በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በእምነታቸው ምሰሏቸው | ሚርያም

“ለይሖዋ ዘምሩ”!

“ለይሖዋ ዘምሩ”!

 ልጅቷ ራቅ ብላ ተደብቃ ሁኔታውን እየተከታተለች ነው፤ ዓይኗ ቄጠማው መሃል አርፏል። ሰውነቷ በጭንቀት ተገታትሯል፤ ታላቁ የአባይ ወንዝ ቀስ ብሎ እየፈሰሰ ነው። ጊዜው ነጎደ፤ እሷ ግን በዙሪያዋ በሚበሩት ነፍሳት ትኩረቷ ሳይሰረቅ እዚያው በቆመችበት እየጠበቀች ነው። ዓይኗ ያረፈው በቄጠማው መሃል በተደበቀው ውኃ የማያስገባ ቅርጫት ላይ ነው፤ ሕፃኑ ወንድሟ በቅርጫቱ ውስጥ አለ። ወንድሟ በዚያ ቅርጫት ውስጥ ብቻውን መሆኑን ስታስብ ልቧ በሐዘን ደማ። ሆኖም የወላጆቿ ውሳኔ ትክክል መሆኑን ታውቃለች፤ በዚያ ክፉ ጊዜ ሕፃኑ ያለው ተስፋ ይህ ብቻ ነበር።

 ይህች ትንሽ ልጅ አስደናቂ ድፍረት አሳይታለች፤ አሁን ደግሞ ድፍረት የሚጠይቅ ሌላ ሁኔታ ሊያጋጥማት ነው። በዚህች ትንሽ ልጅ ልብ ውስጥ አንድ ግሩም ባሕርይ እያቆጠቆጠ ነው—እምነት። ቀጥሎ የሚያጋጥማት ነገር ይህን ባሕርይ ለማሳየት አጋጣሚ ይሰጣታል፤ መላው ሕይወቷን የቀረጸውም ይኸው ባሕርይ ነው። ዓመታት አልፈው ዕድሜዋ በገፋበት ጊዜ ይህ እምነቷ በሕዝቦቿ ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ የሚሰጠውን ዘመን እንድታልፍ አስችሏታል። ከባድ ስህተት በሠራችበት ወቅትም የረዳት ይኸው ባሕርይ ነው። ይህች ሴት ማን ነች? ካሳየችው እምነትስ ምን እንማራለን?

ሚርያም—የባሪያዎች ልጅ

 መጽሐፍ ቅዱስ የዚህች ልጅ ስም ማን እንደሆነ ባይናገርም ማንነቷ ብዙም አሻሚ አይደለም። ይህች ልጅ በግብፅ ምድር በባርነት የሚኖሩ አምራምና ዮካቤድ የተባሉ ዕብራውያን የመጀመሪያ ልጅ ነበረች፤ ስሟ ሚርያም ይባላል። (ዘኁልቁ 26:59) ሕፃኑ ወንድሟ ከጊዜ በኋላ ሙሴ የሚል ስም ወጥቶለታል። የሕፃኑ ታላቅ ወንድም የሆነው አሮን በወቅቱ ዕድሜው ሦስት ዓመት ገደማ ነበር። የሚርያምን ዕድሜ በእርግጠኝነት ማወቅ ባይቻልም በወቅቱ ዕድሜዋ ከአሥር ዓመት በታች ነበር ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ይመስላል።

 ሚርያም የኖረችው ከባድ ጊዜ ውስጥ ነው። ግብፃውያን የሚርያም ወገን የሆኑትን ዕብራውያንን ስለፈሯቸው በባርነት ይገዟቸውና ይጨቁኗቸው ነበር። ዕብራውያኑ በቁጥር እየበዙ ሲሄዱ ግብፃውያኑ ስጋት ስላደረባቸው የከፋ ጭካኔ የሚንጸባረቅበት እርምጃ ወሰዱ። ፈርዖን የዕብራውያን ወንዶች ልጆች በሙሉ ልክ ሲወለዱ እንዲገደሉ አዘዘ። ሚርያም የንጉሡን ትእዛዝ ሳያከብሩ የቀሩት ሺፍራና ፑሃ የተባሉ አዋላጆች ስላሳዩት እምነት ታውቅ እንደነበር ምንም አያጠራጥርም።—ዘፀአት 1:8-22

