በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በእምነታቸው ምሰሏቸው | ሣራ

አምላክ “ልዕልት” ብሎ ጠርቷታል

አምላክ “ልዕልት” ብሎ ጠርቷታል

ሣራ ከምታከናውነው ሥራ ቀና በማለት ወደ ማዶ አሻግራ ተመለከተች። የሣራ አገልጋዮች ብልህ የሆነችው እመቤታቸው የምትሰጣቸውን መመሪያ በመከተል ደስ እያላቸው ሥራቸውን በትጋት ያከናውናሉ። ታታሪ የሆነችው ሣራም ብትሆን ሥራ አልፈታችም። በሐሳብ ተውጣ በሥራ የዛሉ እጆቿን እያሻሸች ስታፍታታ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ምናልባትም የሚኖሩበት ድንኳን ላይ ያለውን ቀዳዳ ስትጥፍ ቆይታ ሊሆን ይችላል። ከፍየል ፀጉር የተሠራው ድንኳን ለዓመታት ፀሐይና ዝናብ ስለተፈራረቀበት እየሳሳ ሄዷል፤ ይህም ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ ምን ያህል ረጅም ዘመን እንደኖሩ እንድታስታውስ አድርጓት ሊሆን ይችላል። ቀትር አልፎ ጀምበሯ ማዘቅዘቅ ጀምራለች። ሣራ፣ አብርሃም * ጠዋት ከቤት ወጥቶ ወደሄደበት አቅጣጫ ትኩር ብላ እያየች በጉጉት እየጠበቀችው ነው። ከዚያም በአቅራቢያው ባለው ኮረብታ ላይ ባሏን ከርቀት ስትመለከት ፊቷ በፈገግታ ተሞላ።

አብርሃም ብዙ አባላት ካለው ቤተሰቡ ጋር ሆኖ የኤፍራጥስን ወንዝ በመሻገር ወደ ከነአን ምድር ከገባ አሥር ዓመት አልፏል። ሣራ፣ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ዘርና ብሔር ለማስገኘት ይሖዋ ባወጣው ዓላማ ውስጥ ባሏ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ስለተገነዘበች ወደማያውቁት አገር ባደረጉት ጉዞ ባለቤቷን በፈቃደኝነት ደግፋዋለች። ይሁንና ሣራ በዚህ የይሖዋ ዓላማ ውስጥ ምን ድርሻ ይኖራታል? ሣራ መሃን ስትሆን አሁን ደግሞ 75 ዓመት ሆኗታል። በመሆኑም ‘አብርሃም ከእኔ ጋር እየኖረ የይሖዋ ተስፋ ሊፈጸም የሚችለው እንዴት ነው?’ የሚል ሐሳብ መጥቶባት ሊሆን ይችላል። ሣራ ይህ ጉዳይ ቢያሳስባት አልፎ ተርፎም መታገሥ ቢያቅታት አይፈረድባትም።

እኛም ‘አምላክ የሰጠው ተስፋ የሚፈጸመው መቼ ይሆን?’ የሚለው ጉዳይ አንዳንድ ጊዜ ያሳስበን ይሆናል። በተለይ በጣም የምንጓጓለትን ተስፋ በምንጠባበቅበት ጊዜ ትዕግሥት ማሳየት ቀላል አይሆንም። ታዲያ ይህች የምትደነቅ ሴት ካሳየችው እምነት ምን ልንማር እንችላለን?

“ይሖዋ ልጆች እንዳልወልድ አድርጎኛል”

