዊ ጥንካሬያችንን አሟጥጦታል። አንድ ጤነኛ ልጅ ለማሳደግ የሚያስፈልገውን ኃይል አስቡትና ይህን በመቶ በማባዛት፣ የጤና እክል ያለበት ልጅ ማሳደግ የሚጠይቀውን ኃይል መገመት ትችላላችሁ። ትዳራችን ውጥረት ውስጥ የሚገባበት ጊዜም አለ።”

ሚያ፦ “አንጀሎን በጣም ቀላል የሆነ ነገር ለማስተማር እንኳ ከፍተኛ ጽናትና ትዕግሥት ይጠይቃል። በጣም ሲደክመኝ ትንሽ ነገር ስለሚያበሳጨኝ በባለቤቴ በካርሎ ላይ መነጫነጭ እጀምራለሁ። አንዳንድ ጊዜ በምንነጋገርባቸው ጉዳዮች ላይ ስለማንስማማ ውይይታችን ወደ ጭቅጭቅ ይቀየራል።”

ልጃችሁ የተወለደበትን ዕለት ታስታውሳላችሁ? በወቅቱ ልጃችሁን ለማቀፍ ጓግታችሁ እንደነበረ ጥርጥር የለውም። እንደ ካርሎና ሚያ ያሉ ወላጆች ግን ልጃቸው እንደታመመ ወይም የጤና እክል እንዳለበት ሲነገራቸው ደስታቸው ወደ ጭንቀት ይለወጣል።

የጤና እክል ያለበት ልጅ አላችሁ? ከሆነ ሁኔታውን መቋቋም ስለመቻላችሁ ታስቡ ይሆናል። እንግዲያው ተስፋ አትቁረጡ። ሌሎች ወላጆች ተመሳሳይ ችግሮችን በተሳካ ሁኔታ መወጣት ችለዋል። ሊያጋጥሟችሁ የሚችሉ ሦስት የተለመዱ ተፈታታኝ ሁኔታዎችንና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጥበብ የተንጸባረቀበት ምክር እንዴት ሊረዳችሁ እንደሚችል እስቲ እንመልከት።

ተፈታታኝ ሁኔታ 1፦ የሕክምና ምርመራውን ውጤት ለመቀበል መቸገር።

ብዙ ወላጆች ልጃቸው እንደታመመ ሲያውቁ ቅስማቸው ይሰበራል። “ልጃችን ሳንቲያጎ፣ ሴሬብራል ፓልሲ የተባለ በአንጎል መጎዳት ምክንያት የሚመጣ በሽታ እንዳለበት ሐኪሞቹ ሲነግሩኝ ማመን ከብዶኝ ነበር። ሰማይ ምድሩ ዞረብኝ” በማለት ጁሊያና የተባለች በሜክሲኮ የምትኖር አንዲት እናት ተናግራለች። ሌሎች ደግሞ ቪላና እንደምትባለው ጣሊያናዊት እናት ይሰማቸው ይሆናል። ቪላና እንዲህ ብላለች፦ “በእኔ ዕድሜ ያሉ ሴቶች፣ ልጅ መውለዳቸው አደገኛ እንደሆነ ባውቅም ለመውለድ ወሰንኩ። ልጄ በዳውን ሲንድሮም ምክንያት በሚመጡ የተለያዩ ችግሮች እየተሠቃየ  እንደሆነ ስመለከት ሁልጊዜ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኛል።”

ከተስፋ መቁረጥ ወይም ከጥፋተኝነት ስሜት ጋር እየታገላችሁ ነው? እንዲህ ቢሰማችሁ የሚገርም አይደለም። ምክንያቱም አምላክ ሰዎችን የፈጠረው እንዲታመሙ አይደለም። (ዘፍጥረት 1:27, 28) እንዲሁም ወላጆች ተፈጥሯዊ ያልሆነን ነገር በቀላሉ እንዲቀበሉ አድርጎ አልፈጠራቸውም። በሌላ አነጋገር፣ የልጃችሁ ጤንነት በመጓደሉ በጥልቅ ማዘናችሁ ተገቢ ነው። ልጃችሁ እንደታመመ አምናችሁ ለመቀበልና ይህን ስሜት ለመቋቋም ጊዜ ይወስድባችኋል።

በልጃችሁ ላይ ለደረሰው የአካል ጉዳት ተጠያቂዎቹ እናንተ እንደሆናችሁ ቢሰማችሁስ? የዘር ውርስ፣ አካባቢና ሌሎች ነገሮች በአንድ ልጅ ጤንነት ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ ሙሉ በሙሉ ማወቅ የሚችል ሰው እንደሌለ አስታውሱ። በሌላ በኩል ደግሞ የትዳር ጓደኛችሁን ተጠያቂ ወደማድረግ ታዘነብሉ ይሆናል። ሆኖም እንዲህ ልታደርጉ አይገባም። ከዚህ ይልቅ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር በመተባበር ልጃችሁን በመንከባከብ ላይ ብታተኩሩ የተሻለ ነው።—መክብብ 4:9, 10