 ሚርያም ወላጆቿ ያሳዩትን እምነትም ተመልክታለች። ውብ የሆነው ሦስተኛ ልጃቸው ከተወለደ በኋላ አምራምና ዮካቤድ ለሦስት ወር ደብቀው አቆዩት። የንጉሡን ትእዛዝ ፈርተው ልጃቸው እንዲገደል አሳልፈው አልሰጡትም። (ዕብራውያን 11:23) ሆኖም ሕፃን ልጅ መደበቅ ቀላል ነገር አይደለም፤ በመሆኑም በእነዚህ ወላጆች ፊት ከባድ ውሳኔ ተደቀነ። ዮካቤድ ልጁን አንድ ቦታ ወስዳ ልትደብቀው አሰበች፤ የልጁን ሕይወት መታደግና ልጁን ተንከባክቦ ማሳደግ የሚችል ሰው ሊያገኘው እንደሚችል ተስፋ አድርጋ ነበር። ይህች እናት ከደንገል ቅርጫት ስትሠራ፣ ቅርጫቱ ውኃ እንዳያስገባ በቅጥራንና በዝፍት ስትለቀልቀው፣ ከዚያም የምትወደውን ልጇን ወስዳ በአባይ ወንዝ ዳር ስታስቀምጠው ምን ያህል ጸልያ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ሚርያም እዚያው ቆይታ ሁኔታውን እንድትከታተል የነገረቻትም እሷ መሆን አለባት።—ዘፀአት 2:1-4

ሚርያም የወንድሟን ሕይወት ታደገች

 ሚርያም በትዕግሥት መጠባበቋን ቀጠለች። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ጥቂት ሴቶች ሲመጡ አየች። እነዚህ ሴቶች ተራ ግብፃውያን አልነበሩም። የመጡት የፈርዖን ሴት ልጅና ደንገጡሮቿ ናቸው፤ የፈርዖን ልጅ ገላዋን ለመታጠብ ወደ አባይ ወረደች። ሚርያም ይህን ስታይ ልቧ ዝቅ ብሎ መሆን አለበት። የፈርዖን ልጅ የአባቷን ትእዛዝ ጥሳ የዚህን ዕብራዊ ሕፃን ሕይወት ለማትረፍ ትሞክራለች ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው? ሚርያም በዚህ ሰዓት አጥብቃ ጸልያ እንደነበር ጥያቄ የለውም።

 በቄጠማው መሃል ያለውን ቅርጫት መጀመሪያ ያየችው የፈርዖን ልጅ ነች። ወዲያውኑም ቅርጫቱን እንድታመጣላት ባሪያዋን ላከቻት። የፈርዖን ልጅ “[ቅርጫቱን] ስትከፍት ሕፃኑን አየችው፤ ሕፃኑም እያለቀሰ ነበር።” ልጁን እንዳየችው አንዲት ዕብራዊት እናት የልጇን ሕይወት ለማትረፍ ያደረገችው ነገር እንደሆነ ገባት። ያም ቢሆን የፈርዖን ልጅ የሚያምረውን ሕፃን ስታይ አንጀቷ ተላወሰ። (ዘፀአት 2:5, 6) ንቁ የሆነችው ሚርያም በልዕልቲቱ ፊት ላይ የሚነበበውን ስሜት አስተዋለች። ሚርያም በይሖዋ ተማምና እርምጃ የምትወስድበት ጊዜ እንደደረሰ አወቀች። እንደምንም ራሷን አደፋፍራ ወደ ፈርዖን ልጅ ሄደች።

