በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

“የገዛ መቃብሬን እየቆፈርኩ ነበር”

“የገዛ መቃብሬን እየቆፈርኩ ነበር”
  • የትውልድ ዘመን፦ 1978

  • የትውልድ አገር፦ ኤል ሳልቫዶር

  • የኋላ ታሪክ፦ ዓመፀኛና የወሮበሎች ቡድን አባል የነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ

 “ስለ አምላክ ከልብህ ማወቅ የምትፈልግ ከሆነ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናትህን ቀጥል።” ይህን ሐሳብ ስሰማ ጆሮዬን ማመን አልቻልኩም። በዚያ ወቅት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ከጀመርኩ የተወሰነ ጊዜ አልፎ ነበር። ይህን ሐሳብ ስሰማ በጣም የተገረምኩት ለምን እንደሆነ በደንብ እንዲገባችሁ ቀደም ሲል ስለነበረኝ ሕይወት ጥቂት ላጫውታችሁ።

 የተወለድኩት ኤል ሳልቫዶር በምትገኘው በኬሶልቴፔኬ ከተማ ነው። ወላጆቼ 15 ልጆች ያሏቸው ሲሆን እኔ ስድስተኛ ልጅ ነኝ። ወላጆቼ ሐቀኛና ሕግ አክባሪ እንድሆን አድርገው ለማሳደግ ይጥሩ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ሌኦናርዶ እና ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሊያስተምሩን ብዙ ጊዜ ይመጡ ነበር። እኔ ግን የተማርኩትን ነገር ችላ በማለት በርካታ መጥፎ ውሳኔዎች አደረግኩ። የ14 ዓመት ልጅ ሳለሁ ከትምህርት ቤት ጓደኞቼ ጋር የአልኮል መጠጥ መጠጣትና ዕፅ መውሰድ ጀመርኩ። ውሎ አድሮም እነዚህ ጓደኞቼ ትምህርታቸውን አቋርጠው አንድን የወሮበሎች ቡድን ተቀላቀሉ፤ እኔም የእነሱን መጥፎ ምሳሌ ተከተልኩ። ጊዜያችንን የምናሳልፈው ጎዳና ላይ ሲሆን ሰዎች ገንዘብ እንዲሰጡን እንጠይቅ እንዲሁም ሱሳችንን ለማርካት ስንል እንሰርቅ ነበር።

 የወሮበሎች ቡድኑን የምመለከተው እንደ ቤተሰቤ ነበር። ለቡድኑ ምንጊዜም ታማኝ መሆን እንዳለብኝ ይሰማኝ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ቀን አንዱ የቡድናችን አባል ዕፅ ወስዶ ከጎረቤቶቼ መካከል አንዱን መማታት ጀመረ። ጎረቤቴም በድብድቡ ጓደኛዬን ካሸነፈው በኋላ ፖሊስ ጠራ። በዚህ በጣም ስለተናደድኩ ጓደኛዬን ለማስለቀቅ ስል የጎረቤቴን መኪና በዱላ መሰባበር ጀመርኩ። መስታወቶቹን እየሰባበርኩ እና መኪናውን እየደበደብኩ ሳለ ጎረቤቴ እንዳቆም ይለምነኝ ነበር፤ እኔ ግን እሱን ለመስማት ፈቃደኛ አልሆንኩም።

 የ18 ዓመት ልጅ ሳለሁ፣ የወሮበሎች ቡድናችን ከፖሊሶች ጋር ተጋጨ። በዚህ ግጭት ላይ ቦምብ ልወረውር ስል ቦምቡ ቀድሞ እጄ ላይ ፈነዳ፤ እንዴት ሊፈነዳ እንደቻለ በትክክል አላውቅም። የማስታውሰው ነገር ቢኖር ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበትን እጄን ማየቴን ብቻ ነው፤ ከዚያም ራሴን ሳትኩ። ሆስፒታል ውስጥ ስነቃ ቀኝ እጄ እንደተቆረጠና ቀኝ ጆሮዬ መስማት እንደማይችል አወቅኩ፤ ቀኝ ዓይኔም ቢሆን የታወረ ያህል ሆኖ ነበር።

 ከፍተኛ ጉዳት የደረሰብኝ ቢሆንም ከሆስፒታል እንደወጣሁ በቀጥታ የሄድኩት ወደ ወሮበሎች ቡድናችን ነው። ሆኖም ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ፖሊሶች በቁጥጥር ሥር አዋሉኝና ታሰርኩ። እስር ቤት ስገባ ከወሮበሎች ቡድናችን አባላት ጋር ያለኝ ወዳጅነት ይበልጥ ተጠናከረ። ጠዋት የመጀመሪያውን ማሪዋና ከምናጨስበት ሰዓት አንስቶ እስከምንተኛበት ሰዓት ድረስ ቀኑን ሙሉ አብረን እናሳልፍ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