የአብርሃም ቤተሰብ ከግብፅ የተመለሰው በቅርቡ ነው። (ዘፍጥረት 13:1-4) አብርሃምና ቤተሰቡ፣ ከነዓናውያን ሎዛ ብለው በሚጠሩት ከቤቴል በስተ ምሥራቅ በሚገኘው ኮረብታ ላይ ድንኳናቸውን ተከሉ። ሣራ ከዚህ ኮረብታ ላይ ሆና አብዛኛውን የተስፋይቱን ምድር ማየት ትችል ነበር። የከነዓናውያን መንደሮች እንዲሁም መንገደኞች ወደ ሩቅ አገሮች የሚሄዱባቸው ጎዳናዎች ይታያሉ። ይሁንና ሣራ በሁሉም አቅጣጫ የምታየው ነገር ከተወለደችበት ከተማ ጋር ጨርሶ አይወዳደርም። ሣራ ያደገችው 1,900 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ዑር የምትባል የሜሶጶጣሚያ ከተማ ነው። ከዑር ስትወጣ ከበርካታ ዘመዶቿ ተለይታለች፤ ከዚህም ሌላ ገበያና መደብሮች ባሉበት የሞቀ ከተማ ውስጥ ያለውን የተመቻቸ ሕይወት እንዲሁም በሚገባ የተገነባውንና ምናልባትም የውኃ መስመር የተዘረጋለትን ቤቷን ትታ ወጥታለች! ሆኖም ሣራ በልጅነት ቤቷ የነበረው ምቾት ናፍቋት ወደ ምሥራቅ እየተመለከተች እንደምትተክዝ ካሰብን ፈሪሃ አምላክ ያላትን ይህችን ሴት አናውቃትም ማለት ነው።

ከ2,000 ዓመታት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ምን ብሎ እንደጻፈ እስቲ እንመልከት። ጳውሎስ፣ ሣራና አብርሃም ስለነበራቸው እምነት ሲናገር “ትተውት የወጡትን ቦታ ሁልጊዜ ቢያስቡ ኖሮ መመለስ የሚችሉበት አጋጣሚ በኖራቸው ነበር” ብሏል። (ዕብራውያን 11:8, 11, 15) ሣራም ሆነች አብርሃም ትተውት የመጡትን ነገር የሚናፍቁ ሰዎች አልነበሩም። እንደዚያ ቢያደርጉ ኖሮ ወደ አገራቸው ለመመለስ ይወስኑ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ በዑር ቢቀሩ ኖሮ ይሖዋ ያቀረበላቸው አስደናቂ መብት ያመልጣቸው ነበር። ደግሞም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ልብ የነኩ የእምነት ምሳሌዎች መሆን አይችሉም፤ እንዲያውም እስከነመፈጠራቸውም የሚያስታውሳቸው አይኖርም ነበር።

ሣራ ወደ ኋላ ከመመልከት ይልቅ ወደ ፊት ተመልክታለች። በመሆኑም ባሏ በከነአን ምድር ውስጥ በሚያደርገው ጉዞ ደግፋዋለች፤ በየጊዜው ድንኳኖቻቸውን ነቅለውና መንጎቻቸውን ይዘው ሲጓዙ እንዲሁም በሄዱበት ቦታ ድንኳናቸውን እንደ አዲስ ሲተክሉ ታግዘው ነበር። ሣራ ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎችንና ለውጦችንም በጽናት አሳልፋለች። ይሖዋ ለአብርሃም ከዚህ በፊት የሰጠውን ተስፋ የደገመለት ቢሆንም ሣራን ግን ምንም አላላትም!—ዘፍጥረት 13:14-17፤ 15:5-7

በመጨረሻ ሣራ በውስጧ ስታውጠነጥን የቆየችውን ሐሳብ ለአብርሃም ለመናገር ወሰነች። “እንግዲህ እንደምታየው ይሖዋ ልጆች እንዳልወልድ አድርጎኛል” ብላ በምትናገርበት ጊዜ በውስጧ ካለው ስሜት ጋር እየታገለች እንደሆነ ከፊቷ ማየት ይቻላል። ሣራ፣ ከአገልጋይዋ ከአጋር ልጆች እንዲወልድ ባሏን ጠየቀችው። ሣራ ለባሏ ይህን ጥያቄ ማቅረብ ምን ያህል ከብዷት ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ትችላለህ? በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ሰዎች እንዲህ ያለው ጥያቄ እንግዳ ሊሆን ይችላል፤ በዚያ ዘመን ግን አንድ ወንድ ወራሽ የሚሆነው ልጅ ለማግኘት ሲል ሁለተኛ ሚስት ማግባቱ ወይም ቁባት መያዙ ያልተለመደ ነገር አልነበረም። * ሣራ፣ አምላክ ከአብርሃም ዘሮች ብሔር ለማቋቋም ያለው ዓላማ የሚፈጸመው በዚህ መንገድ እንደሆነ አስባ ይሆን? ምን እንዳሰበች ባናውቅም ከባድ መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኛ ነበረች። የአብርሃም ምላሽ ምን ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ፣ አብርሃም “[የሣራን] ቃል ሰማ” ይላል።—ዘፍጥረት 16:1-3

