በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?

ልጅ መውለድ በትዳር ላይ የሚያመጣው ለውጥ

ልጅ መውለድ በትዳር ላይ የሚያመጣው ለውጥ

ቻርልስ፦ * “እኔና ሜሪ ሴት ልጃችን ስትወለድ በጣም ተደስተን ነበር። ይሁን እንጂ እሷ ከተወለደች በኋላ በነበሩት የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት እንቅልፍ መተኛት አልቻልኩም። እሷን በጥሩ መንገድ ለማሳደግ ያላወጣነው እቅድ አልነበረም፤ ብዙም ሳይቆይ ግን ያ ሁሉ እቅድ መና ቀረ።”

ሜሪ፦ “ልጃችን ከተወለደች በኋላ ለራሴ መኖር አቆምኩ። ሥራዬ ሁሉ ጡጦ ማዘጋጀት፣ ሽንት ጨርቅ መቀየርና ልጄን ማባበል ሆነ። ለውጡ በጣም ከፍተኛ ነበር። ከቻርልስ ጋር የነበረኝ ግንኙነት ወደ ድሮው እስኪመለስ ድረስ ወራት ወስዶብኛል።”

ልጅ መውለድ በሕይወት ውስጥ እጅግ አስደሳች ከሆኑት ነገሮች አንዱ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። መጽሐፍ ቅዱስም ልጆችን ከአምላክ የተገኙ “ስጦታ” እንደሆኑ አድርጎ ይገልጻቸዋል። (መዝሙር 127:3) ገና የመጀመሪያ ልጃቸውን የወለዱ እንደ ቻርልስና ሜሪ ያሉ ወላጆች ደግሞ ልጆች ትዳርን ባልተጠበቀ መንገድ ሊለውጡት እንደሚችሉም ያውቃሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት አዲስ እናት ትኩረቷ ሁሉ በልጇ ላይ ሊያርፍ ይችላል፤ እናም አራስ ልጇ ለሚያሰማው ድምፅ ቅጽበታዊ የሆነ ምላሽ መስጠቷ ያስገርማት ይሆናል። አዲሱ አባት ደግሞ በሚስቱና በሕፃኑ መካከል የሚኖረው ትስስር ያስደንቀው ይሆናል። በሌላ በኩል ግን በድንገት መረሳቱ ሊያስጨንቀው ይችላል።

እንዲያውም አንዳንድ ባልና ሚስቶች የመጀመሪያ ልጃቸውን ሲወልዱ በትዳራቸው ውስጥ ያለው ችግር ሊባባስ ይችላል። ወላጅ መሆን በሚፈጥረው ውጥረት ሳቢያ ባልና ሚስቱ ከስሜት ጋር በተያያዘ ያሉባቸው የግል ድክመቶችና በመካከላቸው ያሉ መፍትሔ ያላገኙ ችግሮች ይበልጥ ይፋ ሊወጡ ይችላሉ።

ታዲያ አዲስ ወላጆች አራስ ልጃቸው መላ ትኩረታቸውን በሚፈልግበት በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት ከሚያጋጥማቸው ውጥረት የሞላበት ሕይወት ጋር መላመድ የሚችሉት እንዴት ነው? ባልና ሚስቱ እርስ በርስ ያላቸውን ቅርበት ለመጠበቅ ምን ማድረግ ይችላሉ? ልጅ ከማሳደግ ጋር የተያያዙ አለመግባባቶችንስ እንዴት መፍታት ይችላሉ? እስቲ እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች አንድ በአንድ እንመርምራቸው፤ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ችግሮቹን ለመፍታት ሊረዷቸው የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