 እስር ቤት ሳለሁ ሌኦናርዶ ሊጠይቀኝ መጣ። እየተጫወትን እያለ በቀኝ ክንዴ ላይ ያለውን ንቅሳት እየጠቆመ “ንቅሳትህ ላይ ያሉት ሦስት ነጥቦች ምን እንደሚያመለክቱ ታውቃለህ?” ሲል ጠየቀኝ። እኔም “አዎ። የፆታ ግንኙነት፣ ዕፅ እንዲሁም ሮክ ኤንድ ሮል ሙዚቃ ናቸው” ብዬ መለስኩለት። ከዚያም ሌኦናርዶ እንዲህ አለኝ፦ “እኔ ግን ሆስፒታልን፣ እስር ቤትንና ሞትን እንደሚያመለክቱ ይሰማኛል። ሆስፒታል ገብተህ ነበር፤ አሁን እስር ቤት ነህ፤ ቀጥሎ ደግሞ ምን እንደሚጠብቅህ ታውቃለህ።”

 ሌኦናርዶ የተናገረው ነገር አስደነገጠኝ። ደግሞም የተናገረው ትክክል ነበር። በምከተለው አኗኗር የተነሳ የገዛ መቃብሬን እየቆፈርኩ ነበር። ሌኦናርዶ ከእሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እንዳጠና ጋበዘኝ፤ እኔም ግብዣውን ተቀበልኩ። ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርኩት ነገር በሕይወቴ ውስጥ ለውጥ ለማድረግ አነሳስቶኛል። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ “መጥፎ ጓደኝነት ጥሩውን ሥነ ምግባር ያበላሻል” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 15:33 ግርጌ) በመሆኑም ልወስደው የሚገባው የመጀመሪያ እርምጃ ጓደኞቼን መቀየር ነበር። ስለዚህ የወሮበሎች ቡድኑ በሚያደርገው ስብሰባ ላይ መካፈሌን ትቼ የይሖዋ ምሥክሮች በእስር ቤት ውስጥ በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ መገኘት ጀመርኩ። በስብሰባው ላይ አንድሬስ ከተባለ ሌላ እስረኛ ጋር ተዋወቅኩ፤ አንድሬስ ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር የሆነው እዚያው እስር ቤት ውስጥ እያለ ነበር። አንድሬስ አብሬው ቁርስ እንድበላ ጋበዘኝ። ከዚያ ቀን አንስቶ በጠዋት ማሪዋና ማጨሴን አቆምኩ። ከዚህ ይልቅ በየማለዳው ከአንድሬስ ጋር በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ እንወያይ ነበር።

 የወሮበሎች ቡድኑ አባላት ለውጥ እያደረግኩ እንዳለ ወዲያውኑ አስተውለው ነበር። በዚህ የተነሳ የወሮበሎች ቡድኑ መሪ ሊያነጋግረኝ እንደሚፈልግ ገለጸልኝ። በጣም ፈርቼ ነበር። ፍላጎቴ ምን እንደሆነ ቢያውቅ ምን ሊያደርስብኝ እንደሚችል አላውቅም ነበር፤ ምክንያቱም ከወሮበሎች ቡድን መውጣት የማይታሰብ ነገር ነው ሊባል ይችላል። የቡድኑ መሪ “በስብሰባችን ላይ መገኘት አቁመህ ወደ ይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ እንደምትሄድ አውቀናል። ሐሳብህ ምንድን ነው?” አለኝ። እኔም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቴን መቀጠልና ሕይወቴን መለወጥ እንደምፈልግ ነገርኩት። የሚያስገርመው ነገር፣ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ልባዊ ፍላጎት እንዳለኝ እስካሳየሁ ድረስ የወሮበሎች ቡድኑ ውሳኔዬን እንደሚያከብርልኝ ነገረኝ። ከዚያም እንዲህ አለኝ፦ “ስለ አምላክ ከልብህ ማወቅ የምትፈልግ ከሆነ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናትህን ቀጥል። መጥፎ ነገሮች ማድረግህን እንድታቆም እንጠብቅብሃለን። እንኳን ደስ አለህ! በትክክለኛው ጎዳና ላይ መጓዝ ጀምረሃል። የይሖዋ ምሥክሮች በሚገባ ይረዱሃል። ዩናይትድ ስቴትስ ሳለሁ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር አጠና ነበር፤ አንዳንድ የቤተሰቤ አባላትም የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። አትፍራ። በርታ።” በዚህ ወቅት ፍርሃቴ ሙሉ በሙሉ ባይለቀኝም ልዩ ደስታ ተሰማኝ። ይሖዋ አምላክን በልቤ አመሰገንኩት። ከትከሻዬ ላይ ትልቅ ሸክም የወረደልኝ ያህል ሆኖ ተሰማኝ፤ እንዲሁም ኢየሱስ ‘እውነትን ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል’ በማለት የተናገራቸውን ቃላት መረዳት ቻልኩ።—ዮሐንስ 8:32

