በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

“ስልካችሁን ስጠብቅ ነበር”

“ስልካችሁን ስጠብቅ ነበር”

 ኤድ እና ባለቤቱ ጄኒ ለመጀመሪያ ጊዜ በስልክ ምሥክርነት የተካፈሉት በ2010 ነበር። a ጄኒ “ጨርሶ አልወደድኩትም። ለባለቤቴ ‘ድጋሚ አልሞክረውም’ አልኩት” ብላለች። የኤድም ስሜት ተመሳሳይ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ምርትና አገልግሎታቸውን በስልክ የሚያስተዋውቁ ሰዎች ሲደውሉልኝ ደስ አይለኝም፤ ስለዚህ እኔም በስልክ መመሥከርን ሳስበው እንኳ ይከብደኛል።”

 ከዚያም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመከሰቱ የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት መስበካቸውን አቆሙ። ሆኖም ኢየሱስ ምሥራቹን እንዲሰብኩ የሰጣቸውን ትእዛዝ በመከተል አገልግሎታቸውን ቀጠሉ፤ በአብዛኛው በደብዳቤና በስልክ አማካኝነት መስበክ ጀመሩ። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) ከዚህም ሌላ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎችን ጨምሮ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በሙሉ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት መካሄድ ጀመሩ። በአንድ ወቅት፣ ኤድ በስምሪት ስብሰባ ላይ ራሱን አደፋፍሮ የስልክ ምሥክርነት ለመስጠት ወሰነ። የመጀመሪያውን ስልክ ሊደውል ሲል ምን ተሰማው? “በጣም ስለፈራሁ ይሖዋ እንዲረዳኝ ጸለይኩ!” ብሏል። “ከዚያም ስልክ ደወልኩ። ከታይሮን ጋር የተገናኘነው በዚህ ወቅት ነው።” b

 ታይሮንና ባለቤቱ ኤዲት የሚኖሩት በኬንታኪ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሚገኝ ገጠራማ አካባቢ ነው። የ83 ዓመት አረጋዊ የሆነው ታይሮን የማየት ችግር አለበት። ያም ቢሆን ከኤድ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማ። የማስጠኛ ጽሑፉን በአጉሊ መነጽር እያነበበ ከኤድ ጋር በቋሚነት በስልክ ማጥናት ጀመረ።

 ከአንድ ወር ገደማ በኋላ ታይሮንና ኤዲት በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመሩ። ሆኖም ኢንተርኔት ስላልነበራቸው ስብሰባውን የሚከታተሉት በስልክ ነበር። የኤዲትን ፍላጎት የቀሰቀሰው ምንድን ነው?

 ኤድ እና ጄኒ፣ ታይሮንን ሲያስጠኑ ከበስተ ጀርባ የኤዲትን ድምፅ ይሰሙ ነበር፤ ኤዲት ለታይሮን የጥያቄዎቹን መልስ ትጠቁመው እንዲሁም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እንዲያወጣ ትረዳው ነበር። ሆኖም ከዚህ የዘለለ ተሳትፎ አታደርግም። ጄኒ “ድምፅዋ ላይ የሐዘን ስሜት ይነበብ ነበር፤ ሆኖም እኔም ሆንኩ ኤድ ምክንያቱን አላወቅንም” ብላለች።

ኤድ እና ጄኒ በስልክ ሲመሠክሩ

 አንድ ቀን ጄኒ ኤዲትን እንድታነጋግራት ውስጧ ገፋፋት። ስለዚህ ተስማሚ ጊዜ መርጣ ኤድ ስልኩን እንዲሰጣት ጠየቀችው። ከዚያም “ታይሮን፣ የባለቤትህ ድምፅ ከበስተ ጀርባ ይሰማኛል፤ አንድ ጥቅስ እንድታነብ ወይም ሐሳብ እንድትሰጥ ብጠይቃት ደስ ይለኛል” አለች።

 ኤዲት ለአፍታ ዝም ካለች በኋላ ለስለስ ባለ ድምፅ እንዲህ አለች፦ “እኔም ላነጋግራችሁ እፈልግ ነበር። የይሖዋ ምሥክር ነኝ። ከቀዘቀዝኩ 40 ዓመት ሆኖኛል።”

 ጄኒ በጣም ደነገጠች። “እህቴ ነሽ ማለት ነዋ!” ብላ ጮኸች። ከዚያም ተላቀሱ።

 ብዙም ሳይቆይ ኤድ ወደ ይሖዋ ተመለስ የተባለውን ብሮሹር ለኤዲት ሰጣት። በቀጣዮቹ ሳምንታት ኤድ እና ጄኒ በኤዲት ላይ ትልቅ ለውጥ አስተዋሉ። ኤድ እንዲህ ብሏል፦ “መጀመሪያ አካባቢ ድምፅዋ ላይ ከፍተኛ ሐዘን ይነበብ ነበር፤ አሁን ግን ደስተኛ መሆኗ ከድምፅዋ ያስታውቃል።” ኤዲት ጥሩ መንፈሳዊ እድገት አድርጋ በድጋሚ ምሥራቹን በደስታ መስበክ ጀምራለች። ባለቤቷ ደግሞ ሐምሌ 2022 ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ።

 ኤድ ቀደም ሲል የስልክ ምሥክርነትን አስመልክቶ የነበረውን አመለካከት ሲያስብ ከታይሮን ጋር ያደረገውን አንድ ውይይት ያስታውሳል። ኤድ ለታይሮን ዮሐንስ 6:44⁠ን ካነበበለት በኋላ ሰዎችን ወደ እውነት የሚስበው ይሖዋ እንደሆነ አብራራለት። ታይሮንም በዚህ ሐሳብ ተስማማ፤ ከዚያም “እኔም እኮ ስልካችሁን ስጠብቅ ነበር” አለ። ጄኒም እሷና ባለቤቷ ራሳቸውን አደፋፍረው በስልክ ለመስበክ በመሞከራቸው ደስተኛ ናት። “ይሖዋ እንዲህ ያለውን ጥረት ይባርካል” ብላለች።

a የይሖዋ ምሥክሮች አገልግሎታቸውን የሚያከናውኑት ከመረጃ ደህንነት ጋር የተያያዙ ሕጎችን በማይጥስ መልኩ ነው።

b አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።