በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ምን ባሕርያት አሉት?

አምላክ ምን ባሕርያት አሉት?

የአንድን ሰው ባሕርያት ይበልጥ ባወቅን መጠን ከዚያ ሰው ጋር ያለን ወዳጅነትም የዚያኑ ያህል ይጠናከራል። በተመሳሳይም የይሖዋን ባሕርያት ይበልጥ እያወቅን ስንሄድ እሱ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ስለምንገነዘብ በመካከላችን ያለው ወዳጅነት እየጠነከረ ይሄዳል። አምላክ የተለያዩ ግሩም ባሕርያት ያሉት ሲሆን ከእነዚህ መካከል አራቱ ጎላ ብለው ይታያሉ። እነሱም ኃይል፣ ጥበብ፣ ፍትሕና ፍቅር ናቸው።

አምላክ ኃያል ነው

“አቤቱ፣ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ! እነሆ፣ አንተ ሰማያትንና ምድርን በታላቅ ኃይልህ . . . ሠርተሃል።”ኤርምያስ 32:17

የአምላክ ኃይል በፍጥረት ሥራዎቹ ላይ በግልጽ ይታያል። ለምሳሌ ያህል፣ በበጋ ወቅት ከቤት ውጭ ስትሆን ምን ይሰማሃል? ከፀሐይ የሚመነጨው ሙቀት ቆዳህ ላይ ሲያርፍ እንደሚሰማህ የታወቀ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ይህ ሙቀት ይሖዋ ለመፍጠር የተጠቀመበት ኃይል ውጤት ነው። ለመሆኑ ፀሐይ ምን ያህል ኃይል አላት? የፀሐይ እምብርት 15,000,000 ዲግሪ ሴልሸስ ገደማ የሚደርስ ሙቀት እንዳለው ይነገራል። ፀሐይ በእያንዳንዱ ሴኮንድ ከብዙ መቶ ሚሊዮን የኑክሌር ቦምብ ፍንዳታ ጋር የሚመጣጠን ኃይል ታመነጫለች።

ያም ሆኖ ፀሐይ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ካሉት በትሪሊዮን የሚቆጠሩ ከዋክብት ጋር ስትነጻጸር ከአብዛኞቹ በመጠን ታንሳለች። ሳይንቲስቶች ትላልቅ ከሆኑት ከዋክብት መካከል አንዱ የሆነው ዊ ስኩቲ የተባለው ኮከብ በስፋት ከፀሐይ 1,700 እጥፍ እንደሚበልጥ ይገምታሉ። ይህ ኮከብ አሁን ፀሐይ ያለችበት ቦታ ላይ ቢቀመጥ ስፋቱ ምድርን ሸፍኖ ጁፒተር ከተባለው ፕላኔት ምሕዋር አልፎ ይሄዳል። ይህን ማወቃችን ኤርምያስ፣ ይሖዋ አምላክ ሰማያትንና ምድርን ማለትም ጽንፈ ዓለምን በታላቅ ኃይሉ እንደሠራ የተናገረውን ሐሳብ ይበልጥ ለመረዳት ያስችለናል።

አምላክ ከፍተኛ ኃይል ያለው መሆኑ ምን ጥቅም ያስገኝልናል? ሕልውናችን የተመካው አምላክ በፈጠራቸው ግዑዛን ፍጥረታት ላይ ነው፤ ለምሳሌ ፀሐይ ወይም በምድር ላይ ያሉት የተፈጥሮ ሀብቶች ከሌሉ የሰው ልጆች በሕይወት ሊቀጥሉ አይችሉም። በተጨማሪም አምላክ ኃይሉን ተጠቅሞ የሰው ልጆችን በግለሰብ ደረጃ የሚጠቅም ነገር ያደርጋል። እንዴት? በመጀመሪያው መቶ ዘመን አምላክ ለኢየሱስ ኃይል በመስጠት ተአምራት እንዲፈጽም አስችሎታል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ዓይነ ስውሮች እያዩ ነው፤ አንካሶች እየተራመዱ ነው፤ የሥጋ ደዌ የያዛቸው እየነጹ ነው፤ መስማት የተሳናቸው እየሰሙ ነው፤ ሙታን እየተነሱ ነው።” (ማቴዎስ 11:5) በዛሬው ጊዜስ? መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ‘ለደከመው ኃይል እንደሚሰጥ’ እንዲሁም ‘ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉ ኃይላቸው እንደሚታደስ’ ይናገራል። (ኢሳይያስ 40:29, 31) አምላክ በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥመንን ችግርና መከራ መቋቋም እንድንችል ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል’ ይሰጠናል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) ታዲያ ገደብ የለሽ ኃይሉን በፍቅር ተነሳስቶ እኛን ለመርዳት ወደሚጠቀምበት እንዲህ ወዳለው አምላክ ለመቅረብ አትገፋፋም?