ዘገባው ሣራ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ እንድታቀርብ ያነሳሳት ይሖዋ እንደሆነ ይገልጻል? በፍጹም። ከዚህ ይልቅ ያቀረበችው ሐሳብ ሰብዓዊ አመለካከት እንደነበራት የሚጠቁም ነው። ልጅ እንዳትወልድ ያደረጋት አምላክ እንደሆነ ተሰምቷት ነበር፤ አምላክ ሌላ መፍትሔ ሊያዘጋጅ እንደሚችል አላሰበችም። ሣራ፣ መፍትሔ ብላ ያቀረበችው ሐሳብ በራሷ ላይ ሐዘንና ችግር የሚያስከትል ነበር። ያም ሆኖ ያቀረበችው ሐሳብ፣ ራስ ወዳድ እንዳልሆነች የሚያሳይ ነው። ከምንም በላይ የራሳቸውን ፍላጎት የሚያስቀድሙ ሰዎች በሞሉበት ዓለም ውስጥ ሣራ ያሳየችው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ መንፈስ የሚያስደንቅ አይደለም? እኛም ከራሳችን ፍላጎት ይልቅ የአምላክን ዓላማዎች ለማስቀደም ፈቃደኞች ከሆንን ሣራን በእምነቷ እየመሰልናት ነው።

“ሳቅሽ እንጂ”

ብዙም ሳይቆይ አጋር ከአብርሃም አረገዘች። አጋር ማርገዟ ከሣራ የበለጠ ተፈላጊ እንደሚያደርጋት ስለተሰማት ሳይሆን አይቀርም እመቤቷን መናቅ ጀመረች። መሃን የሆነችው ሣራ በዚህ በጣም አዝና መሆን አለበት! ሣራ አገልጋይዋን አጋርን እንደቀጣቻት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፤ እርግጥ ይህን ያደረገችው በምን መንገድ እንደሆነ አይገልጽም። አብርሃም፣ ሚስቱ አገልጋይዋን እንድትቀጣት የፈቀደላት ሲሆን አምላክም የሣራን እርምጃ ደግፎታል። ውሎ አድሮ አጋር፣ እስማኤል የሚባል ወንድ ልጅ ወለደች፤ ይህ ከሆነ በኋላም ዓመታት አለፉ። (ዘፍጥረት 16:4-9, 16) ከዚህ በኋላ ይሖዋ ለአብርሃም መልእክት በላከበት ወቅት ሣራ 89 ዓመት ባሏ ደግሞ 99 ዓመት ሆኗቸው ነበር። የመጣላቸው መልእክት በጣም አስደሳች ነበር!

ይሖዋ ለወዳጁ ለአብርሃም ዘሩን እንደሚያበዛው አሁንም በድጋሚ ቃል ገባለት። በተጨማሪም አምላክ ስሙን ቀየረለት። እስከዚህ ጊዜ ድረስ የሚጠራው አብራም እየተባለ ነበር። ይሖዋ ግን ስሙን ለውጦ አብርሃም ብሎ የጠራው ሲሆን ትርጉሙም “የብዙ ሕዝብ አባት” ማለት ነው። በተጨማሪም ይሖዋ፣ ሣራ ከዚህ ተስፋ ጋር በተያያዘ ያላትን ሚና ለመጀመሪያ ጊዜ ገለጸ። “ተጨቃጫቂ” የሚል ትርጉም እንዳለው የሚታሰበውን ሦራ የሚባለውን ስሟን ለውጦ ሁላችንም የምናውቀውን ሣራ የሚል ስም ሰጣት። ሣራ የሚለው ስም ትርጉሙ ምንድን ነው? “ልዕልት” ማለት ነው! ይሖዋ ለዚህች ተወዳጅ ሴት ይህን ስም የመረጠው ለምን እንደሆነ ሲገልጽ “እኔም እባርካታለሁ፤ ከእሷም ወንድ ልጅ እሰጥሃለሁ። እባርካታለሁ፤ እሷም ብዙ ብሔር ትሆናለች፤ የሕዝቦች ነገሥታትም ከእሷ ይወጣሉ” ብሏል።—ዘፍጥረት 17:5, 15, 16