ተፈታታኝ ሁኔታ 1፦ ትኩረታቸው ሁሉ በልጁ ዙሪያ ያጠነጠነ መሆኑ።

አንድ ሕፃን የእናቱን ሙሉ ጊዜ ሊወስድና ሐሳቧን ሁሉ ሊሰርቅባት ይችላል። እርግጥ ነው፣ እናቲቱ ልጇን በመንከባከብ ጥልቅ የሆነ ስሜታዊ እርካታ ይሰማት ይሆናል። ባሏ ግን ችላ እንደተባለ ሊሰማው ይችላል። በብራዚል የሚኖረው ማኑዌል እንዲህ ይላል፦ “ለመቀበል እጅግ የከበደኝ ነገር ቢኖር ሚስቴ ለእኔ የምትሰጠኝን ትኩረት ወደ ልጃችን ማዞሯ ነበር። ቀደም ሲል ከእኔ ሌላ ማንም አልነበራትም፤ ከዚያም ሁኔታዎች በድንገት ተለወጡና ለልጇ ብቻ ማሰብ ጀመረች።” ታዲያ እንዲህ ያለውን ዱብ ዕዳ መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው?

ቁልፉ፦ ታጋሽ ሁኑ።

መጽሐፍ ቅዱስ “ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው። . . . የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም [እንዲሁም] አይበሳጭም” በማለት ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 13:4, 5) ታዲያ አንድ ባልና ሚስት ልጅ በሚወልዱበት ጊዜ ይህንን ምክር በሥራ ላይ ለማዋል ሁለቱም በበኩላቸው ምን ማድረግ ይችላሉ?

ጥበበኛ የሆነ ባል፣ ልጅ መውለድ በሴቶች አካል ላይም ሆነ በአእምሯቸው ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለማወቅ በመጣር ለሚስቱ ፍቅር እንዳለው ያሳያል። እንዲህ ካደረገ ሚስቱ ጠባይዋ ቶሎ ቶሎ የሚለዋወጠው ለምን እንደሆነ ይረዳል። * የ11 ወር ሴት ልጅ አባት የሆነውና በፈረንሳይ የሚኖረው አዳም እንደሚከተለው በማለት የተሰማውን ሳይደብቅ ተናግሯል፦ “ባለቤቴ ጠባይዋ ሲለዋወጥ አንዳንድ ጊዜ ስሜቷን መረዳትም ሆነ እሷን መታገሥ አስቸጋሪ ይሆንብኛል። ይሁን እንጂ የምትበሳጨው በእኔ እንዳልሆነ ለማስታወስ እሞክራለሁ። እንዲህ የምትሆነው አዲሱ ሁኔታችን ባመጣው ያልታሰበ ውጥረት ምክንያት ነው።”

ባለቤትህ እሷን ለመርዳት የምታደርገውን ጥረት ሳትረዳልህ የምትቀርበት ጊዜ ይኖር ይሆን? ከሆነ ቶሎ አትበሳጭ። (መክብብ 7:9) ከዚህ ይልቅ ለራስህ የሚመችህን ብቻ ሳይሆን ለእሷ የሚጠቅማትን ነገር የምታስብ ከሆነ ከመናደድ ትድናለህ።​—ምሳሌ 14:29

በሌላ በኩል ደግሞ አንዲት አስተዋይ ሚስት ባሏ አዲሱን ኃላፊነቱን እንዲወጣ ለማበረታታት ጥረት ታደርጋለች። ባሏ መጀመሪያ ላይ የሚደነባበር ቢመስልም የሽንት ጨርቅ እንዴት እንደሚቀይር ወይም ለሕፃኑ ጡጦ እንዴት እንደሚያዘጋጅ በትዕግሥት በማሳየት ልጁን በመንከባከቡ ሥራ ታሳትፈዋለች።

ኤለን የተባለች የ26 ዓመት ዕድሜ ያላት አንዲት እናት ባሏን በምትይዝበት መንገድ ላይ አንዳንድ ማስተካከያ ማድረግ እንደሚያስፈልጋት ተገነዘበች። “ልጃችን የእኔ ብቻ እንደሆነች አድርጌ መመልከቴን ማቆም ነበረብኝ” ብላለች። “እንዲሁም ባለቤቴ ሕፃኗን እንዴት እንደሚንከባከብ የሰጠሁትን ሐሳብ ተግባራዊ ለማድረግ በሚጥርበት ጊዜ ጥቃቅን ስህተት መለቃቀም እንደሌለብኝ ለራሴ ደጋግሜ መንገር አስፈልጎኛል።”