አምላክ ጥበበኛ ነው

“ይሖዋ ሆይ፣ ሥራህ ምንኛ ብዙ ነው! ሁሉንም በጥበብ ሠራህ።”መዝሙር 104:24

አምላክ ስለሠራቸው ነገሮች እያወቅን በሄድን መጠን በጥበቡ ይበልጥ እንደመማለን። እንዲያውም ሳይንቲስቶች የይሖዋን ፍጥረታት በመመርመርና በእነዚህ ፍጥረታት ላይ የሚታየውን ንድፍ በመኮረጅ ከዚህ በፊት የሠሯቸውን ነገሮች ንድፍ ለማሻሻል ጥረት የሚያደርጉበት ባዮሚሜቲክስ ወይም ባዮሚሚክሪ የሚባል የጥናት መስክ አለ። ሳይንቲስቶች ቀላል ከሆነው ማጣበቂያ አንስቶ ውስብስብ እስከሆነው አውሮፕላን ንድፍ ድረስ ተፈጥሮን ኮርጀዋል።

የሰው ዓይን ድንቅ የፍጥረት ሥራ ነው

ሆኖም የሰውን አካል ያህል የአምላክን ጥበብ የሚያሳይ ፍጥረት የለም ማለት ይቻላል። አንድ ሽል በእናቱ ማህፀን ውስጥ የሚያድግበትን መንገድ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ሂደቱ የሚጀምረው በአንድ የዳበረ ሴል ሲሆን ይህ ሴል አስፈላጊውን ጄኔቲካዊ መመሪያ በሙሉ ይዟል። ይህ ሴል እየተከፋፈለ በርካታ ተመሳሳይ ሴሎችን ያስገኛል። ሆኖም ልክ በትክክለኛው ጊዜ ላይ እነዚህ ሴሎች ዓይነታቸው መለያየት ይጀምራል፤ ይህ ሂደት በመቶዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ ሴሎችን ለምሳሌ የደም ሴሎችን፣ የነርቭ ሴሎችን እንዲሁም የአጥንት ሴሎችን ያስገኛል። ብዙም ሳይቆይ ከእነዚህ ሴሎች የተሠሩት የአካል ክፍሎች ተቀናጅተው መሥራት ይጀምራሉ። በዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ መጀመሪያ ላይ የነበረው አንድ ሴል አድጎ በብዙ ቢሊዮኖች በሚቆጠሩ ሴሎች የተገነባና ሙሉ አካል ያለው ሕፃን ይሆናል። በርካታ ሰዎች እንዲህ ባለው ንድፍ ላይ የተንጸባረቀውን ጥበብ ሲመለከቱ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ እንዳለው “በሚያስደምም ሁኔታ ግሩምና ድንቅ ሆኜ ስለተፈጠርኩ አወድስሃለሁ” ለማለት ይገፋፋሉ።—መዝሙር 139:14

አምላክ ጥበበኛ መሆኑ ምን ጥቅም ያስገኝልናል? ፈጣሪያችን ደስተኞች ለመሆን ምን እንደሚያስፈልገን ያውቃል። ወሰን የለሽ እውቀትና ማስተዋል ስላለው በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ጥበብ ያዘለ ምክር ሊሰጠን ይችላል። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ “እርስ በርስ . . . በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ” የሚል ምክር ይዟል። (ቆላስይስ 3:13) ይህ ምክር በእርግጥ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ነው? አዎ። ተመራማሪዎች እንዳረጋገጡት ይቅር ባይነት ጥሩ እንቅልፍ ለመተኛትና የደም ግፊትን ለመቀነስ ይረዳል። በተጨማሪም ለመንፈስ ጭንቀትና ለሌሎች የጤና ችግሮች የመጋለጥ አጋጣሚን ሊቀንስ ይችላል። አምላክ ምንጊዜም ጠቃሚ ምክር እንደሚሰጥ አሳቢና ጥበበኛ ጓደኛ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ታዲያ እንዲህ ዓይነት ጓደኛ እንዲኖርህ አትፈልግም?

