በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል

በመጨረሻ ከአባቴ ጋር ሰላም ፈጠርን

በመጨረሻ ከአባቴ ጋር ሰላም ፈጠርን
  • የትውልድ ዘመን፦ 1954

  • የትውልድ አገር፦ ፊሊፒንስ

  • የኋላ ታሪክ፦ ተደባዳቢ ከነበረው አባቱ ጋር ተራርቆ የነበረ

የቀድሞ ሕይወቴ

 በርካታ ጎብኚዎች ፊሊፒንስ ውስጥ ባለችው ፓግሳንሃን ከተማ አቅራቢያ የሚገኙትን ዝነኛ ፏፏቴዎች ለማየት ይመጣሉ። አባቴ ናርዶ ለሮን ያደገው በዚያ አካባቢ ሲሆን ቤተሰቦቹ ድሆች ነበሩ። አባቴ በመንግሥት ተቋማትና በፖሊስ ኃይል ውስጥ እንዲሁም በሥራ ቦታው ይመለከት የነበረው ምግባረ ብልሹነት ስላስመረረው ብስጩ ነበር።

 ወላጆቼ ስምንት ልጆቻቸውን ለማሳደግ ተግተው ይሠሩ ነበር። በተራራ ላይ የሚገኘውን እርሻ ለመከታተል ብዙውን ጊዜ ከቤት ርቀው ይሠሩ ነበር። በዚህም ምክንያት እኔና ወንድሜ ሮዲሊዮ ራሳችንን መንከባከብ ነበረብን፤ እንዲያውም ብዙ ጊዜ እንራብ ነበር። ልጆች ብንሆንም ለጨዋታ ጊዜ የምናገኘው ከስንት አንዴ ነበር። በቤተሰባችን ውስጥ እያንዳንዱ ልጅ ሰባት ዓመት ሲሆነው ወደ እርሻ ሄዶ መሥራት ይጀምራል፤ ይህም አቀበታማ በሆነው የተራራ መንገድ ላይ ከባድ ኮኮናቶችን ተሸክሞ መጓዝን ያካትታል። ሸክሙ በጣም ከባድ ሲሆንብን እየጎተትን ለመውሰድ እንገደዳለን።

 አባታችን ይደበድበን ነበር፤ የበለጠ ያሳዝነን የነበረው ግን እናታችንን ሲመታት መመልከት ነበር። እሷን ከጥቃት ለመከላከል ጥረት ብናደርግም አቅማችን ውስን ነበር። እንዲያውም እኔና ሮዲሊዮ ስናድግ አባታችንን ለመግደል በሚስጥር ተስማምተን ነበር። አፍቃሪ አባት እንዲኖረን በጣም እመኝ ነበር!

 አባቴ የሚፈጽመው ድርጊት ተስፋ ስላስቆረጠኝና ስላናደደኝ በ14 ዓመቴ ከቤት ወጣሁ። ከዚያ በኋላ ጎዳና ላይ ለተወሰነ ጊዜ በኖርኩበት ወቅት ማሪዋና ማጨስ ጀመርኩ። ብዙም ሳይቆይ ጀልባ ነጂ ሆኜ ጎብኚዎችን ወደ ፏፏቴዎቹ በመውሰድ እተዳደር ጀመር።

 ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ፣ በማኒላ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን መከታተል ጀመርኩ። ሆኖም ቅዳሜና እሁድ ሥራ ለመሥራት ወደ ፓግሳንሃን እሄድ ስለነበር ለጥናት የሚሆን ጊዜ አጣሁ። ሕይወት አስቸጋሪና ምንም ትርጉም የሌለው ሆኖ ተሰማኝ፤ ማሪዋና ማጨሴም ቢሆን ጭንቀቴን አልቀነሰልኝም። በመሆኑም ሜታምፌታሚን፣ ኮኬይንና ሄሮይን የሚባሉትን ዕፆች መውሰድ ጀመርኩ። ዕፆችን መውሰድ ደግሞ ብዙውን ጊዜ የፆታ ብልግና ወደመፈጸም ይመራል። የምኖረው ድህነትና መከራ ባለበት እንዲሁም ኢፍትሐዊ ድርጊት በተንሰራፋበት አካባቢ ነበር። ለእነዚህ ችግሮች ተጠያቂው መንግሥት እንደሆነ ስለተሰማኝ ለመንግሥት ጥላቻ አድሮብኝ ነበር። አምላክን “ሕይወት እንደዚህ በችግር የተሞላው ለምንድን ነው?” በማለት እጠይቀው ነበር፤ ለጥያቄዎቼ መልስ ለማግኘት የተለያዩ ሃይማኖቶችን ብመረምርም ጥረቴ ውጤት አላስገኘም። የሚሰማኝን የተስፋ መቁረጥ ስሜት ለመቋቋም ከበፊቱ የበለጠ ዕፅ መውሰድ ጀመርኩ።