 አንዲት ዕብራዊት ባሪያ ወደ ንጉሣዊ ቤተሰብ አባል ሄዳ ለመናገር ብትደፍር ምን ሊያጋጥማት እንደሚችል አናውቅም። ሆኖም ሚርያም ለልዕልቲቱ ቀጥተኛ ጥያቄ አቀረበችላት፦ “ከዕብራውያን ሴቶች መካከል ልጁን እያጠባች የምታሳድግልሽ ሞግዚት ልጥራልሽ?” አለቻት። ደግሞም ይህን ጥያቄ ማቅረቧ ተገቢ ነበር። የፈርዖን ልጅ ራሷም ብትሆን ሕፃኑን እያጠባች ማሳደግ እንደማትችል ታውቃለች። ልጁ በራሱ ሕዝቦች መካከል ቢያድግ ትኩረት እንደማይስብ አስባ ሊሆን ይችላል፤ ልጁ ካደገ በኋላ ግን የጉዲፈቻ ልጇ አድርጋ ልትወስደውና እያስተማረች ልታሳድገው ትችላለች። የፈርዖን ልጅ “አዎ፣ ሂጂ!” ብላ ስትመልስላት የሚርያም ልብ በደስታ ፈንጥዞ መሆን አለበት።—ዘፀአት 2:7, 8

ሚርያም በድፍረት የሕፃኑን ወንድሟን ሁኔታ ስትከታተል

 ሚርያም በጭንቀት ተውጠው ወደሚጠብቋት ወላጆቿ እየሮጠች ሄደች። በደስታ እየፈነደቀች ለእናቷ ዜናውን ስትነግራት ይታይህ። በዚህ ጊዜ ዮካቤድ በጉዳዩ ውስጥ የይሖዋ እጅ እንዳለበት ተገንዝባ መሆን አለበት፤ በመሆኑም ከሚርያም ጋር ወደ ፈርዖን ልጅ ሄደች። ልዕልቲቱ “ይህን ሕፃን ወስደሽ እያጠባሽ አሳድጊልኝ፤ እኔም እከፍልሻለሁ” ስትላት ዮካቤድ የተሰማትን የእፎይታና የደስታ ስሜት ለመደበቅ ሞክራ ሊሆን ይችላል።—ዘፀአት 2:9

 ሚርያም በዚያ ዕለት ስለ አምላኳ ስለ ይሖዋ ብዙ ነገር ተምራለች። ይሖዋ ለሕዝቦቹ እንደሚያስብና ጸሎታቸውን እንደሚሰማ ተገንዝባለች። እንዲሁም ድፍረትና እምነት ማሳየት የሚችሉት አዋቂዎች ወይም ወንዶች ብቻ እንዳልሆኑ ተምራለች። ይሖዋ ሁሉም ታማኝ አገልጋዮቹ የሚያቀርቡትን ጸሎት ይሰማል። (መዝሙር 65:2) እንግዲያው ልጅ አዋቂ፣ ወንድ ሴት ሳይል በዚህ አስጨናቂ ዘመን የሚኖሩ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ ይህን እውነታ ማስታወስ ይኖርባቸዋል።

ሚርያም—ታጋሽ እህት

 ዮካቤድ ሕፃኑን እያጠባች ተንከባክባ አሳደገችው። ሚርያም ሕይወቱን ያተረፈችለትን ወንድሟን ምን ያህል ትወደው እንደነበር መገመት አያዳግትም። ምናልባትም መናገር ያስተማረችው እሷ ልትሆን ትችላለች፤ የአምላኩን የይሖዋን ስም ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጠራ ሚርያም ምን ያህል ተደስታ ሊሆን እንደሚችል አስበው። ሕፃኑ አድጎ ወደ ፈርዖን ልጅ የሚወሰድበት ጊዜ ደረሰ። (ዘፀአት 2:10) በዚህ ወቅት መላው ቤተሰብ በሐዘን ተውጦ መሆን አለበት። ሚርያም የፈርዖን ልጅ ሙሴ ብላ የሰየመችው ወንድሟ አዋቂ ሲሆን ምን ዓይነት ሰው እንደሚወጣው ለማየት ምንኛ ጓጉታ ይሆን! በግብፅ ንጉሣዊ ቤተሰብ ውስጥ ሲያድግ ለይሖዋ ያለውን ፍቅር ይዞ መቀጠል ይችል ይሆን?