ይሖዋ፣ ብሔራትን ሁሉ የሚባርክ ዘር እንደሚያመጣ የገባው ቃል ኪዳን የሚፈጸመው ከሣራ በሚወለደው ልጅ በኩል ነው! አምላክ ለዚህ ልጅ ያወጣለት ስም ይስሐቅ የሚል ሲሆን ትርጉሙም “ሣቅ” ማለት ነው። ይሖዋ፣ ሣራን ልጅ እንድትወልድ በማድረግ እንደሚባርካት አብርሃም መጀመሪያ ሲሰማ “በግንባሩ ተደፋ” እንዲሁም ሳቀ። (ዘፍጥረት 17:17) አብርሃም በሰማው ነገር ተገርሞና በጣም ተደስቶ ነበር። (ሮም 4:19, 20) ሣራስ ምን ተሰምቷት ይሆን?

ከዚያ ብዙም ሳይቆይ፣ አብርሃም የማያውቃቸው ሦስት ሰዎች ወደ ድንኳኑ መጡ። እንግዶቹ የመጡት በጠራራ ፀሐይ ቢሆንም እነዚህ አረጋውያን ባልና ሚስት ወዲያውኑ ተነስተው እንግዶቹን ለማስተናገድ ደፋ ቀና ማለት ጀመሩ። አብርሃም ለሣራ “ቶሎ በይ! ሦስት መስፈሪያ የላመ ዱቄት ወስደሽ አቡኪና ቂጣ ጋግሪ” አላት። በዚያ ዘመን እንግዳ መቀበል ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ነገር ነበር። አብርሃም ሥራውን በሙሉ ለሚስቱ ትቶ አልተቀመጠም፤ እሱም ወደ መንጋው ሮጦ በመሄድ አንድ ወይፈን አርዶ ተጨማሪ ምግብና መጠጥ አዘጋጀ። (ዘፍጥረት 18:1-8) እነዚያ “ሰዎች” የይሖዋ መላእክት ነበሩ! ሐዋርያው ጳውሎስ “እንግዳ መቀበልን አትርሱ፤ አንዳንዶች ይህን ሲያደርጉ ሳያውቁት መላእክትን አስተናግደዋልና” በማለት የጻፈው ይህን ሁኔታ አስታውሶ ሊሆን ይችላል። (ዕብራውያን 13:2) አንተስ አብርሃምና ሣራ የተዉትን ግሩም የእንግዳ ተቀባይነት ምሳሌ መኮረጅ ትችላለህ?

ሣራ እንግዳ ተቀባይ ነበረች

ከመላእክቱ አንዱ፣ ሣራ ልጅ እንደምትወልድ አምላክ ለአብርሃም የገባውን ቃል በድጋሚ በነገረው ጊዜ ሣራ በድንኳኑ ውስጥ ሆና እየሰማች ነበር። በዚህ ዕድሜዋ ልጅ መውለድ የማይመስል ነገር ሆኖ ስለተሰማት “አሁን እንዲህ አርጅቼ ጌታዬም ዕድሜው ገፍቶ እያለ በእርግጥ እንዲህ ዓይነት ደስታ ላገኝ እችላለሁ?” ብላ በማሰብ በልቧ ሳቀች። መልአኩም የሣራን አስተሳሰብ ለማረም “ለይሖዋ የሚሳነው ነገር አለ?” በማለት ጠየቃት። እሷም ስለፈራች “ኧረ አልሳቅኩም!” ብላ አስተባበለች፤ ይህ ሌላም ሰው በእሷ ቦታ ቢሆን የሚያደርገው ነገር ነው። መልአኩም “እንዴ! ሳቅሽ እንጂ” አላት።—ዘፍጥረት 18:9-15

ሣራ መሳቋ እምነት እንደጎደላት የሚያሳይ ነበር? በጭራሽ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሣራም የተስፋን ቃል የሰጠው እሱ ታማኝ እንደሆነ አድርጋ ስላሰበች ዕድሜዋ ካለፈ በኋላም እንኳ ዘር ለመፀነስ በእምነት ኃይል አገኘች” ይላል። (ዕብራውያን 11:11) ሣራ ይሖዋን በደንብ ታውቀዋለች፤ የሰጠውን ማንኛውም ተስፋ መፈጸም እንደሚችልም እርግጠኛ ነች። ከእኛ መካከል እንዲህ ዓይነት እምነት የማያስፈልገው ማን አለ? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰውን አምላክ በደንብ ለማወቅ ልንጥር ይገባል። እንዲህ ካደረግን ሣራ በአምላክ ላይ እንደዚያ ዓይነት እምነት ማሳደሯ ተገቢ እንደነበር እንገነዘባለን። በእርግጥም ይሖዋ ታማኝ ስለሆነ የገባውን ቃል ሁሉ ይፈጽማል፤ አንዳንድ ጊዜ፣ የሰጠውን ተስፋ የሚፈጽምበት መንገድ በአግራሞት እንድንስቅ ሊያደርገን ይችላል!

