በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎች ሃይማኖታቸውን እንዲለውጡ ያስገድዳሉ?

የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎች ሃይማኖታቸውን እንዲለውጡ ያስገድዳሉ?

 በፍጹም፤ እንዲህ አናደርግም። ለምሳሌ፣ በዋነኝነት በምንጠቀምበት መጠበቂያ ግንብ በተባለው መጽሔት ላይ “ሰዎች ሃይማኖታቸውን እንዲለውጡ ማስገደድ ትክክል አይደለም” የሚል ሐሳብ ወጥቶ ነበር። a ሰዎች ሃይማኖታቸውን እንዲለውጡ የማናስገድደው በሚከተሉት ምክንያቶች የተነሳ ነው፦

  •   ኢየሱስ፣ ሰዎች የሚያስተምረውን ትምህርት እንዲቀበሉ በፍጹም አላስገደደም። ብዙ ሰዎች ለሚሰብከው መልእክት ጥሩ ምላሽ እንደማይሰጡ ያውቅ ነበር። (ማቴዎስ 7:13, 14) ከደቀ መዛሙርቱ መካከል አንዳንዶቹ በተናገረው ነገር ተሰናክለው ትተውት በሄዱ ጊዜ እንዲከተሉት ከማስገደድ ይልቅ ውሳኔያቸውን አክብሯል።—ዮሐንስ 6:60-62, 66-68

  •   ኢየሱስ በሰዎች ላይ ጫና አሳድረው እምነታቸውን እንዲያስለውጡ ተከታዮቹን አላስተማረም። ደቀ መዛሙርቱ የመንግሥቱን ምሥራች እንዲቀበሉ ሰዎችን ለማስገደድ ከመሞከር ይልቅ ለመስማት ፈቃደኛ የሆኑትን እንዲፈልጉ አስተምሯቸዋል።—ማቴዎስ 10:7, 11-14

  •   አምላክ፣ ሰዎች በሙሉ ልባቸው እንዲያመልኩት ይፈልጋል፤ በመሆኑም ሰዎች ሃይማኖታቸውን እንዲለውጡ ለማስገደድ መሞከር ዋጋ የለውም።—ዘዳግም 6:4, 5፤ ማቴዎስ 22:37, 38

የምንሰብከው የሰዎችን ሃይማኖት ለማስለወጥ ነው?

 እርግጥ ነው፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት “እስከ ምድር ዳር ድረስ” እንሰብካለን፤ ይህን የምናደርገው ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያዘው “በአደባባይና ከቤት ወደ ቤት” እየሄድን ነው። (የሐዋርያት ሥራ 1:8፤ 10:42፤ 20:20) ልክ እንደ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም አንዳንድ ጊዜ ሕግን በመጣስ የሰዎችን ሃይማኖት ያስለውጣሉ የሚል ክስ ይሰነዘርብናል። (የሐዋርያት ሥራ 18:12, 13) ሆኖም ይህ ክስ ሐሰት ነው። እምነታችንን እንዲቀበል ማንንም ሰው አንጫንም። ከዚህ ይልቅ ሰዎች እውቀት መቅሰምና በዚያ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ማድረግ እንዳለባቸው እናምናለን።

 ሰዎች ሃይማኖታቸውን እንዲለውጡ አናስገድድም፤ እንዲሁም በሃይማኖት ሽፋን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን አናደርግም። አሊያም አዳዲስ የእምነቱ ተከታዮች ለማፍራት ስንል ለሰዎች ቁሳዊ ነገሮችን ወይም ማኅበራዊ ጥቅማ ጥቅሞችን አንሰጥም። ይህ ደግሞ ክርስቲያን ነን እያሉ እንዲህ ያሉ ድርጊቶችን በመፈጸም ክርስቶስን ከሚያዋርዱ ሰዎች የተለየን እንድንሆን አድርጎናል። b

አንድ ሰው ሃይማኖቱን የመቀየር መብት አለው?

ነቢዩ አብርሃም የዘመዶቹን ሃይማኖት መከተል ትቷል

 አዎ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ሃይማኖታቸውን የመለወጥ መብት እንዳላቸው ይጠቁማል። የመምረጥ ነፃነታቸውን ተጠቅመው ቤተሰቦቻቸው የሚከተሉትን ሃይማኖታዊ ሥርዓት ለመፈጸም ፈቃደኛ ያልሆኑና እውነተኛውን አምላክ ለማምለክ የወሰኑ ብዙ ሰዎችን ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እናገኛለን። አብርሃምሩት፣ አንዳንድ የአቴንስ ሰዎችና ሐዋርያው ጳውሎስ ጥቂቶቹ ናቸው። (ኢያሱ 24:2፤ ሩት 1:14-16፤ የሐዋርያት ሥራ 17:22, 30-34፤ ገላትያ 1:14, 23) በተጨማሪም የጥበብ እርምጃ ባይሆንም አንድ ሰው አምላክ የሚቀበለውን አምልኮ የመተው መብት እንኳ እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል።—1 ዮሐንስ 2:19