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ እናንት ሚስቶች፣ ባለቤታችሁ እናንተ ከምታደርጉት በተለየ መንገድ ለልጁ እንክብካቤ የሚያደርግ ከሆነ እሱን ለመንቀፍ ወይም ከእሱ ተቀብላችሁ ሥራውን እንደገና ራሳችሁ ለመሥራት የሚገፋፋችሁን ስሜት ተቋቋሙ። ከዚህ ይልቅ ለሠራው ሥራ አመስግኑት፤ እንዲህ ካደረጋችሁ በራስ የመተማመን መንፈሱን የምታሳድጉለት ሲሆን የሚያስፈልጋችሁን ድጋፍ ለመስጠትም ይበረታታል። እናንት ባሎች፣ በተለይ ሕፃኑ ከተወለደ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት ውስጥ ሚስታችሁን ለመርዳት የሚያስችል ተጨማሪ ጊዜ እንድታገኙ እምብዛም አስፈላጊ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎችን ቀንሱ።

ተፈታታኝ ሁኔታ 2፦ እየተራራቃችሁ መምጣታችሁ።

ብዙ ወላጆች ጥሩ እንቅልፍ ባለማግኘት እንዲሁም በሌሎች ያልተጠበቁ ችግሮች የተነሳ ኃይላቸው ስለሚሟጠጥ በመካከላቸው መራራቅ እንዳይፈጠር መታገል ጠይቆባቸዋል። የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ፈረንሳዊቷ ቪቪያን እንዲህ በማለት በግልጽ ተናግራለች፦ “መጀመሪያ አካባቢ በእናትነት ኃላፊነቴ ላይ በጣም አተኩሬ ስለነበር የሚስትነት ድርሻዬን ረስቼው ነበር ለማለት ይቻላል።”

በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ባል፣ እርግዝና በሚስቱ አካልም ሆነ በስሜቷ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ሳይገነዘብ ሊቀር ይችላል። አዲስ የተወለደው ሕፃን ጊዜያችሁንና ጉልበታችሁን ስለሚያሟጥጥባችሁ ከስሜትና ከፆታ ፍላጎት አንጻር የነበራችሁ ቅርርብ እንደ ድሮው ላይሆን ይችላል። ታዲያ አንድ ባልና ሚስት ምንም የማያውቀው ውድ ልጃቸው በመሃላቸው ገብቶ እንዳይነጣጥላቸው ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

ቁልፉ፦ አንዳችሁ ለሌላው ያላችሁን ፍቅር በድጋሚ አረጋግጡ።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትዳር ሲናገር “ሰው ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ ከሚስቱ ጋር ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ብሏል። * (ዘፍጥረት 2:24) ይሖዋ አምላክ፣ ልጆች ከጊዜ በኋላ ከወላጆቻቸው ተለይተው እንዲኖሩ ዓላማው ነው። በተቃራኒው ግን አምላክ ባልና ሚስትን አንድ ሥጋ የሚያደርጋቸው ትስስር ለዕድሜ ልክ እንዲዘልቅ ይፈልጋል። (ማቴዎስ 19:3-9) ታዲያ አራስ ልጅ ያላቸው ባልና ሚስቶች ይህን ሐቅ መገንዘባቸው ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች ለይተው እንዲያውቁ የሚረዳቸው እንዴት ነው?

ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ቪቪያን እንደሚከተለው ብላለች፦ “በ⁠ዘፍጥረት 2:24 ላይ በሚገኙት ቃላት ላይ ቆም ብዬ አሰብኩ፤ ይህ ጥቅስ ‘አንድ ሥጋ’ የሆንኩት ከባሌ ጋር እንጂ ከልጄ ጋር አለመሆኑን እንድገነዘብ ረድቶኛል። በመሆኑም ትዳራችንን ማጠናከር እንደሚያስፈልገኝ ተገነዘብኩ።” የሁለት ዓመት ሴት ልጅ ያለቻት ተሪሰ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ከባሌ እንደራቅሁ ሲሰማኝ ወዲያውኑ ለእሱ ሙሉ ትኩረቴን ለመስጠት ጥረት አደርጋለሁ፤ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን በየቀኑ ይህን ለማድረግ እሞክራለሁ።”

