በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

አምላክ አለ?

አምላክ አለ?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 አዎን፣ አምላክ አለ፤ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብለን እንድንደመድም የሚያደርግ አጥጋቢ ማስረጃ ይዟል። አምላክ መኖሩን የምናምነው ያለምንም ማስረጃ ወይም በሃይማኖታችን እንደዚያ ተብለን ስለተማርን መሆን የለበትም፤ ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ‘የማሰብ ችሎታችንን’ እና ‘የማስተዋል ችሎታችንን’ እንድናሠራ ያበረታታናል። (ሮም 12:1፤ 1 ዮሐንስ 5:20) እስቲ ቀጥሎ የቀረቡትን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ አሳማኝ ነጥቦች ተመልከት፦

  •   በሥርዓት የተደራጀና ሕይወት ያለበት አጽናፈ ዓለም መኖሩ ፈጣሪ እንዳለ ይጠቁማል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በእርግጥ እያንዳንዱ ቤት የራሱ ሠሪ አለው፤ ሁሉን ነገር የሠራው ግን አምላክ ነው።” (ዕብራውያን 3:4) ብዙ የተማሩ ሰዎች፣ ለመረዳት ቀላል የሆነው ይህ የመከራከሪያ ነጥብ አሳማኝ እንደሆነ ይሰማቸዋል። a

  •   እኛ ሰዎች ከእንስሳት በተለየ መልኩ የሕይወትን ትርጉምና ዓላማ የመረዳት ተፈጥሯዊ ፍላጎት አለን፤ ለአካላችን የሚያስፈልጉ ነገሮች ቢሟሉም እንኳ ይህ ዓይነቱ ፍላጎት ላይረካ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ፍላጎት ‘በመንፈሳዊ ድሃ መሆንን ማወቅ’ በማለት የሚጠራው ሲሆን ይህ ፍላጎት አምላክን ለማወቅና ለማምለክ ያለንን ተፈጥሯዊ ፍላጎትም ያጠቃልላል። (ማቴዎስ 5:3፤ ራእይ 4:11) በውስጣችን እንዲህ ያለ መንፈሳዊ ፍላጎት መኖሩ አምላክ እንዳለ ብቻ ሳይሆን ይህን ፍላጎታችንን እንድናረካ የሚፈልግ አፍቃሪ አምላክ እንደሆነም ይጠቁማል።—ማቴዎስ 4:4

  •   በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙ ዝርዝር ሐሳቦችን የያዙ ትንቢቶች ከተጻፉ ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ በትክክል ተፈጽመዋል። እነዚህ ትንቢቶች የያዙት እያንዳንዱ ዝርዝር ሐሳብ ሳይቀር በትክክል መፈጸሙ ትንቢቶቹን ያስነገረው ከሰው በላይ የሆነ አካል እንደሆነ ይጠቁማል።—2 ጴጥሮስ 1:21

  •   የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች እነሱ በኖሩበት ዘመን ያልተደረሰባቸውን ሳይንሳዊ እውነታዎች ያውቁ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በጥንት ዘመን ሰዎች ምድር የተቀመጠችው እንደ ዝሆን፣ ከርከሮ ወይም በሬ ባለ አንድ እንስሳ ላይ እንደሆነ ያምኑ ነበር። ከዚህ በተለየ መልኩ መጽሐፍ ቅዱስ “ምድርንም እንዲያው በባዶው ላይ አንጠለጠላት” ይላል። (ኢዮብ 26:7) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ምድር “ክበብ” ወይም ክብ እንደሆነች በመናገር የምድርን ቅርጽ በትክክል ገልጿል። (ኢሳይያስ 40:22) ብዙ ሰዎች፣ መጽሐፍ ቅዱስ በዘመኑ ያልተደረሰባቸውን እንዲህ ዓይነት ሐሳቦች ሊይዝ የቻለው ጸሐፊዎቹ መረጃዎቹን ከአምላክ በማግኘታቸው እንደሆነ ይሰማቸዋል።

  •   መጽሐፍ ቅዱስ ለብዙ ከባድ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል፤ አንድ ሰው ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ካላገኘ አምላክ የለም ወደሚል መደምደሚያ ሊደርስ ይችላል። አንዳንድ ምሳሌዎችን ተመልከት፦ አምላክ ሰዎችን የሚወድድ እንዲሁም ሁሉን የሚችል ከሆነ በዓለም ላይ ያለውን መከራና ክፉ ነገር ያላስቆመው ለምንድን ነው? ሃይማኖት አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች መጥፎ ነገር እንዲፈጽሙ ምክንያት የሚሆነው ለምንድን ነው?—ቲቶ 1:16

a የስነ ፈለክ ተመራማሪ የነበሩት አለን ሰንዴጅ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለዋል፦ “በሥርዓት የተደራጀው [አጽናፈ ዓለም] የተገኘው በፍንዳታ ነው ብሎ መቀበል በጣም ይከብደኛል። ሥርዓትና መልክ እንዲኖረው ያደረገ አንድ ነገር መኖር አለበት። ለእኔ አምላክ እንቆቅልሽ ነው፤ ይሁንና ሁሉም ነገር ካለመኖር ወደ መኖር ሊመጣ የቻለው አምላክ በመኖሩ ነው።”