 ከዓመታት በኋላ መልሱ ግልጽ ሆነ። ሚርያም ትንሹ ወንድሟ ካደገ በኋላ በፈርዖን ቤተ መንግሥት ውስጥ መኖር የሚያስገኝለትን ክብርና ዝና ከመቀበል ይልቅ አምላኩን ይሖዋን ለማገልገል እንደወሰነ ስታውቅ ልቧ በኩራት ተሞልቶ መሆን አለበት! ሙሴ 40 ዓመት ሲሞላው ከሕዝቦቹ ጎን ለመቆም የራሱን እርምጃ ወሰደ። ሙሴ አንድ ግብፃዊ አንድን ዕብራዊ ባሪያ ሲደበድበው ሲያይ ግብፃዊውን ገደለው። በዚህ ምክንያት ሕይወቱ አደጋ ላይ ስለወደቀ ከግብፅ ሸሸ።—ዘፀአት 2:11-15፤ የሐዋርያት ሥራ 7:23-29፤ ዕብራውያን 11:24-26

 ሙሴ ርቆ ተጉዞ በምድያም እረኛ ሆኖ ባሳለፋቸው አራት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ሚርያም ስለ እሱ ምንም ወሬ አልሰማች ይሆናል። (ዘፀአት 3:1፤ የሐዋርያት ሥራ 7:29, 30) ዓመታቱ እያለፉ ሲሄዱ ሚርያምም ዕድሜዋ ገፋ። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ሚርያም በሕዝቦቿ ላይ የሚደርሰው እንግልት ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ ሲሄድ አይታለች።

ነቢዪቷ ሚርያም

 ሙሴ ሕዝቡን ነፃ የማውጣት ተልእኮ ከአምላኩ ተቀብሎ ሲመለስ ሚርያም በ80ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳትገኝ አትቀርም። አሮን የሙሴ ቃል አቀባይ ሆነ፤ የሚርያም ሁለት ወንድሞች አንድ ላይ ሆነው ወደ ፈርዖን በመቅረብ ንጉሡ የአምላክን ሕዝብ እንዲለቅ ጥያቄ አቀረቡ። ፈርዖን ሙሴንና አሮንን በተቃወመበትና እነሱም አሥሩን መቅሰፍቶች አስመልክቶ ግብፃውያንን ለማስጠንቀቅ በተደጋጋሚ በፈርዖን ፊት በቆሙበት ወቅት ሚርያም ወንድሞቿን ለመደገፍና ለማበረታታት የቻለችውን ሁሉ እንዳደረገች ጥርጥር የለውም። በመጨረሻም አሥረኛው መቅሰፍት የግብፃውያንን የበኩር ልጆች በሙሉ ከገደለ በኋላ እስራኤላውያን ነፃ የሚወጡበት ጊዜ ደረሰ። ሕዝቡ የሙሴን አመራር ተከትለው ከግብፅ ሲወጡ ሚርያም እነሱን ለመርዳት ደፋ ቀና ስትል ይታይህ።—ዘፀአት 4:14-16, 27-31፤ 7:1–12:51

 በኋላም እስራኤላውያን በቀይ ባሕርና በግብፅ ሠራዊት መካከል አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው በነበረበት ወቅት ሚርያም ወንድሟ ሙሴ በባሕሩ ፊት ቆሞ በትሩን ወደ ላይ ሲያነሳ አየችው። ባሕሩ ለሁለት ተከፈለ! ይሖዋ ሕዝቦቹን በደረቅ መሬት ሲያሻግራቸው ማየት የሚርያምን እምነት ምንኛ አጠናክሮት ይሆን! በእርግጥም የምታመልከው አምላክ የገባውን ቃል በሙሉ መፈጸም የሚችል ሁሉን ቻይ አምላክ ነው።—ዘፀአት 14:1-31

 እስራኤላውያን በሙሉ ባሕሩን ከተሻገሩ በኋላ ባሕሩ በፈርዖንና በሠራዊቱ ላይ ተመልሶ ሲመጣባቸው ሚርያም ይሖዋ በምድር ላይ ካለው እጅግ ኃያል ሠራዊት የሚበልጥ ኃይል እንዳለው አየች። በዚህ ወቅት ሕዝቡ ለይሖዋ ለመዘመር ተነሳሳ። ሚርያምም ሴቶቹን በመምራት እንደሚከተለው እያለች ዘመረች፦ “በክብር እጅግ ከፍ ከፍ ስላለ ለይሖዋ ዘምሩ። ፈረሱንና ፈረሰኛውን ባሕር ውስጥ ጣላቸው።”—ዘፀአት 15:20, 21፤ መዝሙር 136:15