 አንድ ሰው ሃይማኖቱን የመለወጥ መብት እንዳለው በዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ላይ ሰፍሯል፤ ይህን ድንጋጌ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት “ለዓለም አቀፋዊው የሰብዓዊ መብቶች ሕግ መሠረት” በማለት ገልጾታል። ድንጋጌው እያንዳንዱ ሰው “ሃይማኖቱን ወይም እምነቱን የመቀየር ነፃነት” እንዲሁም ሃይማኖታዊ የሆኑትን ጨምሮ ማንኛውንም “መረጃና ሐሳብ የመመርመር፣ የመቀበልና የማካፈል” መብት እንዳለው ይገልጻል። c እርግጥ ነው፣ እያንዳንዱ ሰው እነዚህ መብቶች ያሉት ቢሆንም ሌሎች ሰዎች የፈለጉትን እምነት የመያዝና የማይስማሙበትን ሐሳብ ያለመቀበል መብት እንዳላቸው የመገንዘብና ይህን መብታቸውን የማክበር ግዴታም አለበት።

አንድ ሰው ሃይማኖቱን መቀየሩ ቤተሰቡን ወይም ባሕሉን እንዳያከብር ያደርገዋል?

 አያደርገውም። መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች የሚከተሉት ሃይማኖት ምንም ሆነ ምን፣ ሁሉንም እንድናከብር ያበረታታናል። (1 ጴጥሮስ 2:17) በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች ወላጆቻቸው የተለየ እምነት ቢኖራቸው እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ወላጆቻችሁን አክብሩ’ በማለት የሚሰጠውን ምክር ይታዘዛሉ።—ኤፌሶን 6:2, 3

 ይሁንና ከመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ጋር የሚስማሙት ሁሉም ሰዎች አይደሉም። በዛምቢያ ያደገች አንዲት ሴት “እኔ በምኖርበት አካባቢ ሃይማኖትን መለወጥ . . . ቤተሰብንና ኅብረተሰቡን እንደ መካድ ተደርጎ ይቆጠራል” ብላለች። ይህች ሴት በአሥራዎቹ ዕድሜ እያለች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት በመጀመሯና ከዚያም ሃይማኖቷን ለመለወጥ በመወሰኗ ብዙ ችግሮች አጋጥመዋታል። እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ በጣም እንዳዘኑብኝና እንዳሳፈርኳቸው በተደጋጋሚ ይነግሩኝ ነበር። ወላጆቼ ውሳኔዬን እንዲቀበሉልኝ እፈልግ ስለነበር እነርሱን ማሳዘኔ በጣም ከበደኝ። . . . ከሃይማኖታዊ ልማድ ይልቅ ለይሖዋ ታማኝ መሆኔ ቤተሰቦቼን እንደካድኳቸው የሚያሳይ አይደለም።” d

a የጥር 1, 2002 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 12 አንቀጽ 15ን ተመልከት።

b ለምሳሌ ያህል፣ በ785 ዓ.ም. ገደማ ሻርለማኝ ለመጠመቅና ክርስቲያን ለመሆን ፈቃደኛ ባልሆኑ በሳክሶኒ በሚገኙ ሰዎች ላይ የሞት ቅጣት የሚበይን አዋጅ አውጥቶ ነበር። በተጨማሪም በ1555 ዓ.ም. በቅዱሷ የሮማ ግዛት በሚገኙ የጦር አንጃዎች መካከል የተፈረመው የኦግስበርግ የሰላም ስምምነት አገረ ገዢዎች የሮማ ካቶሊክ ወይም የሉተራን አማኝ እንዲሆኑ እንዲሁም እያንዳንዱ ሰው የገዢውን ሃይማኖት እንዲከተል የሚደነግግ ሕግ ነበረው። የገዢዎቻቸውን ሃይማኖት ለመከተል ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ይደረግ ነበር።

c ተመሳሳይ የሆኑ ሰብዓዊ መብቶች በሚከተሉት ድንጋጌዎች ውስጥም ተካተዋል፦ የአፍሪካ የሰብዓዊ እና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር፣ የአሜሪካ የሰብዓዊ መብቶችና ግዴታዎች ድንጋጌ፣ በ2004 የተደነገገው የአረብ አገራት የሰብዓዊ መብቶች ቻርተር፣ የኤ ኤስ ኢ ኤ ኤን (የደቡባዊ ምሥራቅ እስያ አገራት ማኅበር) የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ፣ የአውሮፓ አገራት የሰብዓዊ መብቶች ስምምነት እና ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት። ይሁንና እነዚህን መብቶች ለዜጎቻቸው እንደሚሰጡ የሚናገሩ አንዳንድ አገራት እንኳ የእነዚህን መብቶች ተግባራዊነት የሚያስፈጽሙበት ሁኔታ ይለያያል።

d መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የእውነተኛው አምላክ የግል ስም ይሖዋ ነው።