“የምትልህን ስማ”

ይሖዋ ሣራን ላሳየችው የላቀ እምነት ክሷታል

ሣራ ዕድሜዋን ሙሉ ስትመኘው የኖረችውን አስደሳች ነገር በ90 ዓመቷ አገኘች። በወቅቱ መቶ ዓመት ለሞላው ውድ ባለቤቷ ወንድ ልጅ ወለደችለት! አብርሃም፣ አምላክ በነገረው መሠረት ሕፃኑን ይስሐቅ ወይም “ሳቅ” ብሎ ጠራው። ሣራ በዕድሜ ምክንያት የተሸበሸበው ፊቷ በፈገግታ ተሞልቶ “አምላክ በደስታ እንድስቅ አድርጎኛል፤ ይህን የሰማም ሁሉ ከእኔ ጋር አብሮ ይስቃል” ብላ ስትናገር በዓይነ ሕሊናችን መሳል እንችላለን። (ዘፍጥረት 21:6) ሣራ ከይሖዋ ያገኘችው ይህ ተአምራዊ ስጦታ ቀሪ ሕይወቷን በደስታ እንድታሳልፍ እንዳደረጋት ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ስጦታው ትልቅ ኃላፊነትም አስከትሎባታል።

ይስሐቅ አምስት ዓመት ሲሆነው አብርሃም፣ ልጁ ጡት የጣለበትን ቀን ምክንያት በማድረግ ድግስ አዘጋጀ። ይሁን እንጂ ስጋት የሚፈጥር ነገር ነበር። ሣራ ‘በተደጋጋሚ ያስተዋለችው’ አንድ የሚያሳስብ ነገር ነበር። የአጋር ልጅ የሆነው የ19 ዓመቱ እስማኤል በትንሹ ይስሐቅ ላይ በተደጋጋሚ ያፌዝበት ነበር። እስማኤል ይህን ያደረገው እንዲሁ ለቀልድ ብሎ አልነበረም። ሐዋርያው ጳውሎስ ከጊዜ በኋላ በመንፈስ መሪነት እንደጻፈው እስማኤል በይስሐቅ ላይ ስደት አድርሶበታል። ሣራ ይህ አድራጎት ለልጇ ደህንነት ከባድ ስጋት የሚፈጥር እንደሆነ ገባት። ሣራ፣ ይስሐቅ ልጇ ከመሆኑም ባሻገር በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ታውቅ ነበር። ስለዚህ እንደምንም ራሷን አደፋፍራ አብርሃምን በግልጽ አነጋገረችው። አጋርንና እስማኤልን እንዲያባርራቸው ጠየቀችው።—ዘፍጥረት 21:8-10፤ ገላትያ 4:22, 23, 29

ታዲያ አብርሃም ምን ተሰማው? መጽሐፍ ቅዱስ “ሣራ ስለ ልጁ የተናገረችው ነገር በጣም ቅር አሰኘው” ይላል። አብርሃም እስማኤልን ይወደው ነበር፤ ለእስማኤል ያለው ፍቅር የተፈጠረውን ሁኔታ እንዳያስተውል አድርጎታል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ጉዳዩን በሚገባ ስለሚያውቅ ጣልቃ ገባ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አምላክ አብርሃምን እንዲህ አለው፦ ‘ሣራ ስለ ልጁና ስለ ባሪያህ እየነገረችህ ያለው ነገር ምንም ቅር አያሰኝህ። ዘርህ የሚጠራልህ በይስሐቅ በኩል ስለሆነ የምትልህን ስማ።’” ይሖዋ ለአጋርና ለልጁ አስፈላጊው እንክብካቤ እንደሚያደርግላቸው ለአብርሃም አረጋገጠለት። ታማኙ አብርሃምም የታዘዘውን አደረገ።—ዘፍጥረት 21:11-14

