በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ይቅር የማይባል ኃጢአት አለ?

ይቅር የማይባል ኃጢአት አለ?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ይቅር የማይባል ኃጢአት፣ አንድ ኃጢአተኛ የአምላክን ምሕረት ፈጽሞ እንዳያገኝ የሚያደርገውን ድርጊትና ዝንባሌ የሚያመለክት ነው። አንድ ሰው እንዲህ ያለ ሁኔታ የሚያጋጥመው እንዴት ነው?

 አምላክ ከኃጢአታቸው ንስሐ የሚገቡ፣ በሕይወታቸው የእሱን መመሪያ የሚከተሉ እንዲሁም በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎችን ይቅር ይላል። (የሐዋርያት ሥራ 3:19, 20) ያም ሆኖ አንድ ሰው ዝንባሌውንም ሆነ ምግባሩን መቀየር እስኪያቅተው ድረስ በኃጢአት ሊዘፈቅ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነቱን ሰው ‘ኃጢአት ባለው የማታለል ኃይል የደነደነ ክፉ ልብ ያለው’ በማለት ይገልጸዋል። (ዕብራውያን 3:12, 13) አንድ ሸክላ፣ በእሳት ከተጠበሰ በኋላ ቅርጹን መቀየር እንደማይቻል ሁሉ እንዲህ ያለው ሰው ልብም ምንጊዜም የአምላክ ተቃዋሚ ሆኗል። (ኢሳይያስ 45:9) በመሆኑም ይህን ሰው ይቅር ለማለት የሚያስችል ምንም መሠረት አይኖርም፤ በመሆኑም ይህ ሰው ኃጢአቱ ይቅር አይባልም ወይም ምሕረት አያገኝም።—ዕብራውያን 10:26, 27

 በኢየሱስ ዘመን የነበሩ አንዳንድ የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ይቅር የማይባል ኃጢአት ፈጽመዋል። ኢየሱስ ተአምር የሚፈጽመው በአምላክ መንፈስ አማካኝነት እንደሆነ ቢያውቁም ሆን ብለው ‘ኃይሉን ያገኘው ከሰይጣን ዲያብሎስ ነው’ በማለት ተናግረዋል።—ማርቆስ 3:22, 28-30

ይቅር የሚባሉ ኃጢአቶች

  •  ባለማወቅ አምላክን መሳደብ። ሐዋርያው ጳውሎስ በአንድ ወቅት አምላክን ይሳደብ ነበር፤ ሆኖም “ባለማወቅና ባለማመን ስላደረግኩት፣ ምሕረት ተደርጎልኛል” በማለት ከጊዜ በኋላ ተናግሯል።—1 ጢሞቴዎስ 1:13

  •  ምንዝር። መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ወቅት ምንዝር የፈጸሙ ሆኖም ምግባራቸውን ስላስተካከሉና የአምላክን ይቅርታ ስላገኙ ሰዎች ይጠቅሳል።—1 ቆሮንቶስ 6:9-11

“ይቅር የማይባል ኃጢአት ፈጽሜ ይሆን?”

 ከዚህ በፊት በፈጸምከው ኃጢአት ከልብ ከተጸጸትክና እውነተኛ ለውጥ ማድረግ የምትፈልግ ከሆነ የፈጸምከው፣ ይቅር የማይባል ኃጢአት አይደለም። አምላክ እሱን በመቃወም ልብህን እስከ መጨረሻው እስካላደነደንክ ድረስ አንድን ኃጢአት የፈጸምከው በተደጋጋሚ ቢሆን እንኳ ይቅር ይልሃል።—ኢሳይያስ 1:18

 አንዳንዶች ከፍተኛ የጥፋተኝነት ስሜት ስለሚሰማቸው ‘ይቅር የማይባል ኃጢአት ሠርቻለሁ’ ብለው ያስባሉ። ያም ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ ስሜታችንን ትክክል የማይሆንበት ጊዜ እንዳለ ይናገራል። (ኤርምያስ 17:9) አምላክ በማንም ላይ የመፍረድ ሥልጣን አልሰጠንም፤ ይህ ደግሞ በራሳችን ላይ መፍረድንም ይጨምራል። (ሮም 14:4, 12) ልባችን እየወቀሰን እንኳ እሱ ይቅር ሊለን ይችላል።—1 ዮሐንስ 3:19, 20

የአስቆሮቱ ይሁዳ ይቅር የማይባል ኃጢአት ፈጽሟል?

 አዎ፣ ይሁዳ የፈጸመው ይቅር የማይባል ኃጢአት ነው። በስግብግብነት ተነሳስቶ ለቅዱስ ዓላማ የተዋጣውን ገንዘብ ሰርቋል። የሚሰርቀው ብዙ ገንዘብ ለማግኘት ሲል ለድሆች ተቆርቋሪ መስሎ ቀርቧል። (ዮሐንስ 12:4-8) የይሁዳ ልብ በክፋት ድርጊት ውስጥ ስለተዘፈቀ ለ30 የብር ሳንቲሞች ሲል ኢየሱስን አሳልፎ ሰጠው። ኢየሱስ፣ ይሁዳ ለፈጸመው ኃጢአት መቼም ቢሆን እውነተኛ ንስሐ እንደማይገባ ስለሚያውቅ ‘የጥፋት ልጅ’ በማለት ጠርቶታል። (ዮሐንስ 17:12) በመሆኑም ይሁዳ ለዘላለም ጠፍቷል ማለትም ማለትም የትንሣኤ ተስፋ የለውም።—ማርቆስ 14:21

 ይሁዳ ለሠራው ኃጢአት እውነተኛ ንስሐ አልገባም። ኃጢአቱን የተናዘዘው እንኳ ለአምላክ ሳይሆን ከእሱ ጋር አብረው ለተመሳጠሩት የሃይማኖት መሪዎች ነበር።—ማቴዎስ 27:3-5፤ 2 ቆሮንቶስ 7:10