በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መምረጥ ነፃነት ምን ይላል? አምላክ ዕድልህን ወስኖታል?

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መምረጥ ነፃነት ምን ይላል? አምላክ ዕድልህን ወስኖታል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 አምላክ ዕድላችንን አስቀድሞ ከመወሰን ይልቅ የመምረጥ ነፃነት ይኸውም የራሳችንን ምርጫ የማድረግ መብት በመስጠት አክብሮናል። እስቲ የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች እንመልከት፦

  •   አምላክ ሰውን የፈጠረው በራሱ መልክ ወይም አምሳል ነው። (ዘፍጥረት 1:26) በዋነኝነት በደመ ነፍስ ከሚንቀሳቀሱት ከእንስሳት በተለየ እንደ ፍቅርና ፍትሕ የመሳሰሉ ባሕርያትን በማንጸባረቅ ፈጣሪያችንን መምሰል እንችላለን። ደግሞም ልክ እንደ ፈጣሪያችን ነፃ ምርጫ ማድረግ እንችላለን።

  •   የወደፊቱ ሕይወታችን በአብዛኛው በእኛ ምርጫ ላይ የተመካ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የአምላክን ቃል በማዳመጥ’ ማለትም ሕጎቹን በመታዘዝ ‘ሕይወትን እንድንመርጥ’ ያበረታታናል። (ዘዳግም 30:19, 20) የመምረጥ ነፃነት ባይኖረን ኖሮ እንዲህ ያለው ግብዣ ትርጉም የለሽ እንዲያውም ጭካኔ ይሆን ነበር። አምላክ እሱ የሚፈልገውን እንድንፈጽም ከማስገደድ ይልቅ ‘ትእዛዜን ሰምተህ ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ ይሆናል’ የሚል ፍቅራዊ ግብዣ አቅርቦልናል።​—ኢሳይያስ 48:18

  •   በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥመን ስኬትም ይሁን ውድቀት አስቀድሞ አልተወሰነም። በመሆኑም በሥራችን ስኬት ማግኘት ከፈለግን ጠንክረን መሥራት ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ “እጅህ የሚያገኘውን ሥራ ሁሉ በሙሉ ኀይልህ ሥራው” ይላል። (መክብብ 9:10) በተጨማሪም “የትጕህ ሰው ዕቅድ ወደ ትርፍ ያመራል” በማለት ይናገራል።​—ምሳሌ 21:5

 የመምረጥ ነፃነታችን ከአምላክ ያገኘነው ውድ ስጦታ ነው፤ ምክንያቱም በራሳችን ፍላጎት ተነሳስተን አምላክን ‘በሙሉ ልባችን’ እንደምንወደው ለማሳየት የሚያስችል አጋጣሚ ይሰጠናል።​—ማቴዎስ 22:37

አምላክ ሁሉንም ነገር መቆጣጠር አይችልም ማለት ነው?

 መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ሁሉን ቻይ እንደሆነ ያስተምራል፤ የራሱን ኃይል መገደብ የሚችለው እሱ ብቻ ነው። (ኢዮብ 37:23፤ ኢሳይያስ 40:26) ይሁንና ኃይሉን ሁሉንም ነገሮች ለመቆጣጠር አይጠቀምበትም። ለምሳሌ ያህል አምላክ የሕዝቦቹ ጠላቶች ከነበሩት ከባቢሎናውያን ጋር በተያያዘ ሲናገር “ራሴንም ገታሁ” ብሏል። (ኢሳይያስ 42:14) ዛሬም በተመሳሳይ የመምረጥ ነፃነታቸውን ተጠቅመው ሌሎችን እየጎዱ ያሉ ሰዎችን ለጊዜው እየታገሠ ነው። ይሁን እንጂ አምላክ እርምጃ መውሰዱ አይቀርም።​—መዝሙር 37:10, 11