ባል ከሆንክ ትዳርህን ለማጠናከር ምን ልታደርግ ትችላለህ? ለሚስትህ እንደምትወዳት ንገራት። ፍቅርህ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም የተደገፈ ይሁን። ሚስትህ ሊያጋጥማት የሚችለውን ያለመረጋጋትና የመጣል ስሜት ለማስወገድ የታሰበበት ጥረት አድርግ። የ30 ዓመት ዕድሜ ያላት ሣራ የተባለች አንዲት እናት “አንዲት ሚስት ከወለደች በኋላ ሰውነቷ እንደቀድሞው ባይሆንም እንኳ ባሏ አሁንም ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታትና እንደሚያፈቅራት ማወቅ ያስፈልጋታል” ብላለች። በጀርመን የሚኖረውና የሁለት ወንዶች ልጆች አባት የሆነው አለን ለሚስቶች ስሜታዊ ድጋፍ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ያምንበታል። “ሚስቴ ሲከፋት ምንጊዜም ከጎኗ ለመሆን ጥረት አደርጋለሁ” ብሏል።

አንድ ባልና ሚስት ልጅ ሲወልዱ ከፆታ ግንኙነት ጋር በተያያዘ በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥ እንደሚኖር ግልጽ ነው። ስለዚህ ባልና ሚስቱ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በግልጽ መነጋገር ይኖርባቸዋል። ባልና ሚስት ከፆታ ግንኙነት ጋር በተያያዘ ለውጥ ማድረግ ያለባቸው ‘በጋራ ተስማምተው’ ሊሆን እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 7:1-5) ይህ ደግሞ መነጋገር ይጠይቃል። አስተዳደጋችሁ ወይም የመጣችሁበት ባሕል ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ስለ ፆታ ጉዳይ በግልጽ እንዳትነጋገሩ እንቅፋት ሊሆንባችሁ ይችላል። ይሁን እንጂ ወላጅነት ከሚያስከትላቸው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ጋር እየተላመዳችሁ ስትሄዱ ስለ ፆታ ጉዳይ መነጋገራችሁ አስፈላጊ ነው። የሌላውን ስሜት የምትረዱ፣ ታጋሾችና ሐቀኞች ሁኑ። (1 ቆሮንቶስ 10:24) በዚህ መንገድ ሁለታችሁም አለመግባባትን ከማስወገድ አልፋችሁ በመካከላችሁ ያለው ፍቅር እያደገ እንዲሄድ ታደርጋላችሁ።​—1 ጴጥሮስ 3:7, 8

በተጨማሪም አንድ ባልና ሚስት እርስ በርስ የሚሞጋገሱ ከሆነ አንዳቸው ለሌላው ያላቸው ፍቅር ጥልቅ እየሆነ ይሄዳል። ጥበበኛ የሆነ ባል አንዲት አዲስ እናት ብዙ ነገር ብታከናውንም ልፋቷ ላይስተዋል እንደሚችል ይገነዘባል። ቪቪያን “ቀኑን ሙሉ ያለ ምንም ፋታ ልጄን ስንከባከብ ብውልም ብዙውን ጊዜ በቀኑ መገባደጃ ላይ ምንም እንዳልሠራሁ ሆኖ ይሰማኛል!” ብላለች። አንዲት አስተዋይ ሚስት በጣም ሥራ ቢበዛባትም ባሏ ለቤተሰቡ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ አቅልላ ላለመመልከት ትጠነቀቃለች።​—ምሳሌ 17:17