 በ1972 በፊሊፒንስ ያሉ ተማሪዎች በመንግሥት ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ለመግለጽ ተደራጅተው ነበር። እኔም በአንደኛው ተቃውሞ ውስጥ የተካፈልኩ ሲሆን ተቃውሞውም ወደ ዓመፅ ተለወጠ። በርካታ ሰዎች ታሰሩ፤ ከወራት በኋላ ደግሞ አገሪቱ በወታደራዊ ሕግ መተዳደር ጀመረች።

 በዓመፁ ስለተካፈልኩ የመንግሥት ባለሥልጣናቱ እንዳይዙኝ እፈራ ነበር፤ በዚህም ምክንያት ዳግም ጎዳና ላይ ወደቅኩ። የዕፅ ሱሴን ለማርካት መስረቅ ውሎ አድሮም በዝሙት አዳሪነት ተሰማርቼ ከሀብታሞችና ከውጭ አገር ከመጡ ሰዎች ጋር የፆታ ብልግና መፈጸም ጀመርኩ። በሕይወት ብኖርም ብሞትም ግድ አልነበረኝም።

 በዚህ መሃል፣ እናቴና ታናሽ ወንድሜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምረው ነበር። አባቴ ይህ በጣም ስላናደደው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻቸውን አቃጠለባቸው። ሆኖም እነሱ በአቋማቸው በመጽናት ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ።

 አንድ ቀን አንድ የይሖዋ ምሥክር፣ እውነተኛ ፍትሕ በመላው ምድር እንደሚሰፍን የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ለአባቴ ነገረው። (መዝሙር 72:12-14) አባቴ በዚህ ተስፋ ልቡ ስለተማረከ ስለ ጉዳዩ የበለጠ ለመመርመር ወሰነ። መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠና አምላክ ፍትሐዊ መንግሥት እንደሚመሠርት የሰጠውን ተስፋ ብቻ ሳይሆን ከባሎችና ከአባቶች ምን እንደሚጠብቅም ተማረ። (ኤፌሶን 5:28፤ 6:4) ከዚያ ብዙም ሳይቆይ እሱም ሆነ ወንድሞቼና እህቶቼ በሙሉ የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ። እኔ የምኖረው ከቤት ርቄ በመሆኑ ይህንን ሁሉ አልሰማሁም ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን የለወጠው እንዴት ነው?

 በ1978 ወደ አውስትራሊያ ተዛወርኩ። ሰላማዊና ባለጸጋ በሆነች አገር ውስጥ ብኖርም ውስጣዊ ሰላም ማግኘት ግን አልቻልኩም። የአልኮል መጠጥ መጠጣቴንም ሆነ ዕፅ መውሰዴን ቀጠልኩ። በዚያ ዓመት መጨረሻ አካባቢ የይሖዋ ምሥክሮች አነጋገሩኝ። ሰላም ስለሚሰፍንባት ምድር ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያሳዩኝ ነገር ቢያስደስተኝም ስላላመንኳቸው ከእነሱ ጋር ለማጥናት አልፈለግኩም።

 ከይሖዋ ምሥክሮቹ ጋር ከተገናኘን ብዙም ሳይቆይ ለጥቂት ሳምንታት ወደ ፊሊፒንስ ተመለስኩ። ወንድሞቼና እህቶቼ፣ አባታችን የተሻለ ሰው ለመሆን ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንዳለ ነገሩኝ፤ እኔ ግን በጣም ተመርሬበት ስለነበረ ከእሱ ጋር ላለመገናኘት እጥር ነበር።

 ሕይወት በመከራና ኢፍትሐዊ በሆኑ ድርጊቶች የተሞላው ለምን እንደሆነ ታናሽ እህቴ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አስረዳችኝ። ስለ ሕይወት ያን ያህል ተሞክሮ የሌላት በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ልጅ ለጥያቄዎቼ መልስ መስጠቷ አስገረመኝ። ወደ አውስትራሊያ ከመመለሴ በፊት ደግሞ አባቴ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ ሰጠኝ። a ከዚያም “በተሳሳተ መንገድ ለጥያቄዎችህ መልስ ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት አቁም። ይህ መጽሐፍ ስትፈልገው የነበረውን ነገር እንድታገኝ ይረዳሃል” አለኝ። ወደ አውስትራሊያ ስመለስ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንድገናኝም መከረኝ።

