በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

አምላክ ይቅር ይለኝ ይሆን?

አምላክ ይቅር ይለኝ ይሆን?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 አዎ፣ አስፈላጊውን ነገር እስካደረግክ ድረስ አምላክ ኃጢአትህን ይቅር ይልሃል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ “ይቅር ለማለት ዝግጁ” መሆኑንና “ይቅርታው ብዙ” እንደሆነ ይናገራል። (ነህምያ 9:17፤ መዝሙር 86:5፤ ኢሳይያስ 55:7) አምላክ ይቅር የሚለን ሙሉ በሙሉ ነው። በመሆኑም ኃጢአታችን ‘ይደመሰሳል’ ወይም ይወገዳል። (የሐዋርያት ሥራ 3:19) ከዚህ በተጨማሪ አምላክ፣ ‘ኃጢአታቸውን ከእንግዲህ አላስታውስም’ በማለት ስለተናገረ ይቅር የሚለን ለዘለቄታው ነው። (ኤርምያስ 31:34) ኃጢአታችንን ይቅር ካለን በኋላ እንደ አዲስ እያነሳ አይከሰንም ወይም አይቀጣንም።

 ይሁን እንጂ አምላክ ኃጢአታችንን ይቅር የሚለው መጨከን ስለማይችል ወይም ስሜታዊ ስለሆነ አይደለም። የጽድቅ መሥፈርቶቹን በፍጹም አያላላም። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ኃጢአቶችን ይቅር አይልም።—ኢያሱ 24:19, 20

የአምላክን ይቅርታ ለማግኘት የሚረዱ እርምጃዎች

  1. ኃጢአት መሥራትህ የአምላክን መሥፈርት መጣስ መሆኑን አምነህ ተቀበል። ባደረግከው ነገር የተጎዱ ሰዎች ሊኖሩ ቢችሉም ከማንም በላይ ግን የበደልከው አምላክን እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብሃል።—መዝሙር 51:1, 4፤ የሐዋርያት ሥራ 24:16

  2. ኃጢአትህን በጸሎት ለአምላክ ተናዘዝ።—መዝሙር 32:5፤ 1 ዮሐንስ 1:9

  3. በሠራኸው ኃጢአት ከልብህ ማዘን ይኖርብሃል። እንዲህ ያለው ‘ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ’ ሐዘን ንስሐ ወደ መግባት ማለትም ልብን ወደ መለወጥ ይመራል። (2 ቆሮንቶስ 7:10) ይህ ደግሞ ኃጢአቱን ወደ መፈጸም በመሩህ የተሳሳቱ እርምጃዎች መጸጸትን ይጨምራል።—ማቴዎስ 5:27, 28

  4. አካሄድህን ቀይር ወይም ‘ተመለስ።’ (የሐዋርያት ሥራ 3:19) ይህም አንድን መጥፎ ድርጊት ወይም ልማድ ከመድገም መቆጠብ አሊያም አስተሳሰብህንና ድርጊትህን በአጠቃላይ መለወጥ ሊጠይቅብህ ይችላል።—ኤፌሶን 4:23, 24

  5. የሠራኸውን ጥፋት ለማረም ወይም ያደረግከው ነገር ያስከተለውን ጉዳት ለማስተካከል እርምጃ ውሰድ። (ማቴዎስ 5:23, 24፤ 2 ቆሮንቶስ 7:11) ባደረግከው ወይም ሳታደርግ በቀረኸው ነገር የተነሳ የተጎዱ ሰዎችን ይቅርታ ጠይቅ፤ እንዲሁም በተቻለህ መጠን ጉዳቱን ለማካካስ ጥረት አድርግ።—ሉቃስ 19:7-10

  6. በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት መሠረት አምላክ ኃጢአትህን ይቅር እንዲልህ ልመና አቅርብ። (ኤፌሶን 1:7) ጸሎትህ መልስ እንዲያገኝ ደግሞ አንተም የበደሉህን ይቅር ማለት አለብህ።—ማቴዎስ 6:14, 15

  7. የሠራኸው ኃጢአት ከባድ ከሆነ፣ መንፈሳዊ እርዳታ ለመስጠት ብቃት ላለውና ሊጸልይልህ ለሚችል ሰው ተናገር።—ያዕቆብ 5:14-16

