በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

ዘኁልቁ 6:24-26—“እግዚአብሔር ይባርክህ፤ ይጠብቅህም”

ዘኁልቁ 6:24-26—“እግዚአብሔር ይባርክህ፤ ይጠብቅህም”

 “ይሖዋ ይባርክህ፤ ደግሞም ይጠብቅህ። ይሖዋ ፊቱን ያብራልህ፤ ሞገሱንም ያሳይህ። ይሖዋ ፊቱን ወደ አንተ ይመልስ፤ ሰላምም ይስጥህ።”—ዘኁልቁ 6:24-26 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “እግዚአብሔር ይባርክህ፣ ይጠብቅህም፤ እግዚአብሔር ፊቱን ያብራልህ፣ ይራራልህም፤ እግዚአብሔር ፊቱን ወደ አንተ ያንሣ፣ ሰላምንም ይስጥህ።”—ዘኁልቁ 6:24-26 የ1954 ትርጉም

የዘኁልቁ 6:24-26 ትርጉም

 እነዚህ ቃላት የካህናት ወይም የአሮን ቃለ ቡራኬ ተብለው ይጠራሉ፤ አሮን የእስራኤል የመጀመሪያው ሊቀ ካህናት ነው። (ዘፀአት 28:1) እነዚህ የበረከት ቃላት እንዲነገሩ ያደረገው አምላክ ነው። (ዘኁልቁ 6:22, 23) አምላክ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አሮንንና ወንዶች ልጆቹን እንዲህ በላቸው፦ ‘የእስራኤልን ሕዝብ የምትባርኩት በዚህ መንገድ ነው።” ከዚያም በዘኁልቁ 6:24-26 ላይ የሚገኙትን የበረከት ቃላት ነገረው። ታማኝ ካህናት ይህን መለኮታዊ ትእዛዝ ይከተሉ ነበር። ይሖዋ a የሚለውን የአምላክ ስምም ይቀድሱ ነበር። ቁጥር 27 “እኔም እንድባርካቸው [ካህናቱ] ስሜን በእስራኤል ሕዝብ ላይ ያድርጉ” ይላል።

 “ይሖዋ ይባርክህ፤ ደግሞም ይጠብቅህ።” ይሖዋ አገልጋዮቹን የሚባርከው እነሱን በመጠበቅ፣ በመምራትና ስኬት በመስጠት ነው። (ምሳሌ 10:22) ዘኁልቁ 6:24-26 ላይ “አንተ” የሚለው የነጠላ ቁጥር ተውላጠ ስም ጥቅም ላይ እንደዋለ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ይህ ምን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል? አምላክ ብሔሩን በቡድን ደረጃ ብቻ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃም እያንዳንዱን እስራኤላዊ የመባረክ ፍላጎት እንዳለው ያሳያል።

 “ይሖዋ ፊቱን ያብራልህ፤ ሞገሱንም ያሳይህ።” “ፊቱን ያብራልህ” የሚለው ልመና አምላክ ግለሰቡን ሞገስ እንዲያሳየውና በበጎ እንዲመለከተው የሚቀርብ ጥያቄ ነው። b ሐሳቡ “አምላክ በፈገግታ ይመልከትህ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። (ዘኁልቁ 6:25 ኒው ኢንተርናሽናል ሪደርስ ቨርዥን) ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ሞገስ የሚያሳየው እነሱን በደግነት፣ በርኅራኄና በምሕረት በመያዝ ነው።—ኢሳይያስ 30:18

 “ይሖዋ c ፊቱን ወደ አንተ ይመልስ፤ ሰላምም ይስጥህ።” ይሖዋ ወደ አገልጋዮቹ ‘ፊቱን የሚመልሰው’ በፍቅር ተነሳስቶ ለእነሱ ትኩረት በመስጠት ነው፤ እንዲሁም ሰላም ይሰጣቸዋል። ይህ ሰላም ምን ነገሮችን ያካትታል? አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው “ሰላም ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል (ሻሎም) የሚያመለክተው የጦርነት አለመኖርን ብቻ አይደለም፤ አጠቃላይ ደህንነትን እንዲሁም በአካላዊም ሆነ በመንፈሳዊ ጥሩ ሁኔታ ላይ መሆንን የሚያጠቃልል ነው።”