 አባቴ የሰጠኝን ምክር በመከተል በብሪዝበን ባለው መኖሪያ ቤቴ አቅራቢያ ወደሚገኝ የይሖዋ ምሥክሮች የስብሰባ አዳራሽ ሄድኩ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመርም ተስማማሁ። በዳንኤል ምዕራፍ 7 እና በኢሳይያስ ምዕራፍ 9 ላይ እንዳሉት ካሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች፣ ወደፊት የሚገዛን የአምላክ መንግሥት ከምግባረ ብልሹነት ሙሉ በሙሉ የጸዳ እንደሆነ ማስተዋል ቻልኩ። በተጨማሪም ገነት በምትሆነው ምድር ላይ እንደምንኖር ተማርኩ። በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት እፈልግ ነበር፤ ሆኖም ስሜቴን መቆጣጠር፣ ዕፅ መውሰዴንና አልኮል ከመጠን በላይ መጠጣቴን ማቆም እንዲሁም ልቅ የሆነ አኗኗሬን መተው እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። ስለዚህ አብሬያት እኖር ከነበረች ሴት ጋር ተለያየሁ፤ እንዲሁም ሱሶቼን አስወገድኩ። በይሖዋ ላይ ያለኝ እምነት እያደገ ሲሄድ ደግሞ ሌሎች ለውጦችን ለማድረግ እንዲረዳኝ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ።

 ከመጽሐፍ ቅዱስ እየተማርኩ ያለሁት ነገር አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ማድረግ እንዲችል እንደሚረዳው ውሎ አድሮ ተገነዘብኩ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጥረት የምናደርግ ከሆነ “አዲሱን ስብዕና” መልበስ እንደምንችል ይገልጻል። (ቆላስይስ 3:9, 10) እኔም እንዲህ ያለ ጥረት ሳደርግ፣ አባቴ ባሕርይው እንደተለወጠ የሰማሁት ነገር እውነት ሊሆን እንደሚችል ተረዳሁ። በእሱ ከመናደድና እሱን ከመጥላት ይልቅ ከእሱ ጋር ሰላም ለመፍጠር ተመኘሁ። በመጨረሻም አባቴን ይቅር ማለትና ከልጅነቴ አንስቶ ለእሱ የነበረኝን ጥላቻ ማስወገድ ቻልኩ።

ያገኘሁት ጥቅም

 ወጣት ሳለሁ፣ ጎጂ እና አስቸጋሪ ባሕርይ ካላቸው ሰዎች ጋር እሆን ስለነበር እንደ እነሱ ዓይነት አካሄድ እከተል ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ መጥፎ ባልንጀርነት ወደ ተሳሳተ ጎዳና እንደሚመራ የሚናገረው ሐሳብ እውነት መሆኑን በራሴ ሕይወት አይቻለሁ። (1 ቆሮንቶስ 15:33) እምነት ከሚጣልባቸው የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ወዳጅነት መመሥረቴ ግን የተሻልኩ ሰው እንድሆን ረድቶኛል። ሎሬታ የተባለች ግሩም ሚስትም ማግኘት ችያለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ ስላለው ጥቅም ከባለቤቴ ጋር ሆነን ለሌሎች እናስተምራለን።

ከባለቤቴና ከጓደኞቼ ጋር ስንመገብ

 አባቴ መጽሐፍ ቅዱስን በመማሩ፣ ያደርገዋል ብዬ ጨርሶ አስቤ የማላውቀውን ለውጥ ማድረግ ችሏል፤ አባቴ አፍቃሪ ባል ብሎም ትሑት እና ሰላም ወዳድ ክርስቲያን ሆኗል። በ1987 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ከሆንኩ በኋላ ስንገናኝ አባቴ በሕይወቴ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አቀፈኝ።

 አባቴ ከእናቴ ጋር በመሆን ላለፉት ከ35 የሚበልጡ ዓመታት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ተስፋ ለሰዎች ሲሰብክ ቆይቷል። አባቴ ተግቶ በመሥራት፣ ለሌሎች አሳቢነት በማሳየትና ሌሎችን በመርዳት ረገድ ጥሩ ስም ማትረፍ ችሏል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ፣ ለአባቴ ያለኝ አክብሮትና ፍቅር እየጨመረ ሄደ። አሁን ልጁ በመሆኔ ኩራት ይሰማኛል! አባቴ በ2016 ሕይወቱ ቢያልፍም ሁለታችንም የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች ተግባራዊ በማድረግ በሕይወታችን ውስጥ ትላልቅ ለውጦች ማድረግ እንደቻልን ስለማውቅ ስለ እሱ ጥሩ ትዝታ አለኝ። በውስጤ የነበረውን ጥላቻ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ችያለሁ። በተጨማሪም በሰማይ የሚኖረውን አባቴን ይሖዋ አምላክን ማወቅ በመቻሌ በጣም አመስጋኝ ነኝ፤ እሱ በየትኛውም ቤተሰብ ውስጥ ላሉ ችግሮች መንስኤ የሚሆኑ ነገሮችን ሁሉ እንደሚያስወግድ ቃል ገብቷል።

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ፤ አሁን መታተም አቁሟል።