የአምላክን ይቅርታ ከማግኘት ጋር በተያያዘ ሰዎች ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት

 “ብዙ ኃጢአት ስለሠራሁ አምላክ ይቅር ሊለኝ አይችልም።”

ዳዊት ምንዝር የፈጸመና ነፍስ ያጠፋ ቢሆንም አምላክ ይቅር ብሎታል

 አምላክ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሰፈራቸውን እርምጃዎች እስከወሰድን ድረስ ኃጢአታችንን ይቅር ይለናል፤ ምክንያቱም የአምላክ ይቅርታ ከፈጸምናቸው ኃጢአቶች በላይ ነው። አምላክ የተሠራው ኃጢአት ከባድ ወይም በተደጋጋሚ የተፈጸመ ቢሆንም ሁሉንም ይቅር ይላል።—ኢሳይያስ 1:18

 ለምሳሌ ያህል፣ የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት ምንዝር የፈጸመና ነፍስ ያጠፋ ቢሆንም ይቅር ተብሏል። (2 ሳሙኤል 12:7-13) ከማንኛውም ሰው በላይ ኃጢአተኛ እንደሆነ የተሰማው ሐዋርያው ጳውሎስም ይቅርታ ተደርጎለታል። (1 ጢሞቴዎስ 1:15, 16) በመጀመሪያው መቶ ዘመን፣ መሲሕ የሆነውን ኢየሱስን በመግደላቸው በአምላክ ዘንድ ተጠያቂ የነበሩት አይሁዳውያን እንኳ አካሄዳቸውን ከቀየሩ ይቅርታ ማግኘት ይችሉ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 3:15, 19

 “ለቄስ ወይም ለቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ኃጢአቴን ከተናዘዝኩ ይቅር እባላለሁ።”

 በአሁኑ ጊዜ፣ አንድ ሰው በአምላክ ላይ የፈጸመውን ኃጢአት ይቅር የማለት ሥልጣን የተሰጠው ማንም ሰው የለም። አንድ ሰው የሠራውን ኃጢአት ለሌላ ሰው መናዘዙ እንዲፈወስ ሊረዳው ቢችልም ኃጢአትን ይቅር ማለት የሚችለው ግን አምላክ ብቻ ነው።—ኤፌሶን 4:32፤ 1 ዮሐንስ 1:7, 9

 ታዲያ ኢየሱስ ሐዋርያቱን “የማንንም ሰው ኃጢአት ይቅር ብትሉ ኃጢአቱ ይቅር ይባላል፤ ይቅር የማትሉት ሰው ሁሉ ደግሞ ኃጢአቱ እንዳለ ይጸናል” ሲል ምን ማለቱ ነበር? (ዮሐንስ 20:23) ኢየሱስ ሐዋርያቱ መንፈስ ቅዱስን በሚቀበሉበት ወቅት ከእሱ ስለሚያገኙት በዓይነቱ ልዩ የሆነ ሥልጣን መግለጹ ነበር።—ዮሐንስ 20:22

 እነዚህ ሐዋርያት በ33 ዓ.ም. መንፈስ ቅዱስ በፈሰሰበት ወቅት ኢየሱስ ቃል በገባው መሠረት ይህን ስጦታ ተቀብለዋል። (የሐዋርያት ሥራ 2:1-4) ሐዋርያው ጴጥሮስ በዚህ ሥልጣን ተጠቅሞ ሐናንያና ሰጲራ በሚባሉት ደቀ መዛሙርት ላይ ፍርድ አስተላልፏል። ጴጥሮስ አታላዮች መሆናቸው በተአምር የተገለጠለት ሲሆን የሰጠው ፍርድ ደግሞ ኃጢአታቸው ይቅር እንደማይባል ይጠቁማል።—የሐዋርያት ሥራ 5:1-11

 ይህ ተአምራዊ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ፈውስንና በልሳን መናገርን እንደመሳሰሉ ሌሎች ስጦታዎች ሁሉ ከሐዋርያት ሞት በኋላ ቀርቷል። (1 ቆሮንቶስ 13:8-10) በመሆኑም በዛሬው ጊዜ ማንም ሰው ሌላውን ከኃጢአት ነፃ ሊያደርግ አይችልም።