በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 03

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት መጣል ትችላለህ?

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት መጣል ትችላለህ?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በርካታ ተስፋዎችና ምክሮች ይገኛሉ። ከዚህ አንጻር መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚያስተምረው ነገር ለማወቅ ብትጓጓም በውስጥህ የተወሰነ ጥርጣሬ ያድርብህ ይሆናል። እንዲህ ያለ ጥንታዊ መጽሐፍ በሚሰጠው ተስፋና በያዘው ምክር ላይ እምነት መጣል ይቻላል? መጽሐፍ ቅዱስ አሁንም ሆነ ወደፊት ደስተኛ መሆን ስለሚቻልበት መንገድ የሚናገረውን ሐሳብ ልትተማመንበት ትችላለህ? በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበት መጽሐፍ እንደሆነ ይሰማቸዋል። አንተም እንዲህ ብሎ ለማመን የሚያበቁትን ምክንያቶች እንድትመረምር እንጋብዝሃለን።

1. በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ አስተማማኝ መረጃ የያዘ መጽሐፍ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ “የእውነትን ቃል በትክክል” መዝግቦ እንደያዘ ይናገራል። (መክብብ 12:10) በእውነታው ዓለም ስለኖሩ ሰዎችና በትክክል ስለተፈጸሙ ክንውኖች ይገልጻል። (ሉቃስ 1:3⁠ን እና 3:1, 2⁠ን አንብብ።) ብዙ የታሪክ ምሁራንና የአርኪኦሎጂ (የመሬት ቁፋሮ) ባለሙያዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ቀኖች፣ ሰዎች፣ ቦታዎችና ክንውኖች ትክክል መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

2. መጽሐፍ ቅዱስ ጊዜ ያለፈበት መጽሐፍ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ በተጻፈበት ዘመን የማይታወቁ በርካታ መረጃዎችን ይዟል። ለምሳሌ ያህል፣ ሳይንሳዊ ስለሆኑ ጉዳዮች ይናገራል። ስለ እነዚህ ጉዳዮች ከሚናገራቸው ሐሳቦች መካከል አብዛኞቹ በዘመኑ ተቀባይነት አላገኙም ነበር። ሆኖም ዘመናዊ ሳይንስ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር ትክክል መሆኑን አረጋግጧል። መጽሐፍ ቅዱስ “አሁንም ሆነ ለዘላለም፣ ምንጊዜም አስተማማኝ” ነው።—መዝሙር 111:8

3. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ በሚናገረው ነገር ላይ መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ‘ገና ያልተከናወኑትን ነገሮች’ አስቀድመው የሚናገሩ ትንቢቶች ይዟል። (ኢሳይያስ 46:10) በርካታ ታሪካዊ ክንውኖችን ከመፈጸማቸው ከረጅም ጊዜ በፊት በትክክል ተናግሯል። በተጨማሪም በዛሬው ጊዜ በዓለማችን ላይ የሚታየውን ሁኔታ አስደናቂ በሆነ መንገድ በዝርዝር ገልጿል። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን እንመለከታለን። እነዚህ ትንቢቶች በትክክል ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል!

ጠለቅ ያለ ጥናት

ዘመናዊ ሳይንስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚስማማው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን። በተጨማሪም አንዳንድ አስደናቂ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን እንመለከታለን።

4. ሳይንስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይስማማል

በጥንት ዘመን አብዛኞቹ ሰዎች ምድር በሆነ ነገር ላይ እንደተቀመጠች ያምኑ ነበር። ቪዲዮውን ተመልከቱ።

ከ3,500 ዓመታት ገደማ በፊት የተጻፈው የኢዮብ መጽሐፍ ምን እንደሚል ተመልከት። ኢዮብ 26:7ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • መጽሐፍ ቅዱስ ምድር ‘ያለምንም ነገር እንደተንጠለጠለች’ የሚናገር መሆኑ አስገራሚ የሆነው ለምንድን ነው?

ፀሐይ በውቅያኖሶች ላይ ያለው ውኃ እንዲተን ታደርጋለች። ከዚያም የተነነው ውኃ ዝናብ ሆኖ ከወረደ በኋላ ወደ ውቅያኖሶች ተመልሶ ይገባል። እስከ 1800ዎቹ ዓመታት ድረስ ሰዎች ይህን የውኃ ዑደት በሚገባ አልተረዱትም ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ግን በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ምን እንዳለ ተመልከት። ኢዮብ 36:27, 28ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • ስለ ውኃ ዑደት ቀለል ባለ መንገድ የሚናገረው ይህ ሐሳብ አስገራሚ የሆነው ለምንድን ነው?

