በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 5

ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ምን ጥቅም ታገኛለህ?

ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ምን ጥቅም ታገኛለህ?

አርጀንቲና

ሴራ ሊዮን

ቤልጅየም

ማሌዥያ

ብዙ ሰዎች በሃይማኖታዊ ፕሮግራሞች ላይ መንፈሳዊ መመሪያም ሆነ ማጽናኛ ማግኘት ባለመቻላቸው እንደነዚህ ወዳሉ ቦታዎች መሄድ አቁመዋል። ታዲያ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት የሚኖርብህ ለምንድን ነው? እዚያ ምን ጥቅም ታገኛለህ?

አፍቃሪና አሳቢ ከሆኑ ሰዎች ጋር በመሰብሰብ ትደሰታለህ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩት ክርስቲያኖች በተለያዩ ጉባኤዎች ውስጥ ይታቀፉ የነበረ ሲሆን አምላክን ለማምለክ፣ ቅዱሳን መጻሕፍትን ለማጥናት እንዲሁም እርስ በርስ ለመበረታታት ይሰበሰቡ ነበር። (ዕብራውያን 10:24, 25) በስብሰባዎቻቸው ላይ አፍቃሪ ከሆኑ መንፈሳዊ ወንድሞቻቸው ጋር ስለሚገናኙ ከእውነተኛ ወዳጆቻቸው ጋር እንደሆኑ ይሰማቸው ነበር። (2 ተሰሎንቄ 1:3፤ 3 ዮሐንስ 14) እኛም የእነሱን ምሳሌ ስለምንከተል በስብሰባዎቻችን እንደሰታለን።

የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል ትማራለህ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጸው መሠረት ዛሬም ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች አንድ ላይ እንሰበሰባለን። ብቃት ያላቸው አስተማሪዎች በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች በዕለታዊ ሕይወታችን እንዴት ተግባራዊ እንደምናደርግ ማስተዋል እንድንችል ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያብራሩልናል። (ዘዳግም 31:12፤ ነህምያ 8:8) ሁሉም ሰው መዘመር እንዲሁም ውይይት በሚደረግባቸው የስብሰባው ክፍሎች ላይ ሐሳብ መስጠት የሚችል ሲሆን ይህም ክርስቲያናዊ ተስፋችንን ለመግለጽ ያስችለናል።—ዕብራውያን 10:23

በአምላክ ላይ ያለህ እምነት ይጠናከራል። ሐዋርያው ጳውሎስ በዘመኑ ከነበሩት ጉባኤዎች ለአንዱ ሲጽፍ “ላያችሁ እጓጓለሁና፤ ይህን ስል እኔ በእናንተ እምነት እናንተም በእኔ እምነት እርስ በርሳችን እንድንበረታታ ነው” ብሎ ነበር። (ሮም 1:11, 12) በስብሰባዎቻችን ላይ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር አዘውትረን መገናኘታችን እምነታችንን የሚያጠናክርልን ከመሆኑም ሌላ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምተን ለመኖር ባደረግነው ቁርጥ ውሳኔ ለመጽናት ያስችለናል።

አንተስ ከላይ የተጠቀሱትን ጥቅሞች ማግኘት ትፈልጋለህ? ከሆነ በስብሰባዎቻችን ላይ እንድትገኝ እንጋብዝሃለን። በስብሰባው ላይ ጥሩ አቀባበል እንደሚደረግልህ አትጠራጠር። መግቢያ በነፃ ሲሆን ሙዳየ ምጽዋትም አይዞርም።

  • በጉባኤ ስብሰባዎቻችን ላይ የእነማንን ምሳሌ እንከተላለን?

  • በስብሰባዎች ላይ በመገኘት ምን ጥቅም እናገኛለን?