 ይሁን እንጂ አንዳንድ የቀድሞ ጓደኞቼ ዕፅ እንድወስድ በመገፋፋት ይፈትኑኝ ነበር። እኔም አንዳንድ ጊዜ በፈተናው እንደተሸነፍኩ አልክድም። ያም ቢሆን ደጋግሜ ከልቤ በመጸለዬ ውሎ አድሮ ያሉብኝን ሱሶች ማስወገድ ችያለሁ።—መዝሙር 51:10, 11

 ብዙዎች ከእስር ከተፈታሁ በኋላ ወደ ቀድሞ አኗኗሬ እንደምመለስ ጠብቀው ነበር፤ እኔ ግን አልተመለስኩም። ከዚህ ይልቅ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርኩትን ነገር ለሌሎች እስረኞች ለማስተማር አዘውትሬ ወደ እስር ቤት እሄዳለሁ። ውሎ አድሮ የቀድሞ ጓደኞቼ በሕይወቴ ውስጥ ለውጥ ማድረጌን አምነው ተቀበሉ። የሚያሳዝነው ግን የቀድሞ ጠላቶቼ እንዲህ ያለ አመለካከት አልነበራቸውም።

 አንድ ቀን ከአንድ ወንድም ጋር እያገለገልን ሳለ ቀደም ሲል የቡድናችን ተቀናቃኝ የነበረ አንድ የወሮበሎች ቡድን አባላት መሣሪያ ይዘው በድንገት ከበቡን፤ እነዚህ ሰዎች እኔ መግደል ይፈልጉ ነበር። የአገልግሎት ጓደኛዬ በትሕትና ሆኖም በድፍረት፣ ከወሮበሎች ቡድን መውጣቴን ገለጸላቸው። እኔም ራሴን ለማረጋጋት ሞከርኩ። ከደበደቡኝና ወደዚያ አካባቢ ድርሽ እንዳልል ካስጠነቀቁኝ በኋላ መሣሪያቸውን አውርደው እንድንሄድ ፈቀዱልን። መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥም ሕይወቴን ለውጦታል። በፊት ቢሆን ኖሮ ሰዎቹን ለመበቀል የምችለውን አድርግ ነበር። አሁን ግን በ1 ተሰሎንቄ 5:15 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ አደርጋለሁ። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ማንም ሰው በማንም ላይ በክፉ ፋንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፤ ከዚህ ይልቅ እርስ በርሳችሁም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ሁሉ ምንጊዜም መልካም የሆነውን ነገር ለማድረግ ተጣጣሩ።”

 የይሖዋ ምሥክር ከሆንኩበት ጊዜ አንስቶ ሐቀኛ ሰው ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ጀምሬያለሁ። እርግጥ ይህን ማድረግ ቀላል አልነበረም። ያም ቢሆን ከይሖዋ አምላክ ባገኘሁት እርዳታ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ባገኘሁት ምክር እንዲሁም አዳዲስ ጓደኞቼ ባደረጉልኝ ድጋፍ ሊሳካልኝ ችሏል። ወደ ቀድሞ አኗኗሬ ፈጽሞ መመለስ አልፈልግም።—2 ጴጥሮስ 2:22

ያገኘሁት ጥቅም

 ቀደም ሲል ዓመፀኛና ቁጡ ሰው ነበርኩ። በዚያ መጥፎ አኗኗሬ ገፍቼበት ቢሆን ኖሮ ዛሬ በሕይወት እንደማልገኝ እርግጠኛ ነኝ። ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርኩት ነገር ለውጦኛል። ከሱሶቼ መላቀቅ ችያለሁ። ከቀድሞ ጠላቶቼ ጋር እንኳ በሰላም መኖር ችያለሁ። (ሉቃስ 6:27) በአሁኑ ጊዜ፣ መልካም ባሕርያትን እንዳዳብር የሚረዱኝ ጥሩ ወዳጆች አሉኝ። (ምሳሌ 13:20) ዓላማ ያለው ደስተኛ ሕይወት እየመራሁ ነው፤ የሠራኋቸውን መጥፎ ነገሮች ሁሉ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ የሆነውን አምላክ እያገለገልኩ እገኛለሁ።—ኢሳይያስ 1:18

 በ2006፣ ላላገቡ ክርስቲያን ወንጌላውያን በተዘጋጀ ትምህርት ቤት ውስጥ ልዩ ሥልጠና መውሰድ ችያለሁ። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ውዷ ባለቤቴን ያገባሁ ሲሆን አሁን ሴት ልጃችንን አብረን እያሳደግን ነው። አብዛኛውን ጊዜዬን የማሳልፈው በሕይወቴ ውስጥ ለውጥ እንዳደርግ የረዱኝን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ለሌሎች በማስተማር ነው። በተጨማሪም በጉባኤያችን ውስጥ ሽማግሌ ሆኜ አገለግላለሁ። በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወጣቶች እኔ በእነሱ ዕድሜ ሳለሁ የሠራኋቸውን ስህተቶች እንዳይደግሙ ለመርዳት እጥራለሁ። በአሁኑ ጊዜ፣ የገዛ መቃብሬን ከመቆፈር ይልቅ አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሰጠው ተስፋ መሠረት የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ተግቼ እየሠራሁ ነው።