በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

“ቁጣዬን መቆጣጠር አልችልም ነበር”

“ቁጣዬን መቆጣጠር አልችልም ነበር”
  • የትውልድ ዘመን፦ 1975

  • የትውልድ አገር፦ ሜክሲኮ

  • የኋላ ታሪክ፦ ቁጣውን መቆጣጠር የማይችልና ወንጀለኛ የነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ

 የተወለድኩት የሜክሲኮ ግዛት በሆነችው በቺያፓስ በምትገኝ ሳን ሁዋን ቻንካላይቶ የምትባል ትንሽ ከተማ ውስጥ ነው። ቤተሰቦቼ የማያ ዝርያ የሆነው ቾል የሚባል ጎሣ አባላት ናቸው። ወላጆቼ 12 ልጆች የነበሯቸው ሲሆን እኔ አምስተኛ ልጅ ነኝ። ትንሽ ልጅ ሳለሁ፣ እኔም ሆንኩ ወንድሞቼና እህቶቼ መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እናጠና ነበር። የሚያሳዝነው ግን በወጣትነቴ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ ማድረግ አልቻልኩም ነበር።

 አሥራ ሦስት ዓመት ሲሆነኝ ዕፅ መውሰድ እንዲሁም መስረቅ ጀመርኩ። በዚያ ዕድሜዬ ከቤት ወጥቼ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወርኩ መኖር ጀመርኩ። የ16 ዓመት ልጅ ሳለሁ በአንድ የማሪዋና እርሻ ላይ መሥራት ጀመርኩ። ለአንድ ዓመት ያህል በዚያ ሠራሁ፤ አንድ ቀን በምሽት ማሪዋና በጀልባ ጭነን ስንሄድ የተቀናቃኝ ዕፅ አዘዋዋሪ ቡድን አባላት የሆኑ መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች ጥቃት ሰነዘሩብን። ጥይት ሲተኩሱብን ለማምለጥ ዘልዬ ወደ ወንዙ ገባሁ፤ ከዚያም የተወሰነ ርቀት ከዋኘሁ በኋላ ከወንዙ ወጣሁ። በኋላም ሸሽቼ ዩናይትድ ስቴትስ ገባሁ።

 ዩናይትድ ስቴትስ ከሄድኩ በኋላም ዕፅ ማዘዋወሬንና ወንጀል መፈጸሜን ቀጠልኩ። በ19 ዓመቴ በዝርፊያና በግድያ ሙከራ ወንጀል ተከስሼ እስር ቤት ገባሁ። እስር ቤት ውስጥም ከአንድ የወንጀለኞች ቡድን ጋር በመቀላቀል ተጨማሪ የዓመፅ ድርጊቶች መፈጸሜን ቀጠልኩ። በዚህ ምክንያት የእስር ቤቱ ባለሥልጣናት በሉዊስበርግ፣ ፔንስልቬንያ ወደሚገኝ ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግበት እስር ቤት አዛወሩኝ።

 ሉዊስበርግ በሚገኘው እስር ቤት ውስጥ ባሕርዬ ይበልጥ ተበላሸ። የአንድ ወንጀለኞች ቡድን ንቅሳት ስለነበረኝ በዚህኛው እስር ቤት ካሉ የቡድኑ አባላት ጋር በቀላሉ ተቀላቀልኩ። ይበልጥ ዓመፀኛ የሆንኩ ሲሆን በተደጋጋሚ ከሰዎች ጋር እጣላ ነበር። በአንድ ወቅት በእስር ቤቱ ሜዳ ላይ የቡድን ጸብ ተነስቶ ተደባደብን። የተደባደብነው በቤዝ ቦል መጫወቻ ዱላና በክብደት ማንሻ ብረት ጭምር ነበር። የእስር ቤቱ ጠባቂዎች ድብድቡን ለማስቆም አስለቃሽ ጭስ መጠቀም አስፈልጓቸው ነበር። ከዚያ በኋላ የእስር ቤቱ ባለሥልጣናት አደገኛ እስረኞች በሚጠበቁበት ልዩ ቁጥጥር የሚደረግበት ክፍል አስገቡኝ። ቁጣዬን መቆጣጠር አልችልም ነበር፤ እንዲሁም ተሳዳቢ ነበርኩ። ሰዎችን ለመደብደብ ትንሽ ነበር የሚበቃኝ። እንዲያውም ሰው መደብደብ ያስደስተኝ ነበር። በፈጸምኩት ድርጊት ጨርሶ ጸጸት ተሰምቶኝ አያውቅም ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

