በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?

ችግሮችን መፍታት

ችግሮችን መፍታት

ባል፦ “ልጆቹ የት ሄዱ?”

ሚስት፦ “ልብስ ሊገዙ ወደ ገበያ ሄደዋል።”

ባል፦ [በቁጣ ስሜት] “ልብስ ሊገዙ ስትይ ምን ማለትሽ ነው? ባለፈው ወር በርካታ ልብሶች ገዝተው የለም እንዴ!”

ሚስት፦ [ጉዳዩን በማስተባበል እንዲሁም ተወቃሽ እንዳደረጋት ስለተሰማት ስሜቷ መጎዳቱን በሚያሳይ መንገድ] “ልብሶቹ እኮ የሚሸጡት በታላቅ ቅናሽ ነው። ለማንኛውም፣ ካልሄድን ሲሉኝ ፈቀድኩላቸው።”

ባል፦ [በጣም ተናዶ] “ልጆቻችን እኔን ሳይጠይቁ ወጪ እንዲያወጡ እንደማልፈልግ ታውቂያለሽ! እንዴት እኔን ሳታማክሪ እንዲህ ያለውን ውሳኔ ታደርጊያለሽ?”

እነዚህ ባልና ሚስት መፍትሔ የሚያሻቸው ምን ችግሮች አጋጥመዋቸዋል? ባልየው ንዴቱን የመቆጣጠር ችግር እንዳለበት ግልጽ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ባልና ሚስቱ፣ ልጆቻቸው እስከ ምን ድረስ ነፃነት ሊሰጣቸው ይገባል በሚለው ጉዳይ የተስማሙ አይመስሉም። በመካከላቸው ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት እንደሌለም መገንዘብ ይቻላል።

ፍጹም የሆነ ትዳር የለም። ሁሉም ባልና ሚስቶች የተለያዩ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። ባለትዳሮች የሚገጥማቸው ችግር ከባድም ይሁን ቀላል ሁኔታውን እንዴት መፍታት እንደሚችሉ መማር ያስፈልጋቸዋል። ለምን?

መፍትሔ ያልተገኘላቸው ችግሮች ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት እንዳይኖር እንቅፋት ይሆናሉ። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን ‘ጠብ እንደ ጠንካራ የግንብ መዝጊያ ነው’ ሲል ተናግሯል። (ምሳሌ 18:19) ችግሮች በሚያጋጥሟችሁ ወቅት ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት እንዲኖራችሁ ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው?

የሐሳብ ግንኙነት ለአንድ ትዳር የደም ሥር ከሆነ ፍቅርና አክብሮት ደግሞ እንደ ልብና እንደ ሳምባ ሊታዩ ይችላሉ። (ኤፌሶን 5:33) ፍቅር፣ አንድ ባልና ሚስት ከዚህ ቀደም የተፈጠረን ቅራኔ ረስተው አሁን ያለውን ችግር በመፍታት ላይ እንዲያተኩሩ ይገፋፋቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 13:4, 5፤ 1 ጴጥሮስ 4:8) አንዳቸው ለሌላው አክብሮት የሚያሳዩ ባልና ሚስት በግልጽ የሚነጋገሩ ከመሆኑም ሌላ የትዳር ጓደኛቸው ምን ለማለት እንደፈለገ ለመረዳትም ይጥራሉ።

ችግሮችን ለመፍታት የሚረዱ አራት ነጥቦች

ከዚህ በታች የሠፈሩትን አራት ነጥቦች በጥንቃቄ ስትመረምር የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ችግሮችን በፍቅርና በአክብሮት ለመፍታት የሚረዱህ እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ጣር።

1. በችግሩ ላይ ለመወያየት ጊዜ መድብ።

“ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ . . . ለዝምታ ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው።” (መክብብ 3:1, 7) ከላይ በመግቢያችን ላይ እንደተመለከትነው አንዳንድ ችግሮች ቁጣና ጭቅጭቅ ሊያስነሱ ይችላሉ። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲከሰት ውይይቱ ወደ ጭቅጭቅ ከማምራቱ በፊት ራስህን በመግዛት ለጊዜው ንግግርህን ማቆም በሌላ አባባል ‘ዝም ማለት’ አለብህ። መጽሐፍ ቅዱስ “ጠብ መጫር ግድብን እንደ መሸንቈር ነው፤ ስለዚህ ጠብ ከመጫሩ በፊት ከነገር ራቅ” በማለት የሚሰጠውን ምክር በመታዘዝ ትዳርህን ከከፋ ችግር መታደግ ትችላለህ።—ምሳሌ 17:14