የመፍትሔ ሐሳብ፦ ስለ ልጃችሁ የጤና ችግር ለማወቅ ጥረት አድርጉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ጥሩ ቤተሰብ እንዲኖር ጥበብ ያስፈልጋል፤ ቤተሰቡ ጠንካራ እንዲሆን ማድረግም ማስተዋል ይጠይቃል” ይላል።—ምሳሌ 24:3 ኒው ሴንቸሪ ቨርዥን

ከሕክምና ባለሙያዎችና እምነት ከሚጣልባቸው ጽሑፎች ብዙ ነገር መማር ትችላላችሁ። ስለ ልጃችሁ የጤና ችግር ለማወቅ የምታደርጉት ጥረት አንድን አዲስ ቋንቋ ጠንቅቆ ለመማር ከሚደረገው ጥረት ጋር ተመሳሳይ ነው። መጀመሪያ ላይ ከባድ ቢሆንም መማር ግን ይቻላል።

በመግቢያው ላይ የተጠቀሱት ካርሎና ሚያ ከሐኪማቸውና ስለ ልጃቸው የጤና ችግር ዝርዝር መረጃ መስጠት ከሚችል አንድ ድርጅት ጠቃሚ ምክር ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። እንዲህ ብለዋል፦ “ይህን ማድረጋችን ሊያጋጥሙን የሚችሉ ችግሮችን ብቻ ሳይሆን ዳውን ሲንድሮም ያለበት ሰው ማከናወን የሚችላቸውንም ነገሮች እንድናውቅ ረድቶናል። ልጃችን ጤናማ የሆነ ሰው ሊያደርጋቸው የሚችላቸውን ብዙ ነገሮች ማከናወን እንደሚችል ተገንዝበናል። ይህ ደግሞ በጣም አጽናንቶናል።”

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ልጃችሁ ማከናወን በሚችላቸው ነገሮች ላይ ትኩረት አድርጉ። በቤተሰብ ደረጃ በአንዳንድ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል ዕቅድ አውጡ። አነስተኛ ቢሆንም እንኳ፣ ልጃችሁ አንድ ነገር ሲያከናውን አመስግኑት፤ እንዲሁም አብራችሁ ተደሰቱ።

ተፈታታኝ ሁኔታ 2፦ መዛልና ስሜታችሁን የምትገልጹለት ሰው ማጣት።

ለታመመ ልጃችሁ እንክብካቤ ማድረግ ጉልበታችሁን ሁሉ እንዳሟጠጠው ሊሰማችሁ ይችላል። ጄኒ የምትባል በኒው ዚላንድ የምትኖር አንዲት እናት እንዲህ ብላለች፦ “ልጄ ስፓይና ቢፊዳ የሚባል የነርቭ እክል እንዳለበት በሐኪም ምርመራ ታወቀ፤ ከዚያ በኋላ በነበሩት ጥቂት ዓመታት፣ ቤት ውስጥ ከወትሮው የተለየ ነገር ለመሥራት ከሞከርኩ በጣም ይደክመኝ ነበር፤ እንዲሁም አልቅሽ አልቅሽ ይለኝ ነበር።”

በሌላ በኩል ደግሞ ስሜታችሁን የምትገልጹለት ሰው እንዳጣችሁ ይሰማችሁ ይሆናል። ቤን፣ መስኩላር ዲስትሮፊ በሚባል ጡንቻን የሚያዝል በሽታ እንዲሁም አስፐርገርስ ሲንድሮም በተባለ የአእምሮ ችግር የሚሠቃይ ልጅ አለው። “ብዙ ሰዎች ያለንበትን ሁኔታ ፈጽሞ ሊረዱ አይችሉም” ብሏል። የምታወያዩት ሰው የምትፈልጉበት ጊዜ አለ። ሆኖም አብዛኞቹ ወዳጆቻችሁ ጤነኛ ልጆች ያሏቸው ይሆናሉ። በመሆኑም ለእነሱ ስሜታችሁን መግለጽ ይከብዳችኋል።