 ልዩ ቁጥጥር በሚደረግበት ክፍል ውስጥ ታስሬ እያለሁ አብዛኛውን ጊዜዬን የማሳልፈው ክፍሌ ውስጥ ነበር። በመሆኑም እንደ ጊዜ ማሳለፊያ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ጀመርኩ። በኋላም አንዲት የእስር ቤቱ ጠባቂ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ a የተባለውን መጽሐፍ ሰጠችኝ። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚያገለግለውን ይህን መጽሐፍ ሳነብ በልጅነቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ሳጠና የተማርኳቸውን በርካታ ነገሮች አስታወስኩ። ከዚያም በዓመፀኝነት ባሕርዬ ምክንያት ሕይወቴ ምን ያህል እንደተበላሸ ማሰብ ጀመርኩ። ስለ ቤተሰቤም አሰብኩ። ሁለቱ እህቶቼ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነው ነበር፤ ስለዚህ ‘እነሱ እኮ የዘላለም ሕይወት ሊያገኙ ነው። እኔስ ምን ያግደኛል?’ ብዬ ራሴን ጠየቅኩ። ለውጥ ለማድረግ የቆረጥኩት በዚህ ጊዜ ነበር።

 ይሁን እንጂ ለውጥ ለማድረግ የግድ ተጨማሪ እርዳታ ማግኘት እንደሚያስፈልገኝ ገብቶኝ ነበር። ስለዚህ መጀመሪያ ወደ ይሖዋ በመጸለይ እንዲረዳኝ ለመንኩት። ከዚያም በዩናይትድ ስቴትስ ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንደምፈልግ የሚገልጽ ደብዳቤ ጻፍኩ። ቅርንጫፍ ቢሮውም በአቅራቢያዬ የሚገኝ አንድ ጉባኤ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስጠናኝ ሰው እንዲመድብልኝ ዝግጅት አደረገ። በወቅቱ የቤተሰቤ አባል ያልሆነ ሰው መጥቶ እንዲጎበኘኝ አይፈቀድልኝም ነበር፤ በመሆኑም በዚያ ጉባኤ ውስጥ ያለ አንድ የይሖዋ ምሥክር አበረታች የሆኑ ደብዳቤዎችንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ይልክልኝ ጀመር፤ ይህም ለውጥ ለማድረግ ያለኝን ፍላጎት ይበልጥ አጠናክሮልኛል።

 ቀጥሎ የወሰድኩት ትልቅ እርምጃ ለበርካታ ዓመታት አባል የሆንኩበትን የወንጀለኞች ቡድን መልቀቅ ነበር። የቡድኑ መሪም የታሰረው ልዩ ቁጥጥር በሚደረግበት ክፍል ውስጥ ነበር፤ ስለዚህ በመዝናኛ ሰዓታችን ላይ ወደ እሱ ሄጄ የይሖዋ ምሥክር መሆን እንደምፈልግ ነገርኩት። የሚገርመው ነገር “እውነት የይሖዋ ምሥክር መሆን ፈልገህ ከሆነ ትችላለህ። ከአምላክ ጋር ባለህ ግንኙነት ጣልቃ ልገባ አልችልም። ከቡድኑ ለመውጣት ፈልገህ ብቻ ከሆነ ግን ምን እንደሚጠብቅህ ታውቃለህ” አለኝ።

 በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በእስር ቤቱ የሚሠሩት ሰዎች ባሕርዬ እየተሻሻለ መሆኑን አስተዋሉ። በዚህም ምክንያት እኔን የሚይዙበት መንገድ ተቀየረ። ለምሳሌ ያህል ጠባቂዎቹ ወደ መታጠቢያ ቤት ሲወስዱኝ እጄን በካቴና ማሰር አቆሙ። አንዱ ጠባቂ ደግሞ ለውጥ ማድረጌን እንድቀጥል አበረታቶኛል። እንዲያውም በእስር ቤት ያሳለፍኩት የመጨረሻ ዓመት ላይ ዋናው እስር ቤት አቅራቢያ ወደሚገኝ እምብዛም ቁጥጥር የማይደረግበት ካምፕ ተዛውሬ ነበር። ለአሥር ዓመት ከታሰርኩ በኋላ ከእስር ቤት ወጣሁ፤ ከዚያም በእስረኞች አውቶቡስ ተጭኜ ወደ ሜክሲኮ ተወሰድኩ።

 ሜክሲኮ ከደረስኩ በኋላ ብዙም ሳልቆይ የይሖዋ ምሥክሮችን የስብሰባ አዳራሽ ፈልጌ አገኘሁ። የመጀመሪያ ስብሰባዬን የተካፈልኩት የእስር ቤቱን ዩኒፎርም ለብሼ ነው፤ ምክንያቱም የነበረኝ ብቸኛ ሥርዓታማ ልብስ እሱ ነበር። ሁኔታዬ የሚማርክ ባይሆንም በጉባኤው ውስጥ ያሉት ወንድሞች ሞቅ ባለ መንፈስ ተቀበሉኝ። ደግነታቸውን ስመለከት በእርግጥም እውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል እንዳለሁ ተሰማኝ። (ዮሐንስ 13:35) የጉባኤው ሽማግሌዎች መደበኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንድጀምር በዚያው ቀን ዝግጅት አደረጉልኝ። ከአንድ ዓመት በኋላ ማለትም መስከረም 3, 2005 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።

 ጥር 2007 ላይ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ በመሆን በየወሩ ለ70 ሰዓት ያህል ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስተማር ጀመርኩ። በ2011 ለነጠላ ወንድሞች በተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት (አሁን የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ይባላል) ገብቼ ተማርኩ። ትምህርት ቤቱ በጉባኤ ውስጥ ያሉኝን ኃላፊነቶች እንድወጣ በእጅጉ ረድቶኛል።

በአሁኑ ጊዜ ሰዎች ሰላማዊ እንዲሆኑ ማስተማር ያስደስተኛል

 በ2013 ውዷን ባለቤቴን ፒላርን አገባሁ። ፒላር ስለ ቀድሞ ሕይወቴ የምነግራትን ነገር ለማመን እንደሚከብዳት በቀልድ መልክ ትናገራለች። ምክንያቱም የቀድሞ ልማዴ አገርሽቶብኝ አያውቅም። በእኔ ሕይወት ላይ የታየው ለውጥ መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥም የሰዎችን ሕይወት የመለወጥ ኃይል እንዳለው የሚያሳይ ማስረጃ እንደሆነ እኔም ሆንኩ ባለቤቴ ይሰማናል።—ሮም 12:2

ያገኘሁት ጥቅም

 ኢየሱስ “[የመጣሁት] የጠፋውን ለመፈለግና ለማዳን ነው” በማለት በሉቃስ 19:10 ላይ የተናገረው ሐሳብ ለእኔ እንደሚሠራ ይሰማኛል። በአሁኑ ጊዜ የሕይወት አቅጣጫ እንደጠፋኝ አይሰማኝም። እንዲሁም እንደ ቀድሞው በሰዎች ላይ ጉዳት አላደርስም። ለመጽሐፍ ቅዱስ ምስጋና ይግባውና ሕይወቴ ትርጉም ያለው ሆኗል፤ ከሌሎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት አለኝ፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ ከፈጣሪዬ ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት ችያለሁ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ይህ መጽሐፍ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ ሲሆን አሁን መታተም አቁሟል። በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት በዋነኝነት የሚጠቀሙት ለዘላለም በደስታ ኑር! በተባለው መጽሐፍ ነው።