ሣራ ለአብርሃም ጥሩ ሚስትና እውነተኛ ረዳቱ ነበረች። ባሏ መስማት የሚፈልገውን ነገር ብቻ የምትናገር ሴት አልነበረችም። ቤተሰቡንና የወደፊት ሕይወታቸውን የሚነካ አንድ ችግር ስትመለከት ጉዳዩን ለባሏ በግልጽ ነግራዋለች። ሣራ በግልጽ መናገሯ አክብሮት እንደሌላት የሚያሳይ እንደሆነ ተደርጎ መቆጠር የለበትም። እንዲያውም ባለትዳር የነበረው ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ሣራ ለባሏ ጥልቅ አክብሮት በማሳየት ለሚስቶች በጣም ጥሩ ምሳሌ እንደሆነች ከጊዜ በኋላ ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 9:5፤ 1 ጴጥሮስ 3:5, 6) እውነቱን ለመናገር ሣራ ስለዚህ ጉዳይ ለአብርሃም ሳትናገር ቀርታ ቢሆን ኖሮ ለእሱ አክብሮት እንዳላሳየች ይቆጠር ነበር፤ ምክንያቱም ጉዳዩ በእሱም ሆነ በቤተሰቡ ላይ ከባድ ጉዳት የሚያስከትል ይሆን ነበር። ሣራ መናገር ያለባትን ነገር በፍቅር ተነሳስታ ተናግራለች።

ብዙ ሚስቶች ሣራ የተወችውን ምሳሌ ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። ከባሎቻቸው ጋር በሐቀኝነትና በአክብሮት የሐሳብ ልውውጥ ማድረግን ከእሷ ይማራሉ። አንዳንድ ሚስቶች ይሖዋ ከሣራ ጋር በተያያዘ እንዳደረገው ጣልቃ እንዲገባ የሚመኙበት ጊዜ ይኖር ይሆናል። ያም ቢሆን ሣራ ካሳየችው አስደናቂ እምነት፣ ፍቅርና ትዕግሥት ትምህርት ይወስዳሉ።

ይሖዋ ሣራን “ልዕልት” ብሎ ቢጠራትም እሷ እንደ ልዕልት እንድትከበር አልጠበቀችም

ሣራ፣ ይሖዋ ራሱ “ልዕልት” ብሎ ቢጠራትም እንኳ እንደ ልዕልት እንድትከበር አልጠበቀችም። በ127 ዓመቷ በሞተችበት ወቅት አብርሃም ‘ማዘኑና ማልቀሱ’ ምንም አያስደንቅም። * (ዘፍጥረት 23:1, 2) አብርሃም “ልዕልት” ተብላ የተጠራችውንና የሚወዳትን ሚስቱን በማጣቱ በጣም እንዳዘነ ጥርጥር የለውም። ይሖዋ አምላክም ይህች ታማኝ ሴት በመሞቷ እንደሚያዝንና ገነት በሆነች ምድር ላይ ከሞት ሊያስነሳት እንደሚጓጓ ጥያቄ የለውም። ሣራም ሆነች እሷን በእምነቷ የሚመስሉ ሁሉ እጅግ አስደሳች የሆነ ዘላለማዊ ሕይወት ይጠብቃቸዋል።—ዮሐንስ 5:28, 29

^ አን.3 እነዚህ ባልና ሚስት፣ አምላክ ስማቸውን እስከለወጠበት ጊዜ ድረስ አብራምና ሦራ ተብለው ይጠሩ ነበር፤ ይሁን እንጂ ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል በብዙዎች ዘንድ በጣም በሚታወቀው ስማቸው እንጠቀማለን።

^ አን.10 ይሖዋ ከአንድ ሚስት በላይ የማግባትና ቁባት የማስቀመጥ ልማድ ለተወሰነ ጊዜ እንዲቀጥል ፈቅዶ ነበር፤ ከጊዜ በኋላ ግን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ አምላክ መጀመሪያ በኤደን ያቋቋመውን አንድ ሚስት ብቻ የማግባት ሥርዓት ልንከተል እንደሚገባ አስተምሯል።—ዘፍጥረት 2:24፤ ማቴዎስ 19:3-9

^ አን.25 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት ሴቶች መካከል በስንት ዓመቷ እንደሞተች የተገለጸችው ሣራ ብቻ ናት።