በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች ፀረ ክትባት ናቸው?

የይሖዋ ምሥክሮች ፀረ ክትባት ናቸው?

 አይደሉም። የይሖዋ ምሥክሮች ፀረ ክትባት አቋም የላቸውም። መከተብ ወይም አለመከተብ ለእያንዳንዱ ክርስቲያን የተተወ የግል ውሳኔ እንደሆነ እናምናለን። ብዙዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች መከተብ ይመርጣሉ።

 ጥሩ ሕክምና ማግኘት እንፈልጋለን፤ በተጨማሪም የሕክምናው ሳይንስ በከባድ በሽታ የመጠቃት አጋጣሚን ለመቀነስ የሚያደርጋቸውን የተለያዩ ጥረቶች እናደንቃለን። የሕክምና ባለሙያዎች፣ በተለይ ከባድ ቀውስ በሚፈጠርበት ወቅት ሌሎችን ለማገልገል ለሚያሳዩት ትጋትና ለሚከፍሉት መሥዋዕትነት በጣም አመስጋኞች ነን።

 የይሖዋ ምሥክሮች ከጤና ጥበቃ ባለሥልጣናት ጋር ይተባበራሉ። የይሖዋ ምሥክሮች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ በዚህ ድረ ገጽ ላይ በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች ያወጧቸውን ማሳሰቢያዎች እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል፤ ሰዎች በየአካባቢያቸው የሚሰጣቸውን የደህንነት መመሪያ እንዲከተሉ ሲያበረታቱ ቆይተዋል። ለምሳሌ አካላዊ ርቀትን መጠበቅን፣ መሰባሰብን፣ ከሌሎች ተገልሎ መቆየትን፣ እጅ መታጠብን፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግንና ሌሎች ነገሮችን በተመለከተ ባለሥልጣናት የሚያወጧቸውን ደንቦች መከተል ያለውን አስፈላጊነት በተደጋጋሚ ገልጸዋል።—ሮም 13:1, 2

 የይሖዋ ምሥክሮች የሚያወጧቸው ጽሑፎች፣ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት የሚከተሉትን መርሆዎች ሲያራምዱ ቆይተዋል፦

  •   ከሕክምና ጋር የተያያዙ ጉዳዮች የግል ውሳኔዎች ናቸው።—ገላትያ 6:5

     “[ይህ መጽሔት] ይሄኛው መድኃኒት ወይም የሕክምና ዓይነት ከዚያኛው የተሻለ ነው የሚል ዓይነት አስተያየት አይሰጥም፤ አንባቢዎች አንድን ዓይነት ሕክምና እንዲከታተሉ የሚያበረታታ ሐሳብም አያቀርብም። ዓላማው፣ ያለውን መረጃ ማስቀመጥ ብቻ ነው፤ በዚያ ላይ ተመሥርቶ ውሳኔ ማድረግ የአንባቢው ኃላፊነት ነው።”—ንቁ! የካቲት 8, 1987 (እንግሊዝኛ)

     “‘እኔም ሆንኩ ልጆቼ ብንከተብ ይሻላል ወይስ አይሻልም?’ የሚለው ጥያቄ ለእናንተ የተተወ ውሳኔ ነው።”—ንቁ! ነሐሴ 22, 1965 (እንግሊዝኛ)

  •   ለሕይወት ትልቅ ቦታ ስለምንሰጥ ጥሩ ሕክምና ለማግኘት ጥረት እናደርጋለን።—የሐዋርያት ሥራ 17:28

     “የይሖዋ ምሥክሮች፣ ላሉባቸው የጤና እክሎች መፍትሔ ለማግኘት የጤና ባለሙያዎችን ያማክራሉ። ለሕይወት ትልቅ ዋጋ ስለሚሰጡ ምክንያታዊና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚስማማ እስከሆነ ድረስ ሕይወትን ለማስቀጠል የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ።”—መጠበቂያ ግንብ፣ ሐምሌ 1, 1975 (እንግሊዝኛ)

     “የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰጣቸውን መድኃኒትም ሆነ የሕክምና እርዳታ በደስታ ይቀበላሉ። በተጨማሪም ጥሩ ጤንነት እንዲሁም ረጅም ዕድሜ እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ። እንዲያውም በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረው እንደ ሉቃስ አንዳንዶቹ ሐኪሞች ናቸው። . . . የይሖዋ ምሥክሮች የሕክምና እርዳታ የሚሰጡ ባለሙያዎች በትጋትና በሙሉ ልብ ለሚያከናውኑት ሥራ ከፍተኛ አድናቆት አላቸው። በተጨማሪም እነዚህ ባለሙያዎች ለታመሙ ሰዎች ለሚሰጡት እፎይታ አመስጋኞች ናቸው።”—መጠበቂያ ግንብ፣ የካቲት 1, 2011