የመፍትሔ ሐሳብ፦ እርዳታ ጠይቁ። ሰዎች የሚሰጧችሁን እርዳታም ተቀበሉ። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ጁሊያና “አንዳንድ ጊዜ እኔና ባለቤቴ እርዳታ መጠየቅ ያሳፍረናል” በማለት በግልጽ ተናግራለች። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “በራሳችን ብቻ ሁሉንም ነገር ማከናወን እንደማንችል ተረድተናል። ሌሎች ሲረዱን ብቸኝነት አይሰማንም።” አንድ የቅርብ ወዳጃችሁ ወይም የቤተሰብ አባል በአንድ ማኅበራዊ ግብዣ ወይም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከልጃችሁ ጋር ተቀምጦ እሱን ለመርዳት ቢጠይቃችሁ እገዛውን በአመስጋኝነት ተቀበሉ። “ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው፤ ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል” በማለት አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ይናገራል።—ምሳሌ 17:17

የራሳችሁን ጤንነትም ጠብቁ። አንድ አምቡላንስ በሽተኞችን ወደ ሆስፒታል መውሰዱን እንዲቀጥል ከተፈለገ ምንጊዜም ነዳጅ መሙላት እንዳለበት ሁሉ እናንተም ለልጃችሁ ተገቢውን እንክብካቤ እያደረጋችሁ ለመቀጠል ኃይላችሁን ማደስ ይኖርባችኋል፤ ለዚህ ደግሞ ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት መከተል፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግና እረፍት መውሰድ ጠቃሚ ነው። ካቪየር የተባለ የአካል ጉዳተኛ የሆነ ልጅ ያለው አንድ ወላጅ ሁኔታውን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ልጄ መራመድ አይችልም፤ በመሆኑም እኔ በደንብ መብላት እንዳለብኝ ይሰማኛል። ምክንያቱም ይዤው ወዲያ ወዲህ የምለው እኔ ነኝ። በመሆኑም እንደ እግር የምሆንለት እኔ ነኝ!”

የራሳችሁን ጤንነት ለመጠበቅ ጊዜ ማግኘት የምትችሉት እንዴት ነው? አንዳንድ ወላጆች ልጃቸውን ለመንከባከብ ተራ ይገባሉ። በመሆኑም አንዱ ወላጅ ልጁን ሲንከባከብ ሌላኛው ደግሞ እረፍት ያደርጋል ወይም አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች ነገሮችን ያከናውናል። አላስፈላጊ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን በመቀነስ ጊዜ መግዛት ያስፈልጋችሁ ይሆናል፤ እርግጥ ነው፣ ሚዛናችሁን መጠበቅ ተፈታታኝ ሊሆንባችሁ ይችላል። ይሁን እንጂ ማዩሪ የምትባል በሕንድ የምትኖር አንዲት እናት እንደተናገረችው “ውሎ አድሮ ትለምዱታላችሁ።”

ችግራችሁን ለምትተማመኑበት ወዳጃችሁ ንገሩት። ወዳጆቻችሁ የታመመ ልጅ ባይኖራቸውም ችግራችሁን እንደራሳቸው ችግር አድርገው በማየት በርኅራኄ ሊያዳምጧችሁ ይችላሉ። ወደ ይሖዋ  መጸለይም ትችላላችሁ። በእርግጥ ጸሎት ይረዳል? ያዝሚን፣ ሲስቲክ ፋይብሮሲስ የተባለ የመተንፈሻ አካላትንና የሆድ ዕቃን የሚያጠቃ ከባድ በሽታ ያለባቸው ሁለት ልጆች አሏት፤ ያዝሚን “አንዳንድ ጊዜ በጣም ከመወጠሬ የተነሳ ታፍኜ ልሞት እንደደረስኩ ሆኖ ይሰማኛል” በማለት ተናግራለች። አክላም “እፎይታና ብርታት ለማግኘት ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ። በዚህ ጊዜ ለመቀጠል አቅም እንዳገኘሁ ይሰማኛል” ብላለች።—መዝሙር 145:18

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ስለ አመጋገባችሁ፣ ስለ እንቅልፋችሁና ስለ አካል ብቃት እንቅስቃሴ ቆም ብላችሁ ለማሰብ ሞክሩ። ጤንነታችሁን መጠበቅ እንድትችሉ አላስፈላጊ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን በመቀነስ ጊዜ ማግኘት የምትችሉት እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ሞክሩ። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ በፕሮግራማችሁ ላይ ማስተካከያ አድርጉ።