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ እናንት እናቶች፣ የሚቻል ከሆነ ልጃችሁ ሲተኛ ትንሽ ለማሸለብ ሞክሩ። እንዲህ ማድረጋችሁ ኃይላችሁን ስለሚያድስላችሁ ለትዳራችሁ የሚሆን ተጨማሪ ጉልበት ይኖራችኋል። እናንት አባቶች፣ ከቻላችሁ ሌሊት ተነስታችሁ ልጁን በመመገብ ወይም የሽንት ጨርቁን በመቀየር ሚስታችሁ ማረፍ እንድትችል እርዷት። ማስታወሻ ጽፋችሁ በመተው፣ በሞባይል የጽሑፍ መልእክት በመላክ ወይም ስልክ በመደወል ሚስታችሁን እንደምትወዷት በየጊዜው ግለጹ። ባልና ሚስት እንደመሆናችሁ መጠን ብቻችሁን የምትጨዋወቱበት ጊዜ ለማግኘት ጥረት አድርጉ። ስለ ልጃችሁ ብቻ ሳይሆን ስለ ራሳችሁ ጉዳይም አውሩ። ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ያላችሁ ግንኙነት ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል የምታደርጉ ከሆነ ወላጅነት የሚያስከትላቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት የተሻለ አቅም ይኖራችኋል።

ተፈታታኝ ሁኔታ 3፦ በልጅ አስተዳደግ ጉዳይ አለመግባባት መፈጠሩ።

አንድ ባልና ሚስት ያደጉበት መንገድ እንዳይግባቡ ሊያደርጋቸው ይችላል። አሳሚ የምትባል አንዲት ጃፓናዊት እናትና ባሏ ካትሱሮ እንዲህ ዓይነት ችግር አጋጥሟቸዋል። “እኔ፣ ካትሱሮ ልጃችንን እንደሚያሞላቅቃት ሲሰማኝ እሱ ደግሞ በጣም ጥብቅ እንደሆንኩባት ይሰማዋል” በማለት አሳሚ ተናግራለች። ታዲያ እንዲህ ያለውን አለመግባባት እንዴት ማስወገድ ትችላላችሁ?

ቁልፉ፦ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ተነጋገሩ፤ እርስ በርስም ተደጋገፉ።

ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “ትዕቢት ጠብን ብቻ ያስፋፋል፤ ጥበብ ግን ምክርን በሚቀበሉ [“በሚመካከሩ ሰዎች፣” NW] ዘንድ ትገኛለች” ሲል ጽፏል። (ምሳሌ 13:10) የትዳር ጓደኛችሁ ከልጅ አስተዳደግ ጋር በተያያዘ ስላለው አመለካከት ምን ያህል ታውቃላችሁ? ስለ ልጅ አስተዳደግ ዝርዝር ጉዳዮችን ሳትነጋገሩ ልጁ እስኪወለድ ድረስ ከቆያችሁ ወላጅ ከመሆን ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት ከመጣጣር ይልቅ መጨረሻችሁ መጨቃጨቅ ብቻ ሊሆን ይችላል።

ለምሳሌ ያህል፣ ቀጥሎ ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስ ስትሰጡ በምን ያህሉ እንደምትስማሙ ለማወቅ ሞክሩ፦ “ልጃችንን ጥሩ የአመጋገብና የእንቅልፍ ልማድ እንዲኖረው እንዴት ልናሠለጥነው እንችላለን? ሌሊት ተኝተን ሳለ ልጁ ባለቀሰ ቁጥር አንስተን ልናቅፈው ይገባል? መጸዳጃ አጠቃቀምን በተመለከተ የምንሰጠውን ሥልጠና ቶሎ ባይቀበል ምን እናደርጋለን?” ውሳኔያችሁ ሌሎች ባልና ሚስቶች ከሚያደርጉት ውሳኔ የተለየ እንደሚሆን ግልጽ ነው። የሁለት ልጆች አባት የሆነው ኤታን “አንድ አቋም እንዲኖራችሁ ስለ አንዳንድ ጉዳዮች አስቀድማችሁ መነጋገር ያስፈልጋችኋል። እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ በመካከላችሁ ልዩነት ሳይፈጠር ለልጃችሁ የሚያስፈልገውን ነገር ማድረግ ትችላላችሁ” ብሏል።

