በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች ከዚህ ቀደም “አልፈልግም” ያሉ ሰዎችን ድጋሚ የሚያነጋግሩት ለምንድን ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች ከዚህ ቀደም “አልፈልግም” ያሉ ሰዎችን ድጋሚ የሚያነጋግሩት ለምንድን ነው?

 የይሖዋ ምሥክሮች ቀደም ሲል “አልፈልግም” ያሉ ሰዎችን ጨምሮ ለሁሉም ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ማካፈል ያስደስታቸዋል፤ ይህን እንዲያደርጉ የሚያነሳሳቸው ለአምላክና ለሰዎች ያላቸው ፍቅር ነው። (ማቴዎስ 22:37-39) ለአምላክ ያለን ፍቅር፣ ኢየሱስ “በተሟላ ሁኔታ እንድንመሠክር” የሰጠንን ትእዛዝ እንድናከብር ያነሳሳናል። (የሐዋርያት ሥራ 10:42፤ 1 ዮሐንስ 5:3) ይህን ለማድረግ ደግሞ የጥንቶቹ የአምላክ ነቢያት እንዳደረጉት ሁሉ እኛም የአምላክን መልእክት በተደጋጋሚ ለሰዎች እንናገራለን። (ኤርምያስ 25:4) ለሰዎች ፍቅር ስላለን፣ በመጀመሪያ ፍላጎት ያልነበራቸውን ጨምሮ ለሁሉም ሰው ሕይወት አድን የሆነውን ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ ለማዳረስ ጥረት እናደርጋለን።—ማቴዎስ 24:14

 አንዳንድ ጊዜ ቀደም ሲል ፍላጎት ያሳየ ሰው ወዳልነበረባቸው ቤቶች ተመልሰን ስንሄድ ፍላጎት ያለው ሰው እናገኛለን። ለዚህ ምክንያት የሚሆኑ ሦስት ነገሮችን እንመልከት፦

  •   ሰዎች ቤት ይቀይራሉ።

  •   በቤቱ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ሰዎች መልእክታችንን የመስማት ፍላጎት ይኖራቸዋል።

  •   የሰዎች ሁኔታ ይለወጣል። በዓለም ላይ የሚከሰቱ ነገሮች ወይም በግል ሕይወታቸው ውስጥ የተፈጠሩ ሁኔታዎች ሰዎች ‘መንፈሳዊ ነገሮችን እንዲጠሙና’ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት የመስማት ፍላጎት እንዲያድርባቸው ያደርጋሉ። (ማቴዎስ 5:3) ተቃዋሚ የነበሩ ሰዎች እንኳ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ አመለካከታቸው ሊለወጥ ይችላል።—1 ጢሞቴዎስ 1:13

 ሆኖም ማንም ሰው መልእክታችንን እንዲሰማ አናስገድድም። (1 ጴጥሮስ 3:15) ከአምልኮ ጋር በተያያዘ እያንዳንዱ ሰው የራሱን ውሳኔ ማድረግ እንዳለበት እናምናለን።—ዘዳግም 30:19, 20