 እስራኤላውያን፣ ካህናቱ የሚሰጡት ይህ ቃለ ቡራኬ የሚፈጸምላቸው ይሖዋን ከታዘዙ ነው። (ዘሌዋውያን 26:3-6, 9) ታዛዥ በነበሩበት ጊዜ ሁሉ አምላክ ቃሉን ጠብቆ ባርኳቸዋል። ለምሳሌ ያህል በንጉሥ ሰለሞን እና በንጉሥ ሕዝቅያስ ዘመን የነበራቸውን ሕይወት ማንሳት ይቻላል።—1 ነገሥት 4:20, 25፤ 2 ዜና መዋዕል 31:9, 10

 ክርስቲያኖች ይህን ቃለ ቡራኬ እንዲደግሙ አይጠበቅባቸውም፤ ሆኖም ስለ ሌሎች ሰዎች ወደ አምላክ ሲጸልዩ ወይም የእምነት አጋሮቻቸውን ሲያበረታቱ ተመሳሳይ ሐሳብ መናገር ይችላሉ። (1 ተሰሎንቄ 5:11, 25) ይሖዋ መቼም አይለወጥም። እሱ ታማኝ አገልጋዮቹን መባረክና መጠበቅ ምንጊዜም ያስደስተዋል። እውነተኛ ክርስቲያኖች፣ ይሖዋ በሞገሱ ‘ፊቱን’ እንደሚያበራላቸው ስለሚያውቁ ሰላም አላቸው።

የዘኁልቁ 6:24-26 አውድ

 እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር በሚያደርጉት ጉዞ ላይ በሲና ተራራ አቅራቢያ ለአንድ ዓመት ገደማ ሰፍረው ነበር። በዚህ ወቅት አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው መመሪያዎች በዘኁልቁ መጽሐፍ የመጀመሪያ አሥር ምዕራፎች ላይ ተዘግበዋል። ይሖዋ ሕዝቡን በብሔር ያደራጀውና በሕጉ ቃል ኪዳን ውስጥ የተካተቱትን ሕጎች የሰጣቸው በዚሁ ወቅት ነው።

 ይሖዋ ለሙሴ የነገረው ሌላው ነገር፣ ካህናት እንዲሆኑ የተመረጡት አሮንና ወንዶች ልጆቹ እስራኤላውያንን ምን ብለው እንደሚባርኩ ነው። (ዘኁልቁ 6:22, 23) ከዚያ ጊዜ አንስቶ አሮንና ዘሮቹ ዘኁልቁ 6:24-26 ላይ የሚገኙትን ቃላት በመጠቀም የእስራኤልን ብሔር መባረክ ጀመሩ። በኋላ ላይ ደግሞ ልማድ ሆነና ካህኑ ቤተ መቅደሱ ውስጥ የቀኑን የመጨረሻ መሥዋዕት አቅርቦ ሲያበቃ እነዚህን ቃላት ይደግም ነበር።

 የዘኁልቁ መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።

a ይሖዋ፣ በዕብራይስጥ የተቀመጠው የአምላክ ስም የተለመደ የአማርኛ አጠራር ነው። ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በአምላክ የግል ስም ከመጠቀም ይልቅ “ጌታ” የሚለውን የማዕረግ ስም የመረጡት ለምን እንደሆነ ለማወቅ “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

b በአንጻሩ እስራኤላውያን ይሖዋን የሚያሳዝን ነገር ባደረጉበት ወቅት ‘ፊቱን እንደሰወረባቸው’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ኢሳይያስ 59:2፤ ሚክያስ 3:4

c አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንደገለጸው በዚህ ጥቅስ ላይ የአምላክ ስም የተደጋገመው “ለማጉላትና [ቁጥር 27] ላይ ለሚገኘው ሐሳብ ክብደት ለመስጠት ነው።” ይሁንና አንዳንዶች የአምላክ ስም ሦስት ጊዜ መጠቀሱ የሥላሴን ትምህርት የሚደግፍ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ ግን ትክክል አይደለም። ሥላሴን የሚደግፍ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኝ ጽሑፍ እንዲህ ሲል ሐቁን ተቀብሏል፦ የአምላክ ስም ሦስት ጊዜ መጠቀሱ “ቃለ ቡራኬውን ለሚሰጠው ካህንም ሆነ ለተቀባዩ ሕዝብ እንዲህ ያለ መልእክት ሊያስተላልፍ አይችልም። ሦስቴ መጠቀሱ ለቃለ ቡራኬው ውበትና ሙላት ከመጨመር ውጭ ለእነሱ የሚያስተላልፈው ትርጉም የለም።” (ዘ ፑልፒት ኮሜንታሪ፣ ጥራዝ 2፣ ገጽ 52) ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “አምላክ ሥላሴ ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።