ይሁን እንጂ “ለመናገርም ጊዜ አለው።” ችግሮች በወቅቱ መፍትሔ ካላገኙ እንደ አረም ሊፈሉ ይችላሉ። ስለሆነም አንድ ችግር ሲነሳ ጊዜ ይፍታው ብሎ ችላ ማለት አይገባም። ውይይቱን ለማቆም ከወሰንክ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ጉዳዩን ደግማችሁ በማንሳት የምትወያዩበት ጊዜ በመመደብ ለትዳር ጓደኛህ አክብሮት እንዳለህ አሳይ። በጉዳዩ ላይ ለመወያየት ቀጠሮ መያዛችሁ መጽሐፍ ቅዱስ “በቊጣችሁ ላይ ፀሓይ አይግባ” በማለት የሚሰጠውን ምክር ሁለታችሁም ተግባራዊ እንድታደርጉ ያስችላችኋል። (ኤፌሶን 4:26) ከዚህም በተጨማሪ ቃልህን መጠበቅ ይኖርብሃል።

እንዲህ ለማድረግ ሞክር:- በየሳምንቱ የቤተሰቡን ችግር አንስታችሁ የምትወያዩበትን ጊዜ መድብ። ብዙውን ጊዜ ወደ ጭቅጭቅ እንድታመሩ በሚያደርጋችሁ ሰዓት ላይ፣ ለምሳሌ ከሥራ ስትመለሱ ወይም ምግብ ከመብላታችሁ በፊት ችግሮችን አንስታችሁ ላለመወያየት ወስን። ይልቁንም ሁለታችሁም ዘና ልትሉ የምትችሉበትን ሰዓት ምረጥ።

2. ስሜትህን በሐቀኝነት እንዲሁም አክብሮት በተሞላበት መንገድ ተናገር።

“እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ።” (ኤፌሶን 4:25) ያገባህ ከሆንክ ደግሞ የቅርብ ባልንጀራህ ወይም ወዳጅህ የትዳር ጓደኛህ ናት። ስለዚህ ስሜትህን ለትዳር ጓደኛህ በግልጽና በሐቀኝነት ተናገር። ለ26 ዓመታት በትዳር የቆየችው ማርጋሬታ * እንዲህ ትላለች፦ “ያገባሁ ሰሞን፣ ችግሮች በሚነሱበት ጊዜ ባለቤቴ ስሜቴን ቶሎ እንደሚረዳልኝ ይሰማኝ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ይህ አስተሳሰቤ ከእውነታ የራቀ እንደሆነ ተገነዘብኩ። አሁን ግን የማስበውንና የሚሰማኝን በግልጽ ለመናገር እሞክራለሁ።”

አንድን ችግር አንስታችሁ ስትወያዩ ዓላማችሁ፣ በጦር ሜዳ እንዳለ ወታደር በጠላት ላይ ድል መቀዳጀት ሳይሆን የትዳር ጓደኛችሁ ስሜታችሁን እንዲረዳላችሁ ማድረግ መሆኑን ማስታወስ አለባችሁ። ይህንን በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት ችግሩ ምን እንደሆነ፣ መቼ እንደተነሳና ምን እንደተሰማችሁ መናገር ይኖርባችኋል። ለምሳሌ ያህል፣ የትዳር ጓደኛሽ ልብሱን በሥርዓት የማያስቀምጥ መሆኑ ቢያናድድሽ በአክብሮት እንዲህ ማለት ትችያለሽ፦ ‘አብዛኛውን ጊዜ ከሥራ ስትመለስ ልብስህን አውልቀህ አልጋ ላይ ትጥላለህ፤ [ችግሩ ምን እንደሆነና መቼ እንደተፈጠረ] ይህ ደግሞ ቤቱን በሥርዓት ለመያዝ ለማደርገው ጥረት አድናቆት እንደጎደለህ ሆኖ እንዲሰማኝ አድርጎኛል። [ምን እንደተሰማሽ ገለጽሽ ማለት ነው።]’ ከዚያም ለችግሩ መፍትሔ ይሆናል የምትይውን ሐሳብ በዘዴ ተናገሪ።

እንዲህ ለማድረግ ሞክር:- ከትዳር ጓደኛህ ጋር ውይይት ከመጀመርህ በፊት ልትናገረው ያሰብከው ነጥብ ይበልጥ ግልጽ እንዲሆንልህ ችግሩ ምን እንደሆነና መፍትሔ ይሆናል የምትለውን ነገር ጻፍ።

