በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስ ባነብ የሚያጽናናኝ ሐሳብ አገኝ ይሆን?

መጽሐፍ ቅዱስ ባነብ የሚያጽናናኝ ሐሳብ አገኝ ይሆን?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 አዎ፣ ታገኛለህ። (ሮም 15:4) አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የገቡ ወይም ሐዘንና ጭንቀት የደረሰባቸው ብዙ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ መጽናኛ አግኝተዋል፤ እስቲ ያጽናኗቸውን አንዳንድ ጥቅሶች እንመልከት።

በዚህ ርዕስ ውስጥ

 መከራ

 መዝሙር 23:4 “ድቅድቅ ጨለማ በዋጠው ሸለቆ ውስጥ ብሄድ እንኳ አንተ ከእኔ ጋር ስለሆንክ፣ ጉዳት ይደርስብኛል ብዬ አልፈራም።”

 ምን ማለት ነው? ወደ አምላክ የምትጸልይና ምክር ለማግኘት ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን የምታነብ ከሆነ በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥምህን ማንኛውንም መከራ በድፍረት መወጣት ትችላለህ።

 ፊልጵስዩስ 4:13፦ “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ።”

 ምን ማለት ነው? አምላክ ማንኛውንም ችግር ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት ሊሰጥህ ይችላል።

 የቤተሰብ ወይም የወዳጅ ሞት

 መክብብ 9:10 “በመቃብር ሥራም ሆነ ዕቅድ፣ እውቀትም ሆነ ጥበብ የለም።”

 ምን ማለት ነው? የሞቱ ሰዎች እየተሠቃዩ አይደሉም፤ ሊጎዱንም አይችሉም። ምንም የሚያውቁት ነገር የለም።

 የሐዋርያት ሥራ 24:15 ‘ሰዎች ከሞት ይነሳሉ።’

 ምን ማለት ነው? አምላክ በሞት ያጣናቸውን ሰዎች ሊያስነሳቸው ይችላል።

 ከልክ ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት

 መዝሙር 86:5 “ይሖዋ a ሆይ፣ አንተ ጥሩ ነህና፤ ይቅር ለማለትም ዝግጁ ነህ፤ አንተን ለሚጠሩ ሁሉ የምታሳየው ታማኝ ፍቅር ወሰን የለውም።”

 ምን ማለት ነው? አምላክ በስህተታቸው ከልብ የተጸጸቱና ያንን ላለመድገም የቆረጡ ሰዎችን ይቅር ይላል።

 መዝሙር 103:12 “ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ በደላችንን ከእኛ አራቀ።”

 ምን ማለት ነው? አምላክ ይቅር ሲለን ኃጢአታችንን ልናስበው ከምንችለው በላይ ከእኛ ያርቀዋል። ኃጢአታችንን አሁንም አሁንም እያነሳ አይወቅሰንም ወይም አይቀጣንም።

 ሐዘን

 መዝሙር 31:7 “ጉስቁልናዬን አይተሃልና፤ በጭንቀት መዋጤን ታውቃለህ።”

 ምን ማለት ነው? አምላክ የሚሰማህን ሥቃይ በሚገባ ያውቃል። ሌሎች በማይረዱህ ጊዜም እንኳ የውስጥ ስሜትህን ይረዳልሃል።

 መዝሙር 34:18 “ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተደቆሰባቸውንም ያድናል።”

 ምን ማለት ነው? አምላክ በሐዘን በምትዋጥበት ጊዜ እንደሚደግፍህ ቃል ገብቷል። ሐዘንህን ለመቋቋም የሚያስችልህ ብርታት ሊሰጥህ ይችላል።

 ሕመም

 መዝሙር 41:3 “ታሞ በአልጋ ላይ ተኝቶ ሳለ ይሖዋ ይደግፈዋል።”

 ምን ማለት ነው? ከባድ የጤና እክል ሲያጋጥምህ አምላክ ይደግፍሃል፤ ይህን የሚያደርገው ውስጣዊ ሰላም፣ ጥንካሬ፣ ጽናትና ጥሩ ውሳኔዎች ለማድረግ የሚያስችል ጥበብ በመስጠት ነው።

 ኢሳይያስ 33:24 “በዚያም የሚቀመጥ ማንኛውም ሰው ‘ታምሜአለሁ’ አይልም።”

 ምን ማለት ነው? አምላክ ሁሉም ሰው ጤነኛ የሚሆንበት ጊዜ እንደሚመጣ ቃል ገብቷል።

 ውጥረትና ጭንቀት

 መዝሙር 94:19 “በጭንቀት በተዋጥኩ ጊዜ፣ አጽናናኸኝ፤ ደግሞም አረጋጋኸኝ።”

 ምን ማለት ነው? በጭንቀት በምንዋጥበት ጊዜ የአምላክን እርዳታ ለማግኘት ከሞከርን እንድንረጋጋ ይረዳናል።

 1 ጴጥሮስ 5:7 “የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ በእሱ ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል።”

 ምን ማለት ነው? አምላክ የሚደርስብን ሥቃይ ግድ ይሰጠዋል። ስለሚያስጨንቁን ነገሮች ወደ እሱ እንድንጸልይ ጋብዞናል።

 ጦርነት

 መዝሙር 46:9 “ጦርነትን ከመላው ምድር ላይ ያስወግዳል።”

 ምን ማለት ነው? የአምላክ መንግሥት በቅርቡ ጦርነትን ሙሉ በሙሉ ያስቀራል።

 መዝሙር 37:11, 29 “የዋሆች . . . ምድርን ይወርሳሉ፤ በብዙ ሰላምም እጅግ ደስ ይላቸዋል። . . . ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ።”

 ምን ማለት ነው? ጥሩ ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም በሰላም ይኖራሉ።

 ስለ ወደፊቱ ጊዜ መጨነቅ

 ኤርምያስ 29:11 “‘ለእናንተ የማስበውን ሐሳብ በሚገባ አውቀዋለሁና’ ይላል ይሖዋ፤ ‘ለእናንተ የማስበው ጥፋትን ሳይሆን ሰላምን እንዲሁም የተሻለ ሕይወትንና ተስፋን ነው።’”

 ምን ማለት ነው? አምላክ እሱን የሚያመልኩ ሰዎች የወደፊቱን ጊዜ በተስፋ መጠበቅ እንደሚችሉ ዋስትና ሰጥቷቸዋል።

 ራእይ 21:4 “እሱም እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”

 ምን ማለት ነው? አምላክ በዛሬው ጊዜ በአንተም ሆነ በሌሎች ሰዎች ላይ የሚደርሱትን መጥፎ ነገሮች በሙሉ ለማስወገድ ቃል ገብቷል።

a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።