በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንድፍ አውጪ አለው?

የባሕር መስል ራሱን የሚያጣብቅበት መንገድ

የባሕር መስል ራሱን የሚያጣብቅበት መንገድ

መስል የተባሉት የባሕር ፍጥረታት ራሳቸውን ከድንጋይ፣ ከእንጨት ወይም ከመርከብ ጋር ያጣብቃሉ። አንዳንድ የባሕር ፍጥረታት ይህን የሚያደርጉት በቀጥታ በመለጠፍ ነው፤ የባሕር መስሎች ግን ባይሰስ በሚባሉ ቀጫጭን ክር መሰል ነገሮች አማካኝነት ግዑዝ ነገሮች ላይ ይንጠለጠላሉ። ይህ ዘዴ፣ እንደ ልብ ለመመገብና ከቦታ ወደ ቦታ ለመፍለስ ያስችላቸዋል፤ ሆኖም ክሮቹ በጣም ስስ በመሆናቸው የውቅያኖሱን ሞገድ መቋቋም የሚችሉ አይመስሉም። ታዲያ ይህ ፍጥረት የሚንጠለጠልባቸው እነዚህ ስስ ክሮች ወደ ባሕሩ ተጠርጎ እንዳይወሰድ የሚረዱት እንዴት ነው?

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ባይሰስ የተባሉት እነዚህ ክሮች በአንዱ ጫፍ ደረቅ፣ በሌላኛው ጫፍ ደግሞ ለስላሳና ተለጣጭ ናቸው። ክሩ 80 በመቶ ከጠንካራ፣ 20 በመቶ ደግሞ ከለስላሳ ንጥረ ነገር የተሠራ ነው፤ ተመራማሪዎች ይህ ሬሾ፣ መስሉ በሚገባ መንጠልጠል እንዲችል ወሳኝ እንደሆነ ደርሰውበታል። እነዚህ ክሮች ተለዋዋጭ የሆነውን የባሕር ግፊት መቋቋም እንዲችሉ የረዳቸው ይህ ንድፍ ነው።

ፕሮፌሰር ጋይ ጄነን የዚህ ምርምር ውጤት “በጣም አስደናቂ” እንደሆነ ከተናገሩ በኋላ “ይህ ፍጥረት እንዲህ ያለ አስደናቂ ችሎታ የኖረው ለስላሳው ክፍል ከጠንካራው ክፍል ጋር ግሩም ቅንጅት ስላለው ነው” ብለዋል። የሳይንስ ሊቃውንት፣ የእነዚህ ክሮች ንድፍ በሕንፃዎች ወይም በባሕር ሰርጓጅ መርከቦች ላይ መሣሪያዎችን ለመግጠም፣ ጅማትን ከአጥንት ጋር ለማያያዝ እንዲሁም በቀዶ ጥገና ወቅት ቁስሉን ለማጣበቅ ሊረዳ እንደሚችል ያምናሉ። በሳንታ ባርባራ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ኸርበርት ዌት እንዲህ ብለዋል፦ “ነገሮችን ማጣበቅ ከሚቻልበት መንገድ ጋር በተያያዘ ከተፈጥሮ ስፍር ቁጥር የሌለው ትምህርት ልናገኝ እንችላለን።”

ታዲያ ምን ይመስልሃል? የባሕር መስል ባይሰስ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?