ሚርያም የእስራኤልን ሴቶች በመምራት በቀይ ባሕር ዳርቻ የድል መዝሙር ስትዘምር

 ሚርያም ይህን ታሪካዊ ወቅት ልትረሳው አትችልም። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በዚህ ጊዜ ሚርያምን ነቢዪት በማለት ይጠራታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነቢዪት ተብላ የተጠራችው የመጀመሪያዋ ሴት ሚርያም ናት። ሚርያም ይሖዋን በዚህ ልዩ መንገድ እንዲያገለግሉ ከተመረጡት ጥቂት ሴቶች መካከል አንዷ ነበረች።—መሳፍንት 4:4፤ 2 ነገሥት 22:14፤ ኢሳይያስ 8:3፤ ሉቃስ 2:36

 ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይሖዋ እንደሚያየን እንዲሁም ልባዊ ጥረታችንን፣ ትዕግሥታችንንና እሱን ለማስደሰት ያለንን ፍላጎት ለመባረክ እንደሚጓጓ ያስገነዝበናል። ወጣት አረጋዊ፣ ወንድ ሴት ሳይል ሁላችንም በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ማሳየት እንችላለን። እንዲህ ያለው እምነት ይሖዋን ያስደስተዋል፤ እሱ እምነታችንን ፈጽሞ የማይረሳ ከመሆኑም ሌላ ወሮታ ሊከፍለን ይፈልጋል። (ዕብራውያን 6:10፤ 11:6) በእርግጥም ሚርያምን በእምነቷ መምሰላችን ምንኛ የተገባ ነው!

ኩሩዋ ሚርያም

 መብትና ታዋቂነት በረከት ብቻ ሳይሆን አደጋም ሊያስከትል ይችላል። እስራኤላውያን ከባርነት ነፃ በወጡበት ወቅት በብሔሩ ውስጥ ከማንም በላይ ታዋቂ የሆነችው ሴት ሚርያም ሳትሆን አትቀርም። ታዲያ ሚርያም በኩራትና በሥልጣን ጥመኝነት ወጥመድ ትወድቅ ይሆን? (ምሳሌ 16:18) ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ለኩራት እጅ መስጠቷ ያሳዝናል።

 እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ ከጥቂት ወራት በኋላ ሙሴ ከሩቅ አገር የመጡ እንግዶችን አስተናገደ፤ እነዚህ እንግዶች የሙሴ አማት ዮቶር፣ የሙሴ ሚስት ሲፓራና ሁለቱ ልጆቻቸው ነበሩ። ሙሴ ሲፓራን ያገባት ምድያም ውስጥ ለ40 ዓመት በኖረበት ወቅት ነበር። ሲፓራ ከተወሰነ ጊዜ በፊት ቤተሰቧን ለመጠየቅ ወደ ምድያም ሄዳ የነበረ ይመስላል፤ አሁን ደግሞ አባቷ ወደ እስራኤላውያን ሰፈር አመጣት። (ዘፀአት 18:1-5) እስራኤላውያን የእነዚህን እንግዶች መምጣት ሲሰሙ ተደስተው መሆን አለበት። አምላክ ሕዝቡን ከግብፅ እንዲያወጣ የመረጠውን ሰው የትዳር ጓደኛ ለማየት ብዙዎች ጓጉተው እንደሚሆን ጥያቄ የለውም።

 ሚርያምስ ተደስታ ይሆን? መጀመሪያ ላይ ተደስታ ሊሆን ይችላል። ከጊዜ በኋላ ግን በኩራት የተሸነፈች ይመስላል። ሚርያም ሲፓራ በብሔሩ ውስጥ ከፍተኛ ታዋቂነት በማግኘት የእሷን ቦታ ልትወስድ እንደምትችል በማሰብ ሰግታ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ ሚርያምና አሮን አሉታዊ ነገር መናገር ጀመሩ። እንዲህ ያለው ንግግር ደግሞ ተባብሶ መራራና ጎጂ መሆኑ እንደማይቀር የታወቀ ነው። መጀመሪያ ላይ ወሬው ያጠነጠነው በሲፓራ ዙሪያ ነበር፤ ሲፓራ ኩሻዊት እንጂ እስራኤላዊት እንዳልሆነች በመናገር አጉረመረሙ። a በጊዜ ሂደት ግን ሁኔታው ተባብሶ በሙሴ ላይም ማጉረምረም ጀመሩ። ሚርያምና አሮን “ለመሆኑ ይሖዋ የሚናገረው በሙሴ አማካኝነት ብቻ ነው? በእኛስ በኩል አልተናገረም?” ይሉ ነበር።—ዘኁልቁ 12:1, 2

