በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች ብሔራዊ ስሜት በሚንጸባረቅባቸው ሥነ ሥርዓቶች የማይካፈሉት ለምንድን ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች ብሔራዊ ስሜት በሚንጸባረቅባቸው ሥነ ሥርዓቶች የማይካፈሉት ለምንድን ነው?

 የይሖዋ ምሥክሮች መንግሥታትንም ሆነ የሚጠቀሙባቸውን ብሔራዊ አርማዎች ያከብራሉ። ሰዎች ለአገራቸው የታማኝነት ቃለ መሐላ የመግባት፣ ለባንዲራ ሰላምታ የመስጠት ወይም ብሔራዊ መዝሙር የመዘመር መብት እንዳላቸው እንቀበላለን።

 ይሁንና የይሖዋ ምሥክሮች በእነዚህ ብሔራዊ ሥነ ሥርዓቶች አንካፈልም፤ ምክንያቱም ይህን ማድረግ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ጋር እንደሚጋጭ እናምናለን። በዚህ ረገድ እኛ የሌሎችን አመለካከት እንደምናከብር ሁሉ ሌሎችም ለምናምንበት ነገር አክብሮት ሲያሳዩን ደስ ይለናል።

በዚህ ርዕስ ውስጥ

 ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች የትኞቹ ናቸው?

 ውሳኔ ለማድረግ የረዱን ሁለት ቁልፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ከዚህ በታች ቀርበዋል፦

  •   ሊመለክ የሚገባው አምላክ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ” ይላል። (ሉቃስ 4:8) ብዙውን ጊዜ በታማኝነት ቃለ መሐላዎችና በብሔራዊ መዝሙሮች ላይ ሰዎች ከምንም ነገር በላይ ለአገራቸው ቅድሚያ ለመስጠት ቃል እንደሚገቡ የሚገልጽ ሐሳብ ይካተታል። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች በእነዚህ ሥነ ሥርዓቶች ለመካፈል ሕሊናቸው አይፈቅድላቸውም።

     የይሖዋ ምሥክሮች ለባንዲራ ሰላምታ መስጠትም ከአምልኮ ተለይቶ እንደማይታይ ይሰማቸዋል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ጣዖት አምልኮን ያወግዛል። (1 ቆሮንቶስ 10:14) አንዳንድ የታሪክ ምሁራን፣ ብሔራዊ ባንዲራዎች እንደ ሃይማኖታዊ ምልክት ተደርገው ሊቆጠሩ እንደሚችሉ ገልጸዋል። የታሪክ ምሁር የሆኑት ካርልተን ሄይዝ “የብሔራዊ ስሜት ዋነኛ የእምነት ምልክትና የአምልኮ መሣሪያ ባንዲራ ነው” ሲሉ ጽፈዋል። a ዳንኤል ማኒክስ የተባሉት ደራሲ ደግሞ የጥንት ክርስቲያኖችን በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፦ “ክርስቲያኖች [ለሮም] ንጉሠ ነገሥት ውቃቤ መሥዋዕት ለማቅረብ . . . ፈጽሞ ፈቃደኞች አልነበሩም። ይህም ዛሬ ለባንዲራ ሰላምታ ለመስጠት ፈቃደኛ ካለመሆን ጋር የሚመሳሰል ነው።” b

    የይሖዋ ምሥክሮች ለባንዲራ ሰላምታ ባንሰጥም ባንዲራን አናበላሽም ወይም አናቃጥልም፤ አሊያም ደግሞ ባንዲራንም ሆነ ሌላ ማንኛውንም ብሔራዊ አርማ የሚያቃልል ድርጊት አንፈጽምም።

  •   ሁሉም ሰዎች በአምላክ ፊት እኩል ናቸው። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ “የሰውን ወገኖች በሙሉ ከአንድ ሰው ፈጠረ” ይላል። (የሐዋርያት ሥራ 17:26) በዚህም የተነሳ የይሖዋ ምሥክሮች አንድን ዘር ወይም አገር ከሌሎች አስበልጦ ከፍ ማድረግ ስህተት እንደሆነ ያምናሉ። አገራቸውም ሆነ የሚኖሩበት ቦታ የትም ይሁን የት ሁሉንም ሰዎች እናከብራለን።—1 ጴጥሮስ 2:17

 በብሔራዊ ሥነ ሥርዓቶች መካፈልን ሕጉ የሚያስገድድ ቢሆንስ?

 የይሖዋ ምሥክሮች ፀረ መንግሥት አይደሉም። መንግሥታት ‘አምላክ ያደረገው ዝግጅት’ ክፍል እንደሆኑ በሌላ አባባል ሥልጣን ላይ እንዲቆዩ የፈቀደላቸው እሱ እንደሆነ እንቀበላለን። (ሮም 13:1-7) በተጨማሪም ክርስቲያኖች ለመንግሥት ባለሥልጣናት ሊገዙ እንደሚገባ እናምናለን።—ሉቃስ 20:25

 ይሁንና መንግሥታት ያወጧቸው ሕጎች ከአምላክ ሕጎች ጋር በሚጋጩበት ጊዜስ? በሕጉ ላይ ማስተካከያ እንዲደረግ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ጥያቄ ማቅረብ የሚቻልበት ጊዜ አለ። c ይህን ማድረግ የማይቻል ከሆነ ግን የይሖዋ ምሥክሮች ‘ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያቸው አድርገው እንደሚታዘዙ’ በአክብሮት ይገልጻሉ።—የሐዋርያት ሥራ 5:29

 የይሖዋ ምሥክሮች ማኅበራዊ ወይም ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት እየሞከሩ ነው?

 አይደለም። የይሖዋ ምሥክሮች በማኅበራዊም ሆነ በፖለቲካዊ ጉዳዮች የትኛውንም ወገን አይደግፉም። ለአንድ አገር የታማኝነት ቃለ መሐላ የማንገባው፣ ለባንዲራ ሰላምታ የማንሰጠው ወይም ብሔራዊ መዝሙር የማንዘምረው የፖለቲካ ለውጥ አራማጆች ስለሆንን አይደለም። እነዚህን ነገሮች የማናደርገው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረተ እምነታችን የተነሳ ነው።

a ኤሴይስ ኦን ናሽናሊዝም ከገጽ 107-108

b ዘ ዌይ ኦቭ ግላዲዬተርስ ገጽ 212