3. የትዳር ጓደኛህን ለማዳመጥ እንዲሁም ስሜቷን ለመረዳት ሞክር።

ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ክርስቲያኖች ‘ለመስማት የፈጠኑ፣ ለመናገር የዘገዩ፣ ለቊጣም የዘገዩ’ መሆን እንደሚገባቸው ጽፏል። (ያዕቆብ 1:19) ‘የትዳር ጓደኛዬ ስለተፈጠረው ችግር ምን እንደሚሰማኝ አልተረዳልኝም’ ብሎ ከማሰብ የበለጠ የሚጎዳ ነገር የለም ማለት ይቻላል። ስለዚህ የትዳር ጓደኛችሁ እንዲህ ያለው ስሜት እንዲያድርበት ላለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ!—ማቴዎስ 7:12

ሠላሳ አምስት ዓመታት በትዳር ውስጥ ያሳለፈው ቮልፍጋንግ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ችግሮችን አንስተን በምንነጋገርበት ወቅት፣ በተለይም ባለቤቴ ስሜቴን እንዳልተረዳችልኝ ሲሰማኝ በጣም እጨነቃለሁ።” ለ20 ዓመታት በትዳር የቆየችው ዲያና ደግሞ “ባለቤቴን፣ ‘ውይይት በምናደርግበት ጊዜ በጥሞና አታዳምጠኝም’ በማለት ብዙ ጊዜ እወቅሰዋለሁ” ስትል የተሰማትን ሳትሸሽግ ተናግራለች። እንዲህ ያለውን እንቅፋት ማስወገድ የምትችለው እንዴት ነው?

የትዳር ጓደኛዬ ምን እንደምታስብ ወይም ምን እንደሚሰማት አውቃለሁ ብለህ አትደምድም። የአምላክ ቃል “ከልክ በላይ በራሱ የሚመካ ሰው ጠብ ከመፍጠር ውጪ የሚያመጣው ነገር የለም፤ እርስ በርስ በሚመካከሩ ሰዎች ዘንድ ግን ጥበብ አለ” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 13:10 NW) የትዳር ጓደኛህ ስሜቷን ስትገልጽ በጥሞና በማዳመጥ አክብሮት እንዳለህ አሳይ። ከዚያም ሐሳቧን በትክክል እንደተረዳሃት ለማረጋገጥ የተናገረችውን ነገር በራስህ አባባል ደግመህ ንገራት፤ እንዲህም ስታደርግ በፌዝ አሊያም በቁጣ መሆን የለበትም። ምናልባትም በተሳሳተ መንገድ የተረዳኸው ነገር ካለ እንድታርምህ ፍቀድላት። ስሜትህን የመግለጽ አጋጣሚ ያለህ አንተ ብቻ እንደሆንክ አድርገህ አታስብ። አንዳችሁ የሌላውን ስሜትና ሐሳብ በደንብ መረዳታችሁን እስከምታረጋግጡ ድረስ ተራ በተራ ተነጋገሩ።

እርግጥ ነው፣ የትዳር ጓደኛህን በጥሞና ማዳመጥም ሆነ አመለካከቷን መቀበል ትሕትናና ትዕግሥት ይጠይቃል። ይሁን እንጂ ለትዳር ጓደኛህ አክብሮት በማሳየት ረገድ ቅድሚያውን የምትወስድ ከሆነ እሷም እንዲሁ ለማድረግ ትገፋፋለች።—ማቴዎስ 7:2፤ ሮሜ 12:10

እንዲህ ለማድረግ ሞክር:- የትዳር ጓደኛህ የሰጠችውን ሐሳብ ደግመህ በምትናገርበት ወቅት እሷ ያለችውን ቃል በቃል አትድገም። ከዚህ ይልቅ ስሜቷን ስትገልጽ የተረዳኸውን ነገር ደግነት በተሞላበት መንገድ ንገራት።—1 ጴጥሮስ 3:8

4. በመፍትሔ ሐሳቡ ላይ ተስማሙ።

“ለሥራቸው መልካም ውጤት ስለሚያገኙ፣ ከአንድ፣ ሁለት መሆን ይሻላል፤ አንዱ ቢወድቅ፣ ባልንጀራው ደግፎ ያነሣዋል። ቢወድቅ የሚያነሣው ረዳት የሌለው ግን፣ እንዴት አሳዛኝ ነው!” (መክብብ 4:9, 10) ባልና ሚስቱ ተባብረው የሚሠሩና እርስ በርስ የሚደጋገፉ ከሆነ የማይፈቱት ችግር አይኖርም ማለት ይቻላል።

እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ባልን የቤተሰብ ራስ አድርጎ ሾሞታል። (1 ቆሮንቶስ 11:3፤ ኤፌሶን 5:23) ይሁንና ባል የቤተሰብ ራስ ነው ሲባል አምባገነን ይሆናል ማለት አይደለም። ጥበበኛ ባል የሚስቱን ሐሳብ ከግምት ሳያስገባ ውሳኔ አያደርግም። ሃያ ዓመታት በትዳር ያሳለፈው ዴቪድ “ከባለቤቴ ጋር የሚያስማማንን ነጥብ ለማግኘት እሞክራለሁ፤ ከዚያም ሁለታችንም የምንቀበለውን ውሳኔ ለማድረግ እጥራለሁ” ብሏል። ትዳር ከመሠረተች ሰባት ዓመት የሆናት ታንያ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ወሳኙ ነገር ትክክለኛው ማን ነው የሚለው ጉዳይ አይደለም። አንዳንዴ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ የተለያዩ መንገዶች ይኖራሉ። በዚህ ረገድ ውጤታማ ለመሆን ቁልፉ ምክንያታዊነትና ግትር አለመሆን እንደሆነ ተረድቻለሁ።”

እንዲህ ለማድረግ ሞክር:- ለገጠማችሁ ችግር መፍትሔ ይሆናሉ የምትሏቸውን የተለያዩ ሐሳቦች በመጻፍ በመካከላችሁ ተባብሮ የመሥራት መንፈስ እንዲዳብር ጣሩ። ጽፋችሁ ስትጨርሱ ነጥቦቹን እንደገና ከልሷቸው፤ እንዲሁም የተስማማችሁበትን የመፍትሔ ሐሳብ በተግባር ላይ ለማዋል ወስኑ። ከዚያም በተስማማችሁበት መሠረት እየሠራችሁ እንዳለና ውሳኔያችሁ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ ሳትዘገዩ ለመነጋገር ጊዜ መድቡ።

ተባብራችሁ ሥሩ

ኢየሱስ ጋብቻን አስመልክቶ ሲናገር “እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 19:6) እዚህ ጥቅስ ላይ ‘መጣመር’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ‘በቀንበር መጠመድ’ የሚል ፍቺ አለው። ቀንበር ሁለት እንስሳት አንድን ሥራ በኅብረት እንዲሠሩ ያስችላቸዋል። ይሁንና እንስሶቹ ተስማምተው ቀንበሩን የማይጎትቱ ከሆነ ሥራውን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማከናወን አይችሉም፤ እንዲሁም ቀንበሩ አንገታቸውን ያቆስላቸዋል። በኅብረት የሚሠሩ ከሆነ ግን ማረስም ሆነ ከባድ ጭነት መጎተት ይችላሉ።

በተመሳሳይም ተባብረው መሥራት ያቃታቸው ባልና ሚስት የጋብቻ ቀንበሩ ሊያቆስላቸው ይችላል። ቀንበሩን ተስማምተው መጎተት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ከተማሩ ግን ማንኛውንም ዓይነት ችግር መፍታትና በትዳራቸው ውጤታማ መሆን ይችላሉ። ካላላ የተባለ በትዳሩ ደስተኛ የሆነ አንድ ክርስቲያን ሁኔታውን እንዲህ በማለት ጠቅለል አድርጎ ገልጾታል፦ “እኔና ባለቤቴ በግልጽ በመነጋገር፣ ራሳችንን በሌላኛው ቦታ በማስቀመጥ፣ ይሖዋ እንዲረዳን በመጸለይ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ ለ25 ዓመታት ያህል ችግሮቻችንን ስንፈታ ቆይተናል።” አንተስ እንዲህ ማድረግ ትችላለህ?

ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ . . .

  • ከትዳር ጓደኛዬ ጋር ይበልጥ ልነጋገርበት የምፈልገው ችግር የትኛው ነው?

  • ባለቤቴ በጉዳዩ ላይ ያላትን ትክክለኛ ስሜት መረዳቴን ማረጋገጥ የምችለው እንዴት ነው?

  •  ሁልጊዜ እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን የምል ከሆነ ምን ችግር ሊፈጠር ይችላል?

^ አን.17 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።