ሚርያም በሥጋ ደዌ ተመታች

 ሚርያምና አሮን የተናገሩት ነገር በውስጣቸው መርዘኛ ዝንባሌ እያቆጠቆጠ እንዳለ ያሳያል። ለራሳቸው ተጨማሪ ሥልጣንና ተሰሚነት ማግኘት ስለፈለጉ ይሖዋ ሙሴን በመጠቀሙ አልተደሰቱም። እንዲህ የተሰማቸው ሙሴ የሥልጣን ጥመኛና ጨቋኝ ስለነበረ ይሆን? በፍጹም። ሙሴ እንደ ማንኛውም ሰው የራሱ ድክመቶች ቢኖሩበትም በሥልጣን ጥምና በኩራት የሚጠረጠር ሰው አልነበረም። በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ዘገባ “ሙሴ በምድር ላይ ከነበሩ ሰዎች ሁሉ ይልቅ በጣም የዋህ ነበር” ይላል። ያም ሆነ ይህ ሚርያምና አሮን የተናገሩት ነገር ተገቢ አልነበረም፤ ደግሞም አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ነበሩ። ምክንያቱም ዘገባው እንደሚናገረው ይሖዋ የሚናገሩትን “ይሰማ ነበር።”—ዘኁልቁ 12:2, 3

 በድንገት ይሖዋ ሦስቱም ወደ መገናኛ ድንኳኑ እንዲመጡ ጠራቸው። የይሖዋን መገኘት የሚያመለክተው የደመና ዓምድም ወርዶ በድንኳኑ መግቢያ ላይ ቆመ። ከዚያም ይሖዋ ተናገረ። ከሙሴ ጋር ስላለው ልዩ ዝምድና እንዲሁም የሰጠውን ከፍተኛ አደራ በመግለጽ ሚርያምንና አሮንን ገሠጻቸው። ከዚያም ይሖዋ “ታዲያ አገልጋዬን ሙሴን ስትነቅፉት ምነው አልፈራችሁም?” በማለት ጠየቃቸው። ሚርያምና አሮን ይህን ሲሰሙ በፍርሃት ተንቀጥቅጠው መሆን አለበት። ይሖዋ ሙሴን መናቃቸውን እሱን ራሱን እንደመናቅ አድርጎ ቆጥሮታል።—ዘኁልቁ 12:4-8

 የጉዳዩ ጠንሳሽ ሚርያም ሳትሆን አትቀርም፤ ከእሷ ጋር ተባብሮ የሙሴን ሚስት እንዲቃወም ታናሽ ወንድሟን አሮንን ገፋፍታው ሊሆን ይችላል። በወቅቱ ቅጣት የተቀበለችው ሚርያም የሆነችው ለዚህ ሳይሆን አይቀርም። ይሖዋ ሚርያምን በሥጋ ደዌ መታት። ይህ አስከፊ በሽታ የሚርያምን ቆዳ “እንደ በረዶ ነጭ” አደረገው። ወዲያውኑ አሮን፣ ሙሴ እርምጃ እንዲወስድ ለመነው፤ “የፈጸምነው የሞኝነት ድርጊት ነው” በማለት በሙሴ ፊት ራሱን ዝቅ አደረገ። የዋህ ሰው የሆነው ሙሴም “አምላክ ሆይ፣ እባክህ ፈውሳት! እባክህ!” በማለት ወደ ይሖዋ ጮኸ። (ዘኁልቁ 12:9-13) የሚርያም ሁለት ወንድሞች ያቀረቡት ልመና ታላቅ እህታቸው ድክመት ቢኖርባትም ምን ያህል እንደሚወዷት ያሳያል።