አምላክ ፍትሐዊ ነው

“ይሖዋ ፍትሕን ይወዳል።”መዝሙር 37:28

አምላክ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ምንጊዜም ትክክል ነው። እንዲያውም “‘እውነተኛው አምላክ ክፉ ነገር ያደርጋል፤ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በደል ይፈጽማል’ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው!” (ኢዮብ 34:10) የይሖዋ ፍርዶች ሁሌም ትክክል ናቸው፤ መዝሙራዊው ይሖዋን አስመልክቶ ሲናገር “በሕዝቦች ላይ በትክክል ትፈርዳለህ” ብሏል። (መዝሙር 67:4) ይሖዋ “የሚያየው ልብን” ስለሆነ በሰዎች ግብዝነት ሊታለል አይችልም፤ ምንጊዜም ቢሆን እውነቱን ማወቅና ትክክለኛ ፍርድ መስጠት ይችላል። (1 ሳሙኤል 16:7) ከዚህም በላይ አምላክ በምድር ላይ የሚፈጸመውን የፍትሕ መጓደልና ምግባረ ብልሹነት በሙሉ ጠንቅቆ የሚያውቅ ከመሆኑም ሌላ በቅርቡ ‘ክፉዎች ከምድር ገጽ እንደሚጠፉ’ ቃል ገብቷል።—ምሳሌ 2:22

ይሁን እንጂ አምላክ ጥፋታችንን አንድ በአንድ ተከታትሎ የሚቀጣ ጨካኝ ዳኛ አይደለም። ተገቢ በሆነ ጊዜ ሁሉ ምሕረት ያሳያል። ይሖዋ ከልብ ንስሐ እስከገቡ ድረስ ለክፉዎችም እንኳ “መሐሪና ሩኅሩኅ” እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ታዲያ እውነተኛ ፍትሕ ማለት ይህ አይደል?—መዝሙር 103:8፤ 2 ጴጥሮስ 3:9

አምላክ ፍትሐዊ መሆኑ ምን ጥቅም ያስገኝልናል? ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ እንደማያዳላ በእርግጥ አስተዋልኩ፤ ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።” (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) አምላክ ፍትሐዊና የማያዳላ መሆኑ በብዙ መንገድ ይጠቅመናል። ዘራችን፣ ዜግነታችን፣ የትምህርት ደረጃችን ወይም በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለን ቦታ ምንም ይሁን ምን በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘትና የእሱ አገልጋዮች መሆን እንችላለን።

አምላክ አያዳላም፤ ዘራችን ወይም የኑሮ ደረጃችን ምንም ይሁን ምን ከእሱ ፍትሕ ተጠቃሚ መሆን እንችላለን

አምላክ የእሱን ፍትሕ እንድንረዳና በዚያ መሠረት እንድንመራ ስለሚፈልግ ሕሊና ሰጥቶናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ሕሊና ምግባራችን ትክክል ወይም ስህተት መሆኑን ‘የሚመሠክር በልባችን የተጻፈ’ ሕግ ነው። (ሮም 2:15) ሕሊና የሚጠቅመን እንዴት ነው? ሕሊናችን በአግባቡ ከሠለጠነ ጎጂ ወይም ኢፍትሐዊ ከሆኑ ድርጊቶች እንድንርቅ ይገፋፋናል። ስህተት በምንሠራበት ጊዜ ደግሞ ንስሐ እንድንገባና አካሄዳችንን እንድናስተካክል ያነሳሳናል። በእርግጥም አምላክ ስለ ፍትሕ ያለውን አመለካከት መረዳታችን በግለሰብ ደረጃ የሚጠቅመን ከመሆኑም በላይ ወደ እሱ እንድንቀርብ ይረዳናል!

