በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

ምሳሌ 16:3—“የምታደርገውን ሁሉ ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ”

ምሳሌ 16:3—“የምታደርገውን ሁሉ ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ”

 “የምታደርገውን ሁሉ ለይሖዋ አደራ ስጥ፤ ዕቅድህም ሁሉ ይሳካል።”—ምሳሌ 16:3 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “የምታደርገውን ሁሉ ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤ ዕቅድህም ሁሉ ይሳካልሃል።”—ምሳሌ 16:3 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

የምሳሌ 16:3 ትርጉም

 ይህ ጥቅስ እውነተኛውን አምላክ የሚያገለግሉ ሰዎች የእሱን መመሪያ በመፈለግና በመከተል የሚተማመኑበት እስከሆነ ድረስ ዕቅዳቸው እንደሚሳካ ዋስትና ይሰጣል።

 “የምታደርገውን ሁሉ ለይሖዋ አደራ ስጥ።” የይሖዋ a አገልጋዮች ውሳኔ ከማድረጋቸው በፊት በትሕትና የእሱን አመራር ይፈልጋሉ። (ያዕቆብ 1:5) ለምን? አንዱ ምክንያት የሰው ልጆች ብዙውን ጊዜ በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ነገሮች መቆጣጠር ስለማይችሉ ነው። (መክብብ 9:11፤ ያዕቆብ 4:13-15) ከዚህም ሌላ ዕቅዳቸውን ለማሳካት የሚያስችል ጥበብ ላይኖራቸው ይችላል። በዚህም የተነሳ ብዙዎች መንገዳቸውን ለአምላክ አደራ በመስጠት ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ያደርጋሉ። ይህን የሚያደርጉት መመሪያ ለማግኘት ወደ እሱ በመጸለይ እንዲሁም በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጸው ፈቃዱ ጋር የሚስማማ እርምጃ በመውሰድ ነው።—ምሳሌ 3:5, 6፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

 “የምታደርገውን ሁሉ ለእግዚአብሔር b ዐደራ ስጥ” የሚለው አገላለጽ ቃል በቃል ሲተረጎም “ሥራህን ለይሖዋ አስተላልፍ” ማለት ነው። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደሚናገረው እዚህ ላይ ያለው አገላለጽ “አንድን ከባድ ሸክም ከጀርባው አውርዶ ከእሱ የበለጠ አቅምና ጥንካሬ ወዳለው አካል የሚያስተላልፍን ሰው” ያመለክታል። በትሕትና በአምላክ የሚታመኑ ሰዎች እሱ እንደሚረዳቸውና እንደሚደግፋቸው መተማመን ይችላሉ።—መዝሙር 37:5፤ 55:22

 “የምታደርገውን ሁሉ” የሚለው አገላለጽ ሰዎች ያላቸው ዕቅድ በሙሉ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው ወይም እሱ እንደሚባርከው የሚያመለክት አይደለም። የይሖዋን በረከት ማግኘት ከፈለጉ ዕቅዳቸው ከእሱ መሥፈርትም ሆነ ከፈቃዱ ጋር የሚስማማ መሆን ይኖርበታል። (መዝሙር 127:1፤ 1 ዮሐንስ 5:14) አምላክ ታዛዥ ያልሆኑ ሰዎችን አይባርክም። እንዲያውም “የክፉዎችን ዕቅድ . . . ያጨናግፋል።” (መዝሙር 146:9) በሌላ በኩል ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹትን መሥፈርቶቹን በማክበር ለእሱ ተገዢ የሆኑ ሰዎችን ይደግፋል።—መዝሙር 37:23

 “ዕቅድህም ሁሉ ይሳካል።” አንዳንድ ተርጓሚዎች ይህን አገላለጽ “አሳብህም ትጸናለች” ብለው ተርጉመውታል። በተለምዶ ብሉይ ኪዳን ተብለው በሚጠሩት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “ትጸናለች” ተብሎ የተተረጎመው ቃል መሠረት መጣልን ያመለክታል፤ ብዙውን ጊዜ ይህ ቃል የአምላክ የፍጥረት ሥራዎች የጸኑ መሆናቸውን ለማመልከት ተሠርቶበታል። (ምሳሌ 3:19፤ ኤርምያስ 10:12) በተመሳሳይም አምላክ በእሱ ዘንድ ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርጉ ሰዎችን ዕቅድ ያጸናል፤ አስተማማኝ፣ ደስተኛና ስኬታማ ሕይወት እንዲመሩም ይረዳቸዋል።—መዝሙር 20:4፤ ምሳሌ 12:3

የምሳሌ 16:3 አውድ

 ይህን ጥቅስ የጻፈው አብዛኛውን የምሳሌ መጽሐፍ የጻፈው ንጉሥ ሰለሞን ነው። ሰለሞን አምላክ ጥበብ ስለሰጠው በሺዎች የሚቆጠሩ ምሳሌዎችን ተናግሯል።—1 ነገሥት 4:29, 32፤ 10:23, 24

 ሰለሞን ምዕራፍ 16⁠ን የጀመረው የይሖዋን ጥበብ ከፍ ከፍ በማድረግና አምላክ ኩሩ ሰዎችን እንደሚጸየፍ በመግለጽ ነው። (ምሳሌ 16:1-5) ከዚያም ምዕራፉ አንባቢው አንድ ወሳኝ መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ ይረዳዋል፤ ይህ ነጥብ የምሳሌ መጽሐፍ ጭብጥ ነው ማለት ይቻላል፦ ሰዎች እውነተኛ ጥበብ ማግኘትና ስኬታማ መሆን የሚችሉት ትሑት በመሆን አምላክ መንገዳቸውን እንዲመራላቸው ከፈቀዱ ብቻ ነው። (ምሳሌ 16:3, 6-8, 18-23) ይህ መሠረታዊ እውነታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ ተገልጿል።—መዝሙር 1:1-3፤ ኢሳይያስ 26:3፤ ኤርምያስ 17:7, 8፤ 1 ዮሐንስ 3:22

 የምሳሌ መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።

a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

b የአዲሱ መደበኛ ትርጉም መቅድም እንደሚገልጸው ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በመለኮታዊው ስም ምትክ “እግዚአብሔር” የሚለውን መጠሪያ ይጠቀማል፤ በዚህ ጊዜ የፊደላቱ አጣጣል በሰያፍ ይሆናል። ይህ ልማድ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎችን የሚያምታታ የሆነው ለምን እንደሆነ ለማወቅ በዚህ ዓምድ ሥር የሚገኘውን “ኢሳይያስ 42:8—‘እኔ እግዚአብሔር ነኝ’” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።