በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች ልጆቻቸው የእነሱን ሃይማኖት እንዲከተሉ ያስገድዳሉ?

የይሖዋ ምሥክሮች ልጆቻቸው የእነሱን ሃይማኖት እንዲከተሉ ያስገድዳሉ?

 አያስገድዱም፤ ምክንያቱም አምልኮ የግል ውሳኔ ነው። (ሮም 14:12) የይሖዋ ምሥክሮች ለልጆቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ያስተምሯቸዋል፤ ሆኖም ልጆቹ ሲያድጉ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ወይም ላለመሆን መምረጥ ይኖርባቸዋል።—ሮም 12:2፤ ገላትያ 6:5

 እንደ ማንኛውም ወላጅ ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮችም ልጆቻቸው ጥሩ ሕይወት እንዲመሩ ይፈልጋሉ። በመሆኑም ለልጆቻቸው ይጠቅማል ብለው የሚያስቡትን ነገር በሙሉ ያስተምሯቸዋል፤ ከእነዚህም መካከል ጠቃሚ ክህሎቶች፣ የሥነ ምግባር እሴቶችና ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ይገኙበታል። የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉ የተሻለውን ሕይወት እንድንመራ እንደሚረዳን ያምናሉ፤ ስለዚህ ለልጆቻቸው መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማር እንዲሁም አብረው ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት የመጽሐፍ ቅዱስን ምክሮች በልጆቻቸው ልብ ውስጥ ለመቅረጽ ጥረት ያደርጋሉ። (ዘዳግም 6:6, 7) ከዚያም እያንዳንዱ ልጅ እያደገ ሲሄድ የወላጆቹን እምነት ለመከተል ወይም ላለመከተል የራሱን ውሳኔ ማድረግ ይችላል።

 የይሖዋ ምሥክሮች ጨቅላ ሕፃናትን ያጠምቃሉ?

 በፍጹም። መጽሐፍ ቅዱስ የጨቅላ ሕፃናትን ጥምቀት አይደግፍም። ለምሳሌ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች የተጠመቁት የአምላክን ቃል ሰምተው ‘በደስታ ከተቀበሉና’ ንስሐ ከገቡ በኋላ እንደሆነ ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 2:14, 22, 38, 41) ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው አንድ ሰው ከመጠመቁ በፊት የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት መረዳት፣ ማመንና በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች መሠረት ሕይወቱን ለመምራት መወሰን ይኖርበታል። ጨቅላ ሕፃናት ደግሞ እንዲህ ማድረግ እንደማይችሉ ግልጽ ነው።

 ልጆች ካደጉ በኋላ ለመጠመቅ ሊወስኑ ይችላሉ። ሆኖም ይህን ለማድረግ ስለ ውሳኔያቸው ክብደት አስቀድመው ሊያስቡበት ይገባል።

 የይሖዋ ምሥክሮች ልጆቻቸው ላለመጠመቅ ከወሰኑ ያገልሏቸዋል?

 አያገልሏቸውም። የይሖዋ ምሥክር ወላጆች ልጆቻቸው እምነታቸውን ላለመቀበል ሲወስኑ ያዝናሉ፤ ሆኖም ልጆቻቸውን ይወዷቸዋል እንዲሁም የይሖዋ ምሥክር ላለመሆን ስለወሰኑ ብቻ ከልጆቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት አያቋርጡም።

በየትኛውም ዕድሜ ላይ የሚገኝ ሰው ከጥምቀት ጋር በተያያዘ የራሱን ውሳኔ የማድረግ ኃላፊነት አለበት

 የይሖዋ ምሥክሮች ሲሰብኩ ልጆቻቸውን ይዘው የሚሄዱት ለምንድን ነው?

 ከልጆቻችን ጋር አብረን ለመስበክ የሚያነሳሱን የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። a

  •   ወላጆች ለልጆቻቸው መንፈሳዊ ትምህርት መስጠትና አምላክን እንዲያመልኩ ማሠልጠን እንዳለባቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኤፌሶን 6:4) አምልኮ እምነትን በይፋ መናገርን ስለሚጨምር ለልጆች የሚሰጠው መንፈሳዊ ሥልጠና ስብከትንም ያካትታል።—ሮም 10:9, 10፤ ዕብራውያን 13:15

  •   መጽሐፍ ቅዱስ ልጆች የአምላክን ‘ስም እንዲያወድሱ’ ያበረታታል። (መዝሙር 148:12, 13) አምላክን ማወደስ የሚቻልበት ዋነኛ መንገድ ደግሞ ስለ እሱ ለሌሎች መናገር ነው። b

  •   ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር መስበካቸው ሌሎች ጥቅሞችም ያስገኝላቸዋል። ለምሳሌ ከተለያዩ ሰዎች ጋር የመግባባት ችሎታን እንዲሁም እንደ ርኅራኄ፣ ደግነት፣ አክብሮት እና የሌሎችን ጥቅም ማስቀደም ያሉ መልካም ባሕርያትን ለማዳበር ይረዳቸዋል። በተጨማሪም ለእምነታቸው መሠረት የሆኑትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎች በደንብ ለማወቅ ያስችላቸዋል።

 የይሖዋ ምሥክሮች በዓላትን ያከብራሉ?

 የይሖዋ ምሥክሮች በሃይማኖታዊ በዓላት እንዲሁም አምላክን በሚያሳዝኑ ሌሎች ዝግጅቶች አይካፈሉም። c (2 ቆሮንቶስ 6:14-17፤ ኤፌሶን 5:10) ለምሳሌ እንደ ልደትና ገና ያሉትን በዓላት አናከብርም፤ ምክንያቱም የእነዚህ በዓላት ምንጭ ክርስቲያናዊ አይደለም።

 ያም ቢሆን ከቤተሰቦቻችን ጋር ጊዜ ማሳለፍና ለልጆቻችን ስጦታ መስጠት ያስደስተናል። ከቤተሰብ ጋር ለመገናኘትና ስጦታ ለመለዋወጥ የበዓል ቀን ከመጠበቅ ይልቅ በዓመት ውስጥ በተለያዩ ወቅቶች ከወዳጆቻችን ጋር ጊዜ እናሳልፋለን እንዲሁም ስጦታ እንለዋወጣለን።

ክርስቲያን ወላጆች ለልጆቻቸው ስጦታ መስጠት ያስደስታቸዋል

a በጥቅሉ ሲታይ ትናንሽ ልጆች ለስብከት የሚሄዱት ከወላጆቻቸው ወይም ከሌላ ትልቅ ሰው ጋር ብቻ ነው።

b መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እምነታቸው ለሰዎች በመናገር አምላክን ያስደሰቱ ልጆችን ታሪክ ይዟል።—2 ነገሥት 5:1-3፤ ማቴዎስ 21:15, 16፤ ሉቃስ 2:42, 46, 47

c “የይሖዋ ምሥክሮች በዓላትን የማያከብሩት ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

d አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።