አምላክ ፍቅር ነው

“አምላክ ፍቅር ነው።”1 ዮሐንስ 4:8

አምላክ ኃያል፣ ጥበበኛና ፍትሐዊ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ኃይል፣ ጥበብ ወይም ፍትሕ ነው አይልም። አምላክ ፍቅር ነው ግን ይላል። ለምን? ምክንያቱም አምላክ ኃይል ያለው መሆኑ እርምጃ እንዲወስድ ያስችለዋል፤ እርምጃ የሚወስደው ደግሞ በፍትሑና በጥበቡ ላይ ተመሥርቶ ነው። ይሖዋን እርምጃ እንዲወስድ የሚያነሳሳው ግን ፍቅሩ ነው። አምላክ ሁሉንም ነገር የሚያደርገው በፍቅር ተገፋፍቶ ነው።

ይሖዋ አንዳች የሚጎድለው ነገር ባይኖርም ፍቅሩ በሰማይም ሆነ በምድር የሚኖሩ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታትን እንዲፈጥር አነሳስቶታል፤ እነዚህ ፍጥረታት ከእሱ ፍቅርና እንክብካቤ ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ። በተጨማሪም አምላክ በደግነት ተነሳስቶ ምድርን ለሰብዓዊ ፍጥረታቱ ምቹ መኖሪያ እንድትሆን አዘጋጅቷል። ከዚህም በላይ “በክፉዎችም ሆነ በጥሩ ሰዎች ላይ ፀሐዩን [በማውጣት]” እንዲሁም “በጻድቃንም ሆነ ጻድቃን ባልሆኑ ሰዎች ላይ ዝናብ [በማዝነብ]” ለሁሉም ሰዎች ፍቅር ማሳየቱን ቀጥሏል።—ማቴዎስ 5:45

በተጨማሪም “ይሖዋ እጅግ አፍቃሪና መሐሪ” ነው። (ያዕቆብ 5:11) በቅን ልቦና ተነሳስተው እሱን ለማወቅና ወደ እሱ ለመቅረብ ጥረት ለሚያደርጉ ሰዎች ፍቅሩን ያሳያቸዋል። አምላክ እንዲህ ላሉ ሰዎች በግለሰብ ደረጃ ትኩረት ይሰጣል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “እሱ ስለ እናንተ ያስባል” ይላል።—1 ጴጥሮስ 5:7

አምላክ ፍቅር መሆኑ ምን ጥቅም ያስገኝልናል? ጀምበር ስትጠልቅ የሚታየው ውበት ልባችን በደስታ እንዲሞላ ያደርጋል። የሕፃን ልጅ ሳቅ መስማት ያስደስተናል። የቤተሰባችን አባላት የሚያሳዩን ፍቅር ስሜታችንን በጥልቅ ይነካዋል። እነዚህ ነገሮች ለመኖር የግድ አስፈላጊ ባይሆኑም ሕይወታችን እጅግ አስደሳች እንዲሆን ያደርጋሉ።

በተጨማሪም የአምላክ ፍቅር መግለጫ የሆነው የጸሎት ዝግጅት በእጅጉ ይጠቅመናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ” በማለት ይመክረናል። አምላክ ልክ እንደ አንድ አፍቃሪ አባት ሊረዳን ይፈልጋል፤ ያስጨነቁንን ነገሮች በሙሉ ሌላው ቀርቶ ለሰዎች መንገር የማንፈልጋቸውን ነገሮች እንኳ አውጥተን እንድንነግረው ግብዣ አቅርቦልናል። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ይሖዋ በፍቅሩ ተገፋፍቶ “ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ [የሆነውን] የአምላክ ሰላም” እንደሚሰጠን ቃል ገብቶልናል።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7

ስለ አምላክ ዋና ዋና ባሕርያት ማለትም ስለ ኃይሉ፣ ጥበቡ፣ ፍትሑና ፍቅሩ የተሰጡትን አጠር ያሉ ማብራሪያዎች ማንበብህ የአምላክን ባሕርያት ይበልጥ እንድታውቅ አልረዳህም? ስለ አምላክ ያለህ እውቀት ይበልጥ እየጨመረ እንዲሄድ አምላክ ለሰው ልጆች ሲል ከዚህ በፊት ያደረጋቸውንና ወደፊት የሚያደርጋቸውን ነገሮች እንድታነብ እንጋብዝሃለን።

አምላክ ምን ባሕርያት አሉት? ይሖዋ ከሌላ ከየትኛውም አካል ይበልጥ ኃያል፣ ጥበበኛና ፍትሐዊ ነው። ከሁሉ በላይ ማራኪ የሆነው ባሕርይው ግን ፍቅር ነው