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ወላጆቻችሁ እናንተን ሲያሳድጉ ስለተጠቀሙባቸው የአስተዳደግ ዘዴዎች አስቡ። ከዚያም ልጆቻችሁን ስታሳድጉ እነሱ ከተጠቀሟቸው መንገዶች ውስጥ የትኛውን መከተል እንደምትፈልጉ በየግላችሁ ወስኑ። በተጨማሪም ልትከተሉት የማትፈልጉትን መንገድ አስቀድማችሁ ወስኑ። በመጨረሻም በየፊናችሁ የደረሳችሁበትን መደምደሚያ አንድ ላይ ሆናችሁ ተወያዩበት።

ልጃችሁ በትዳራችሁ ላይ በጎ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል

በበረዶ ላይ በመንሸራተት ትርዒት የሚያሳዩ ልምድ የሌላቸው ጥንዶች ሚዛናቸውን ጠብቀው መሥራት እንዲችሉ ጊዜና ትዕግሥት እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ እናንተም ከአዲሱ የወላጅነት ኃላፊነታችሁ ጋር ለመላመድ ጊዜ ያስፈልጋችኋል። ውሎ አድሮ ግን በራስ የመተማመን መንፈስ ማዳበራችሁ አይቀርም።

ልጅ ማሳደግ ለጋብቻ ቃል ኪዳናችሁ ያላችሁን ጽናት የሚፈትነው ከመሆኑም በላይ በመካከላችሁ ያለውን ዝምድና ለዘለቄታው ይለውጠዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ግሩም የሆኑ ባሕርያትን ለማፍራት አጋጣሚ ይሰጣችኋል። ጥበብ ያዘለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ ካደረጋችሁ እናንተም ኬነዝ ከተባለው አባት ጋር የሚመሳሰል ተሞክሮ ይኖራችኋል። ኬነዝ እንዲህ ብሏል፦ “ልጆችን ማሳደግ በእኔና በሚስቴ ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል። አሁን ከራሳችን ይልቅ ለሌሎች የምናስብ እንዲሁም ከበፊቱ ይበልጥ አፍቃሪዎችና የሰው ችግር የሚገባን ሆነናል።” በእርግጥም እንዲህ ዓይነቶቹ ለውጦች በትዳር ውስጥ ይፈለጋሉ።

^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.11 ብዙ እናቶች ከወለዱ በኋላ ባሉት ሳምንታት ውስጥ አልፎ አልፎ የሚከሰት መለስተኛ የመንፈስ ጭንቀት ያጋጥማቸዋል። አንዳንዶች ደግሞ ከወሊድ ጋር ተያይዞ በሚመጣ ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ይሠቃያሉ። ይህን ችግር ለይቶ ማወቅና መቋቋም የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በሐምሌ 22, 2002 ንቁ! ላይ የሚገኘውን “ከወሊድ በኋላ ከሚመጣው ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ጋር የማደርገውን ትግል በድል ተወጣሁ” የሚለውንና በሰኔ 8, 2003 ንቁ! ላይ የሚገኘውን “ከወሊድ በኋላ የሚመጣን ከባድ የመንፈስ ጭንቀት መረዳት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት። በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁትን እነዚህን ርዕሶች (በአማርኛ አይገኙም) www.watchtower.org በሚለው ድረ ገጽ ላይ ማንበብ ይቻላል።

^ አን.19 አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ እንደሚገልጸው ከሆነ በዘፍጥረት 2:24 ላይ ‘መጣመር’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ግሥ “ከአንድ ሰው ጋር በፍቅርና በታማኝነት መጣበቅን” ሊያመለክት ይችላል።

ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦

  • ባለቤቴ ለቤተሰባችን የምትከፍለውን ወይም የሚከፍለውን መሥዋዕትነት እንደማደንቅ ለማሳየት ባለፈው ሳምንት ምን አድርጌያለሁ?

  • ልጅ ከማሳደግ ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ጉዳዮች አንስተን ከትዳር ጓደኛዬ ጋር የልባችንን ከተጨዋወትን ምን ያህል ጊዜ ሆኖናል?