በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

አምላክ ሐሳቡን ይለውጣል?

አምላክ ሐሳቡን ይለውጣል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 አዎ፣ የሚለውጥበት ጊዜ አለ፤ ይህ የሚሆነው ሰዎች ባሕርያቸውን ሲቀይሩ እሱም ለእነሱ ያለው አመለካከት ስለሚለወጥ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ በጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ ላይ የፍርድ መልእክት ባስተላለፈበት ወቅት እንዲህ ብሏል፦ “ምናልባትም ሰምተው እያንዳንዳቸው ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ይሆናል፤ እኔም ስላደረጉት ክፋት ላመጣባቸው ያሰብሁትን ቅጣት እተዋለሁ።”ኤርምያስ 26:3

 ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ጥቅስ ያስቀመጡት አምላክ፣ በሕዝቡ ላይ ጥፋት ለማምጣት በማሰቡ እንደተቆጨ አድርገው ነው፤ ይህ ዓይነቱ አተረጓጎም ደግሞ አምላክን ስህተት የሠራ ያስመስለዋል። በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው የዕብራይስጥ ቃል “የሐሳብ ወይም የዓላማ ለውጥ ማድረግ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። አንድ ምሁር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ሰዎች አካሄዳቸውን መቀየራቸው አምላክ ለእነሱ በሚሰጠው ፍርድ ላይ ለውጥ ያመጣል።”

 እርግጥ ነው፣ አምላክ ሐሳቡን ሊለውጥ ይችላል ሲባል ሐሳቡን የግዴታ መቀየር አለበት ማለት አይደለም። አምላክ ሐሳቡን ያልቀየረባቸው ጊዜያት እንዳሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፤ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው፦

  •   ባላቅ፣ የእስራኤልን ሕዝብ እንዲረግምለት አምላክን በጠየቀው ወቅት አምላክ ሐሳቡን አልለወጠም።—ዘኍልቍ 23:18-20

  •   ንጉሥ ሳኦል ክፉ ነገር ማድረጉን በቀጠለ ጊዜ አምላክ እሱን ከንግሥና ለማውረድ የነበረውን ሐሳብ አልለወጠም።—1 ሳሙኤል 15:28, 29

  •   አምላክ፣ ልጁን ለዘላለም ካህን አድርጎ ለመሾም የገባውን ቃል ይፈጽማል። ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አምላክ ሐሳቡን አይለውጥም።—መዝሙር 110:4

ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ እንደማይለወጥ የሚናገረው ለምንድን ነው?

 መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም” ብሎ እንደተናገረ ይገልጻል። (ሚልክያስ 3:6) በተጨማሪም አምላክ “ቦታውን እንደሚቀያይር ጥላ አይለዋወጥም” ይላል። (ያዕቆብ 1:17) ይሁንና ይህ ሐሳብ አምላክ ሐሳቡን የለወጠበት ጊዜ እንዳለ ከሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ጋር አይጋጭም። አምላክ አይለወጥም የምንለው ማንነቱ እንዲሁም የፍቅር እና የፍትሕ መሥፈርቶቹ ምንጊዜም አንድ ዓይነት ስለሆኑ ነው። (ዘዳግም 32:4፤ 1 ዮሐንስ 4:8) ያም ቢሆን በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ መመሪያዎችን ለሰዎች ሊሰጥ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ለንጉሥ ዳዊት በሁለት የተለያዩ ውጊያዎች ላይ ተቃራኒ የሚመስሉ ሁለት መመሪያዎችን ሰጥቶት ነበር፤ ይሁንና ሁለቱም መመሪያዎች ዳዊትን ለድል አብቅተውታል።—2 ሳሙኤል 5:18-25

አምላክ የሰው ልጆችን በመፍጠሩ ያዝናል?

 አምላክ አብዛኞቹ ሰዎች እሱን በመተዋቸው ወይም በእሱ ላይ በማመፃቸው ምክንያት የተጸጸተበት ጊዜ ቢኖርም የሰው ልጆችን በመፍጠሩ አያዝንም። በኖኅ ዘመን ከደረሰው የጥፋት ውኃ በፊት የነበረውን ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ ሲገልጽ “እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፤ ልቡም እጅግ አዘነ” በማለት ይናገራል። (ዘፍጥረት 6:6) በዚህ ጥቅስ ላይ “ተጸጸተ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ሐሳብን መለወጥ” የሚል ፍቺም ሊኖረው ይችላል። ከጥፋት ወኃው በፊት የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች ክፉዎች በመሆናቸው አምላክ እነሱን በተመለከተ የሐሳብ ለውጥ አድርጓል። (ዘፍጥረት 6:5, 11) ሆኖም አምላክ፣ እነዚህ ሰዎች መጥፎ አካሄድ በመከተላቸው ቢያዝንም ለሰው ልጆች በአጠቃላይ ያለው አመለካከት አልተለወጠም። እንዲያውም የሰው ዘር በጥፋት ውኃው ሙሉ በሙሉ እንዳይጠፋ ሲል ኖኅን እና ቤተሰቡን ታድጓል።—ዘፍጥረት 8:21፤ 2 ጴጥሮስ 2:5, 9