  • አሁን ያነበብካቸው ጥቅሶች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለህን እምነት ያጠናክሩታል?

5. መጽሐፍ ቅዱስ ወሳኝ ስለሆኑ ክንውኖች አስቀድሞ ተናግሯል

ኢሳይያስ 44:27–45:2ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • ባቢሎን ከመውደቋ ከ200 ዓመት በፊት መጽሐፍ ቅዱስ የትኞቹን ዝርዝር ጉዳዮች አስቀድሞ ተናግሯል?

የፋርስ ንጉሥ ቂሮስና ሠራዊቱ በ539 ዓ.ዓ. a የባቢሎንን ከተማ ድል እንዳደረጉ ታሪክ ያረጋግጣል። ከተማዋን ከጥቃት ይከላከል የነበረውን ወንዝ አቅጣጫ እንዲቀይር አድርገውታል። ክፍት በተተዉት በሮች በመግባት ከተማዋን ያለምንም ውጊያ መቆጣጠር ችለዋል። ይህ ከሆነ ከ2,500 የሚበልጡ ዓመታት ቢያልፉም ባቢሎን አሁንም እንደፈራረሰች ትገኛለች። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ትንቢት ተናግሮ እንደነበር ተመልከት።

ኢሳይያስ 13:19, 20ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • በባቢሎን ላይ የደረሰው ነገር ይህ ትንቢት በትክክል እንደተፈጸመ የሚያሳየው እንዴት ነው?

በዛሬው ጊዜ በኢራቅ የሚገኘው የባቢሎን ፍርስራሽ

6. መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ በዓለማችን ላይ ስለሚታዩት ነገሮች አስቀድሞ ተናግሯል

መጽሐፍ ቅዱስ አሁን የምንኖርበትን ዘመን ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ በማለት ይጠራዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጊዜ አስመልክቶ ምን ትንቢት እንደያዘ ተመልከት።

ማቴዎስ 24:6, 7ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተለው ጥያቄ ላይ ተወያዩ፦

  • መጽሐፍ ቅዱስ በመጨረሻዎቹ ቀናት ምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚኖር ተናግሯል?

ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 3:1-5ን አንብቡ፤ ከዚያም በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ተወያዩ፦

  • መጽሐፍ ቅዱስ በመጨረሻዎቹ ቀናት የሚኖሩት አብዛኞቹ ሰዎች ምን ዓይነት ባሕርይ እንደሚኖራቸው ተናግሯል?

  • አንተ በግልህ የትኞቹን ባሕርያት በሰዎች ላይ ተመልክተሃል?

አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፦ “መጽሐፍ ቅዱስ ተረትና አፈ ታሪክ ነው።”

  • አንተ ‘መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበት መጽሐፍ ነው’ ብለህ እንድታምን የሚያደርግህ ዋነኛው ማስረጃ ምንድን ነው?

ማጠቃለያ

ከታሪክ፣ ከሳይንስና ከትንቢቶች የሚገኘው ማስረጃ መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበት መጽሐፍ እንደሆነ ይጠቁማል።

ክለሳ

  • በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ አስተማማኝ መረጃ የያዘ መጽሐፍ ነው?

  • መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ ጋር እንደሚስማማ የሚያሳዩ አንዳንድ ማስረጃዎች የትኞቹ ናቸው?

  • መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ሊነግረን የሚችል ይመስልሃል? እንዲህ ብለህ የመለስከው ለምንድን ነው?

ግብ

ምርምር አድርግ

ከሳይንስ አንጻር ስህተት የሆነ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አለ?

“መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ ጋር ይስማማል?” (ድረ ገጻችን ላይ የወጣ ርዕስ)

‘የመጨረሻዎቹን ቀናት’ በተመለከተ እውነታው ምንድን ነው?

“6 የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ሲፈጸሙ እያየህ ነው” (መጠበቂያ ግንብ ግንቦት 1, 2011)

ስለ ግሪክ ኃያል መንግሥት የሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዴት እንደሆነ ተመልከት።

“ትንቢታዊው ቃል” ብርታት ይሰጣል (5:22)

አንድ ሰው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ሲያውቅ ለመጽሐፍ ቅዱስ ያለው አመለካከት የተለወጠው እንዴት እንደሆነ አንብብ።

“አምላክ እንደሌለ ይሰማኝ ነበር” (መጠበቂያ ግንብ ቁጥር 5 2017)

a ዓ.ዓ. ሲባል ዓመተ ዓለም ማለት ነው፤ ዓ.ም. ደግሞ ዓመተ ምሕረት ማለት ነው።