ሚርያም ተፈወሰች

 ይሖዋ ምሕረት የሚንጸባረቅበት እርምጃ ወሰደ። ንስሐ የገባችውን ሚርያምን ፈወሳት። ሆኖም ከእስራኤል ሰፈር ውጭ ለሰባት ቀን ተገልላ እንድትቆይ አደረገ። ይሖዋን በመታዘዝ ከእስራኤል ሰፈር ውርደት ተከናንቦ መውጣት ለሚርያም በጣም አሳፋሪ መሆን አለበት። ሆኖም እምነቷ አድኗታል። አፍቃሪ አባቷ ይሖዋ ፍትሐዊ አምላክ እንደሆነና ተግሣጽ የሰጣት በፍቅር ተነሳስቶ እንደሆነ ተገንዝባ እንደነበር ጥያቄ የለውም። በመሆኑም እንደታዘዘችው አደረገች። ሰባቱ የብቸኝነት ቀናት እስኪያልፉ ድረስ እስራኤላውያን ጉዟቸውን አልቀጠሉም። ከዚያም ሚርያም በድጋሚ እምነቷን አሳየች፤ ወደ ሰፈሩ ተመልሳ እንድትቀላቀል ሲደረግ በትሕትና እሺ አለች።—ዘኁልቁ 12:14, 15

 ይሖዋ የሚወዳቸውን ይገሥጻል። (ዕብራውያን 12:5, 6) ሚርያምንም በጣም ስለሚወዳት የኩራት ዝንባሌዋን ሳያርም ሊተዋት አልፈለገም። የተሰጣት እርማት ቢጎዳትም አድኗታል። ተግሣጹን በጥሩ ሁኔታ ስለተቀበለች የይሖዋን ሞገስ መልሳ ማግኘት ችላለች። እስራኤላውያን በምድረ በዳ የቆዩበት ጊዜ ሊጠናቀቅ እስከተቃረበበት ጊዜ ድረስ በሕይወት ኖራለች። በጺን ምድረ በዳ ውስጥ በቃዴስ በሞተችበት ወቅት ዕድሜዋ ወደ 130 ዓመት ሳይጠጋ አልቀረም። b (ዘኁልቁ 20:1) በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ይሖዋ ሚርያምን በታማኝነት ላከናወነችው አገልግሎት አክብሯታል። በነቢዩ ሚክያስ አማካኝነት ለሕዝቡ “[ከባርነት] ቤት ዋጀሁህ፤ ሙሴን፣ አሮንንና ሚርያምን በፊትህ ላክሁ” በማለት ተናግሯል።—ሚክያስ 6:4

የሚርያም እምነት ይሖዋ ተግሣጽ ሲሰጣት በትሕትና እንድትቀበል ረድቷታል

 ከሚርያም ታሪክ ብዙ ትምህርት እናገኛለን። በልጅነቷ እንዳደረገችው እኛም ረዳት የሌላቸውን መታደግና ትክክል ለሆነው ነገር በድፍረት ጥብቅና መቆም ይኖርብናል። (ያዕቆብ 1:27) እንደ እሷ ስለ ይሖዋ በደስታ ማወጅ ያስፈልገናል። (ሮም 10:15) እንደ ቅናትና ምሬት ያሉ መርዛማ ባሕርያትን ማስወገድ እንዳለብን ከእሷ እንማራለን። (ምሳሌ 14:30) እንዲሁም ልክ እንደ እሷ ይሖዋ የሚሰጠንን እርማት በትሕትና መቀበል ይገባናል። (ዕብራውያን 12:5) እንደዚህ ካደረግን ሚርያምን በእምነቷ መምሰል እንችላለን።

a ከሲፓራ ጋር በተያያዘ “ኩሻዊት” የሚለው ቃል የተሠራበት ኢትዮጵያዊት መሆኗን ለማመልከት ሳይሆን እንደ ሌሎቹ ምድያማውያን ከዓረብ አገር የመጣች መሆኑን ለማመልከት ነው።

b ሚርያም፣ አሮንና ሙሴ የሞቱት በተወለዱበት ቅደም ተከተል ነው፤ መጀመሪያ ሚርያም፣ ቀጥሎ አሮን፣ በመጨረሻም ሙሴ። ከሁኔታዎቹ መረዳት እንደሚቻለው ሦስቱም የሞቱት በአንድ ዓመት ውስጥ ነው።