ተፈታታኝ ሁኔታ 3፦ ለታመመው ልጅ ከሌሎቹ የቤተሰብ አባላት የበለጠ ትኩረት መስጠት።

የአንድ ልጅ ሕመም ቤተሰቡ በሚበላው ነገር፣ በሚሄድበት ቦታና ወላጆች ከእያንዳንዱ ልጅ ጋር በሚያሳልፉት ጊዜ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። በዚህም የተነሳ ሌሎቹ ልጆች ችላ እንደተባሉ ይሰማቸው ይሆናል። ከዚህም በላይ ወላጆች የታመመውን ልጃቸውን በመንከባከብ በጣም ከመወጠራቸው የተነሳ ትዳራቸው ችግር ላይ ሊወድቅ ይችላል። በላይቤሪያ የሚኖር ሊዮኔል የተባለ አንድ አባት እንዲህ ብሏል፦ “ባለቤቴ አብዛኛውን ሥራ የምትሠራው እሷ እንደሆነችና እኔ ግን ለልጃችን እንደማላስብ የምትናገርበት ጊዜ አለ። እኔም አክብሮት እንዳላሳየችኝ ስለሚሰማኝ አንዳንድ ጊዜ ደግነት በጎደለው መንገድ እመልስላታለሁ።”

የመፍትሔ ሐሳብ፦ ለሁሉም ልጆቻችሁ እንደምታስቡ ለማሳየት የሚያስደስታቸውን ነገር አብራችኋቸው ለማድረግ ዕቅድ አውጡ። “አንዳንድ ጊዜ ለትልቁ ልጃችን ለየት ያለ ነገር እናደርግለታለን፤ ምናልባትም የሚወደው ምግብ ቤት ሄደን አብረን ምሳ መመገብ ብቻ ሊሆን ይችላል” በማለት ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ጄኒ ተናግራለች።

ለሁሉም ልጆቻችሁ ትኩረት ስጡ

ትዳራችሁን ለመጠበቅ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር መነጋገርና አብራችሁ መጸለይ ያስፈልጋችኋል። ልጁ በሚጥል በሽታ የሚሠቃይ አሲም የተባለ በሕንድ የሚኖር አንድ አባት እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ ጊዜ እኔና ባለቤቴ የምንበሳጭበትና ውጥረት ውስጥ የምንገባበት ጊዜ አለ፤ በዚህ ወቅት ጊዜ መድበን እናወራለን እንዲሁም እንጸልያለን። በየዕለቱ ጠዋት ላይ ልጆቻችን ከእንቅልፋቸው ከመነሳታቸው በፊት በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ለመወያየት ጊዜ መድበናል።” ሌሎች ባለትዳሮች ደግሞ ከመተኛታቸው በፊት ብቻቸውን ይጨዋወታሉ። የልባችሁን አውጥታችሁ መጨዋወታችሁና ከልብ የመነጨ ጸሎት ማቅረባችሁ በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ብትገቡም እንኳ ትዳራችሁ የተጠናከረ እንዲሆን ያደርጋል። (ምሳሌ 15:22) አንድ ባልና ሚስት “በሕይወታችን ውስጥ የማይረሳ ጊዜ ያሳለፍነው በጣም አስቸጋሪ በነበሩት ወቅቶች ነው” ብለዋል።

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ሌሎቹ ልጆች፣ የታመመውን ልጃችሁን ስትንከባከቡ ለሚያደርጉላችሁ ማንኛውም ድጋፍ አመስግኗቸው። ለእነሱም ሆነ ለትዳር ጓደኛችሁ ያላችሁን ፍቅርና አድናቆት አዘውትራችሁ ግለጹ።

ብሩሕ አመለካከት ይኑራችሁ

አምላክ፣ ሕፃን አዋቂ ሳይል በሁሉም የሰው ልጆች ላይ የሚደርሰውን ሕመምና የአካል ጉዳት በቅርቡ እንደሚያስወግድ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ራእይ 21:3, 4) በዚያ ዘመን “‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም” *ኢሳይያስ 33:24

እስከዚያው ድረስ ግን ልጃችሁ የጤና እክል ያለበት ቢሆንም እንኳ እሱን ተንከባክቦ በማሳደግ ረገድ ሊሳካላችሁ ይችላል። ቀደም ሲል የተጠቀሱት ካርሎና ሚያ እንዲህ ብለዋል፦ “ሁሉም ነገር ተስፋ የሌለው በሚመስልበት ጊዜም እንኳ ተስፋ አትቁረጡ። ልጃችሁ ብዙ መልካም ነገሮች ስላሉት በእነዚያ ድንቅ ነገሮች ላይ አተኩሩ።”

^ စာပိုဒ်၊ 3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።

^ စာပိုဒ်၊ 29 መጽሐፍ ቅዱስ ፍጹም ጤንነትን አስመልክቶ ስለሚሰጠው ተስፋ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 3 ማንበብ ትችላለህ።

ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦

  • አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ጤንነቴን በተቻለኝ መጠን ለመጠበቅ ምን እያደረግኩ ነው?
  • ሌሎቹ ልጆቼ ለሰጡኝ እርዳታ ለመጨረሻ ጊዜ ያመሰገንኳቸው መቼ ነው?